>
5:13 pm - Wednesday April 20, 2507

የኢንጅነሩ ጉዳይ!!! (መስከረም አበራ)

የኢንጅነሩ ጉዳይ!!!
መስከረም አበራ
* እጅግ የወረደ አሳፋሪ የምርመራ ውጤት
•ኢንጂነር ስመኘው ራሱን አጥፍቷል የሚለውን የመንግስትን ሪፖርት እንዳላምን ያደረገኝ በኢቲቪ ካየናቸው ሃቆች ብቻ ብንነሳ የስመኘው ሬሳ ወንበር ላይ ተመቻችቶ ኮፍያው ውልፊት ሳትል ተቀምጦ መታየቱን የሚክድ ሰው የለም፡፡ ሰው በጥይት ሲሞት ቀርቶ አንገቱን ለተወሰነ ሰኮንድ ቢታነቅ እንደሚንፈራፈር የሚታወቅ ነው፡፡
•ታዲያ በሽጉጥ ራሱን ያጠፋው ስመኘው ኮፍያው ሸርተት ሳትል ተመቻችታ እንደተቀመጠች ሞቶ የተገኘው  ስመኘው መኪናውን ዘግቶ ራሱን ገደለ ቢሉኝ ለማመን አልችልም-አውቄ ካልተኛሁ በቀር! ስመኘው ሰው ነውና ነፍሱ ሲወጣ ይንፈራፈራል፡፡ እንደዛ በጥንቃቄ አንገቱን ብቻ ዘንበል አድርጎ መሞት የሚችለው ቀስ ብሎ በእንቅልፍ መልክ እንዲሞት በህክምና ባለሙያ መደምስር በሚሰጥ መግደያ መንገድ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ የፖሊስ ማስረጃ አሳመነን የምትሉ ወገኖች ይህችን በተለይ ብታስረዱኝ ደስ ይለኛል፡፡
•ፖሊስ ሰውየው ራሱን ለመግደሉ ማስረገጫ ካላቸው ማስረጃዎች አንዱ የሽጉጡ በሟች ስም መመዝገብ ነው፡፡ ሰው በስሙ በተመዘገበ ሽጉጥ በሌላ ሰው አይገደልም ያለው ማን ነው? ስመኘው ሽጉጡን በስሙ ያወጣው ይዞት ሊንቀሳቀስ ነው፡፡ስለዚህ ሽጉጡ በማንኛውም ሰዓት በስመኘው መኪና ውስጥ የመኖር እድሉ ይሰፋልና ገዳይ ሽጉጥ ይዞ መጥቶ በሌላ ሽጉጥ ቢገድለውና  የስመኘውን ሽጉጥን ከመኪናው ውስጥ አንስቶ  ለሟች አስከሬን ማስጨበጡ የማይታሰብ አጋጣሚ የሆነው እንዴት ነው? በስሙ ያወጣውን ሽጉጥ ከሟች አጠገብ የሚያስቀምጥ ገዳይ ይኖር ይሆን?
•ፓስታዎች ተላኩ የተባለው ነገር ደግሞ ቢያንስ የፖስታዎቹን ይዘት ሊነገረን፣ቢበዛ ደብዳቤው በኢቲቪ ሊታይ ይገባ ነበር፡፡ የስመኘው ነገር ሰውን ሁሉ በጥፍሩ ያቆመ ነገር መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ሆኖም ሰውየው አንደበቱ በተዘጋበት ሁኔታ  ፖስታውን ስመኘው ይላከው አይላከው ራሱ ከጥርጣሬ የፀዳ ነገር አይደለም፡፡
•የፖስታው ነገር እውነትነ ነው ብንል እንኳን በፖስታው ላይ ያለው ፊርማ የስመኘው እንደሆነ አረጋግጠናል የሚለው ማስረጃ ራሱ ስመኘውን ገዳዮቹ አስገድደው ሊያስፈርሙት ይችላሉ ተብሎ ያልታሰበው ለምን ይሆን? ከፖስታው ጋር በተያያዘ የተነሳው ሌላው አስቂኝም አሳዛኝም ነገር አንድ እምቦቀቅላ ልጆቹን ጥሎ በመሞት ስነ-ልቦና ውስጥ ያለ ሰው እጅግ የተረጋጋ ከሆነ እንኳን አንድ  ወረቀት ጫር ጫር አድርጎ በሚሞትበት አካባቢ ያስቀምጥ ይሆናል እንጅ ለተለያዩ ሚኒስትር መስሪያቤቶች እና ባለስልጣናት በግልባጭ በግልባጭ እየፃፈ አንዱን ለሾፌሩ፣አንዱን ለሌላ ፣ቀሪውን ሬሳ ሊያነሳ ለሚመጣ ፖሊስ አዘጋጅቶ ማከፋፈሉ ግሩም ነው!
