>

ዕርቅና ይቅርታ እና ፍትሕና ርትዕ በድጋሚ ሲፈተሽ (ከይኄይስ እውነቱ)

ዕርቅና ይቅርታ እና ፍትሕና ርትዕ

በድጋሚ ሲፈተሽ

ከይኄይስ እውነቱ

ከተጠቀሰው ርእሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የግሌን ምልከታ/አስተያየት አቅርቤአለሁ፡፡ እነዚህን አስተያየቶች ከሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡

ዕርቅ፣ ብሔራዊ መግባባት ከማን ጋራ? 03/04/2016 

 ማንም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ ሊሆን አይገባውም 07/06/2018 

‹‹ይቅር ለእግዚአብሔር›› እና ‹‹ዕርቅ ደም ያደርቅ›› 06/07/2018 

በርእሱ ላይ ዕርቅ፣ ይቅርታ ያልናቸው ቃላት ትርጓሜ ‹‹ዕርቀ ደም ያደርቅ›› በሚለው አስተያየት ውስጥ ስለሚገኝ ያንን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ለመግቢያ ያህል ፍትሕና ርትዕ ከሕግ÷ ከፍርድ÷ ከሥርዓት ÷ ከደንብ ÷ ከውሳኔ ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ በተለይም ርትዕ እውነተኛ ፍርድ÷ የቀና ÷ የተስተካከለ ÷ ሐሰትና ግፍ የሌለበት÷የሚገባ ሥራ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰወስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በሚለው መጽሐፋቸው ይገለጹታል፡፡ ባንፃሩም ዕርቅና ይቅር ለእግዚአብሔርን ከሕግ አስገዳጅነት ይልቅ በባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት በበጎ ችሮታ÷በአገር ልማድ÷ዕድር÷በማኅበረሰብ መልካም ፈቃድና ስምምነት ከቤተሰብ እስከ አገር ያለን አለመግባባት በመፍታት ለጋራ ህልውናና አብሮነት፣ ዕድገትና ልማት ወዘተ አመቺ የሆነ ማኅበረሰባዊ መልካም መስተጋብርን መፍጠሪያ መንገዶች አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡  

ፈትለ ነገሩን በድጋሚ እንድጎበኝ ያስገደደኝ ዐቢይ ምክንያት የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ቊጥራቸው ቀላል የማይባል የሕብረተሰቡ ክፍሎች (የለውጡ ደጋፊዎችና ሸማቂዎች ጭምር) ሳይገባቸውና በወረት፣ አንዳንዱም የነገር ማዋዣና ማጣፈጫ በማድረግ፣ እኩሉም በፌዝና ስላቅ፤ የተወሰኑቱም በቅንነት የሚያነሱት፤ ብዙኃን መገናኛን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነት የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታና በባዶ የቃላት ጋጋታነት ሲጠቀሙበት የሚስተዋለው፤ እና ከታሰበበት ዓላማ ውጭ ትርጕም እየተሰጠው ወይም ትርጕም አልባ እየሆነ የሚገኘው ‹‹ዘመኑ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር ነው፡፡›› የሚለው በወቅቱ የገነነ አባባል በዕርቅ፣ በይቅርታ እና ፍትሕ ረገድ ያለንን አረዳድ እጅጉን የተዛባ ማድረጉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በጅምር የሚገኘውን የለውጥ ተስፋ ለማየት የበቃው እንደ ተራራ የገዘፉ፣ እንደ ባሕር አሽዋ የበዙ፣ እንደ ውቅያኖስ የሰፉና የጠለቁ ግፎችንና በደሎችን÷ መከራንና ሰቈቃን÷ዝርፊያንና ምዝበራን ለሦስት ዐሥርት የሚጠጉ ዓመታት ካስተናገደ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ በሕዝብና አገር ላይ የተፈጸሙ ግዙፍ ጥፋቶች በድርጅት፣ በቡድንና በግለሰብ ደረጃ ተፈጽመዋል፡፡ ከሞትና አካል ጉዳት የተረፈው ነፃነቶቹንና መብቶቹን ተገፎ በመሸጦነት ከመኖሩ በተጨማሪ ድፍን 27 ዓመታት ከሕይወቱ ላይ ተሠርቆበታል፡፡

ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንት ጭምር ሕይወታቸውን የገበሩለት ሕዝባዊ ትግል ዓላማዎች መካከል አንዱ በአገራችን የሕግ የበላይነት በዚህም ፍትሕና ርትዕ የሰፈነበት ሥርዓት ለማምጣት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕግ የበላይነትን የምናረጋግጠው፤ ፍትሕና ርትዕ ማስፈን የምንችለው ደግሞ በሕዝብና ባገር ላይ እነዚህን ግዙፍ የጥፋት ቁንጮዎች በወልም ሆነ በተናጥል የፈጸሙ አካላት በነፃና ገለልተኛ ዳኝነት ተዳኝተው ተገቢውን ፍርድ ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ ተመሳሳይ ግፍና በደል ዳግም እንዳይፈጸም ዋስትና ሊሰጡን ከሚችሉ ርምጃዎች አንዱ በአገዛዞችና ተባባሪዎቻቸው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ያለተጠያቂነት የማለፍ ባህል (culture of impunity) ማቆም ስንችል ነው፡፡ በዚህ መልኩ ፍትሕና ርትዕ ስናደላድል ብቻ ነው የሞቱ ወገኖቻችንን ማክበራችንን÷ ነፍሳቸው ዕረፍት እንድታገኝ÷ የተሠዉለት ዓላማ ከንቱ እንዳልሆነ፣ ዘመድ ወገኖቻቸውንም ማጽናናታችንን ማረጋገጥ የምንችለው፡፡ ይህንን ቊልፍ ጉዳይ ሕዝቡም ሆነ የለውጡ አመራር ኃይሎች ለአፍታም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ትክክለኛውና አመቺው ጊዜ መቼ ይሁን የሚለው ከአገር መረጋጋትና የለውጥ አስተዳደሩ መንበሩን ከማፅናቱ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተጨማሪ አገዛዝን ተገን በማድረግ በይቅርታ ሊታለፉ የሚችሉ ጥቃቅን ወንጀሎችን የፈጸሙ የድርጅትና የቡድን አባለት ወይም የጥቅም ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እውነትን ባደባባይ በመናዘዝ፣ ሕዝብን ይቅርታ በመጠየቅና በቅሚያ/ዝርፊያ የሰበሰቡትን ሀብት በመመለስ በሕጋዊ የይቅርታ ሥርዓት ሊስተናገዱ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ፍትሕና ርትዕ የማስፈኑ ዐቢይ ተግባር የ27 ዓመታቱን የጨለማ ምዕራፍ መዝጊያ ቀዳሚውና ዋናው መንገድ ነው፡፡ ይህንን ተግባር ከዕርቅና ይቅርታ ሥርዓት ጋር ማምታታት የለብንም፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ባለፉት 27 ዓመታት የገጠማት ችግር እጅግ ውስብስብና ሥር የሰደደ፣ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ድቀት ጭምር ያስከተለ በመሆኑ፤ የዘር ፖለቲካው ጦዞ በኹሉም የአገሪቱ ክፍል ጥላቻና ቂም በቀል÷ጥርጣሬና አለመተማመን÷መለያየትና ጽንፈኝነት በመንገሡ፤ በመገፋት÷ከቤት ንብረት በመፈናቀል÷በስደት÷ኢፍትሐዊ በሆነ የሀብት ክፍፍል ምክንያት የተፈጠረው ድርብ ድርብርብ ድህነት÷ባጠቃላይ በተፈጠረው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ምክንያት ብዙዎች የታመቀ እልህና ቁጣ ይዘው ይገኛሉ፡፡ ይህም ብሔራዊ ሕማም ስለሆነ ፈውስ ይፈልጋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ቁስል የሚያጠግገው በብሔራዊ የዕርቅ እና ይቅር ለእግዚአብሔር ሥርዓት እንደሆነ ብዙዎችን የሚያስማማ ሲሆን፤ ያሳለፍነውና በኢትዮጵያ ምድር በጭራሽ እንዳይደገም የምንፈልገው የብሔራዊ ውርደት ምዕራፍ መዝጊያ ሁለተኛው መንገድ ይሆናል፡፡

በአፈጻጸም ረገድ የፍትሕና ርትዕ የማስፈኑ ጉዳይ የሕግ የበላይነትን መርህ አድርጎ በሚቋቋም ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት (ፍርድ ቤት÷ ዐቃቤ ሕግ÷ ፖሊስ÷ ማረሚያ ቤቶች ወዘተ) የሚታይ ሲሆን፣ በዋናነት ሙያን÷ተግባራዊ ልምድን÷ቅንነትና የሞራል ልዕልናን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም ነው፡፡ ባንፃሩም የዕርቅና የይቅር ለእግዚአብሔሩ ሥርዓት ምሰሶዎች ወያኔ በእጅጉ ያዳከማቸው ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም የሃይማኖት አባቶች÷የአገር ሽማግሌዎች÷የማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ታዋቂ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች÷ ለወያኔ አገዛዝ በሎሌነት ያላደሩ ምሁራን ናቸው፡፡