•ለፀሃፊው ስልክ ደውሎ ሌላ ቦታ ልሄድ ስለሆነ ልጄን ጠይቂው እኔ ሌላ ሃገር ልሄድ ነው፤ ስልኩን ቴክስት አደርግልሻለሁ አለ የሚለው ራሱን ለመግደሉ ማስረጃ ሆኖ መቅረቡ በጣም  አስገራሚ ሰው ንቀት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን ሊገድል ያለ ሰው ልጁን አደራ የሚሰጠው የልጁን ስልክ ለማታውቅ ፀሃፊው መሆኑ በጣም ግሩም ነው፡፡
• ስልኩን እልክልሻሁ ልጄን አደራ ማለት ይህች ሰው ከዚህ በፊት ከልጁ ጋር የመደዋወል ልምድ እንደሌላት ማስረጃ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ከሰው የተፈጠረ ሰው፣ ዘመድ አዝማድ ያለው አባት ልጁን ለፀሃፊ አደራ የሚሰጠው ታሪከኛው ስመኘው ብቻ መሆን አለበት! ነገሩ እውነት ቢሆን ስመኘው አክስት አጎት፣የቅርብ ጓደኛ  ያለው ሰው ነው፣ ከሰው የተፈጠረ ሰው ነውና ልጁን ለፀሃፊው አደራ የሚሰጥበት ነገር እንደምንም ብየ ባስበው ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡
•መኪናውን ከውጭ መዝጋት አይቻለም የሚለው ነገር ራሱ ገዳይ አቅጣጫ ለማስቀየር ሰውየው ራሱን ገደለ ለማስባል ሲል  ማድረግ የማይችለው ነገር ነው የሚለው የመጨረሻ ድምዳሜ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ጥይት በቀኝ ጆሮ ገብቶ በግራ በኩል መውጣቱ ራስን ለመግደል ምልክት ነው ተብሎ መቀመጡም አስገራሚ ነው፡፡
• ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለመግለፅ ጊዜ መውሰዱ ለህዝብ አሳማኝ ነገር ይዞ ለመምጣት እና ጥልቅ ምርመራ ለማድረግ ነው የሚለውን ነገር እንመን፣ የቀረበው ነገርም የወሰደውን ጊዜ ያህል “ጥልቅ ምርመራ የጠየቀ መጠቅ ያለ ነው”እንበልና ሌላ ጥያቄ እናንሳ ምርመራው ይቀርባል ጠብቁ  ከተባለበት ቀን በኋላ ለሁለት ጊዜ የተዘዋወረው ለምንድን ነው?
•በመጨረሻም የፖሊስን ምርመራ ለማመን በግድ የዋህ ለመሆን የምትሞክሩ ሰዎች ለመከላከል የምትፈልጉት ምን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የሞተው የእኛ ከምትሉት ወገን ቢሆንና መንግስቱ ደግሞ ከእናንተ ሰፈር ያልሆነ ቢሆን ምን እንደምትሉ እናውቃለን፡፡ ትዝብት ነው ትርፉ፤ሁሉም የአጅን ያገኛል።
Filed in: Amharic