አሁንም አጽንዖት ሰጥቼ መናገር የምፈልገው ‹‹መደመር›› በየትኛውም መመዘኛ የሌቦችና ወንበዴዎች መሸሸጊያ ዋሻ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ያለ ጋጠ ወጥ ኹላ (እላይ የጠቀስናቸውን 2 ሥርዓቶች ውስጥ ሳያልፍ) በማድበስበስ የሚጠለልበት ዣንጥላ አይደለም፡፡ ባሁኑ ሰዓት ሕዝብና አገርን የታደጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከስደት ወደ አገር ቤት እየገቡ እንደሆነ ኹሉ፤ በመርዘኛ ንግግራቸውና በግፍ ድርጊቶቻቸው ሕዝብና አገርንም የበደሉ ዕኩያንና ዕቡያንም ‹‹ተደምረናል›› በሚል ፌዝ (እላይ የጠቀስናቸውን 2 ሥርዓቶች ውስጥ ሳያልፉ) አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ መግባታቸው መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነሱም ጭምር አገር ናትና፡፡ መግባታቸው ለተጠያቂነትም ያመቻል፡፡ ለፈጸሟቸው ነውሮች ኃላፊነት መውሰድ ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም በልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የተጠለሉ በዳዮች ዕውነትን ተናዝዘው በበደሉት ሕዝብ ፊት ንስሓ ገብተው ይቅርታ ሳይጠይቁ ዝም ብሎ በመንጋነት መቀላቀል የለም፡፡ አሁን ባገር ማረጋጋት ሽፋን የምናየው ግን ለፍርድ ሊቀርቡ የሚገባቸውና አንዳንዶቹም በዕርቅና ይቅርታው ሥርዓት ውስጥ ማለፍ የሚገባቸው ግለሰቦች እንደ ‹ጀግና› የአበባ ጉንጉን በማጥለቅና ከፍተኛ የሆቴል ወጪአቸው በመንግሥት (በሕዝብ ሀብት) እየተሸፈነ የሚደረገው አቀባባል ማስተዛዘብ ብቻ ሳይሆን  ሕዝብን ክፉኛ እያስቆጣ ነው፡፡ ግፍና በደል የተፈጸመባቸው በፍርድና በገንዘብ ሳይካሡ÷ሳናቋቁማቸው በደለኞችን ማስታመም በቁስል ላይ እንጨት መስደድ ይሆናል፡፡ እንዴት ዓይነት ይሉኝታ ማጣት ነው? በዚህ የለውጥ ሂደት ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ የታየው ባንዳንና ለአገሩ አስተዋጽዖ ያላደረገን የስም ስደተኛ አክብሮ ላገር ዋስ ጠበቃ የሆኑትን ጀግኖች የማንኳሰስ አስነዋሪ የታሪክ ምዕራፍ (‹ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ› በተባለው ብሂል የሚገለጸውን) ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዘጋት ይኖርበታል ፡፡

ስለሆነም ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉትን ወያኔዎችን (ሕወሓቶች) እና ተረፈ-ወያኔዎችን (ወያኔ ጠፍጥፎ በሠራቸው በ3ቱም ድርጅቶች/ደሕዴን፣ ብአዴንና ኦሕዴድ/ እና ‹አጋር› ባላቸው የጎሣ ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው – የአገር ህልውናና የሕዝብ ሰቈቃ አሳስቧቸው ሳይሆን በግል ምክንያታቸው በስደት ቆይተው እየተመለሱ ያሉትን) ሕዝባችን በንቃትና በቅርብ እንቅስቃሴአቸውን ሊከታተልና አገር ባንፃራዊነት ስትረጋጋ ለለውጡ አመራሮች ያለማቋረጥ በማስታወስና ግፊት በማድረግ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ለአብነት ያህል ጁነይዲን ሳዶን ማንሳት እፈልጋለኹ፡፡ ወንድሜ አቻምየለህ ስለዚህ ነውረኛ ግለሰብ ከጓደኛው ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ድውይ አስተሳሰቡን ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ላይ ስላለው ንቀት አካፍሎናል፡፡ ስለዚህ ግለሰብ ማስረጃን መሠረት በማድረግ ብዙ ማለት ቢቻልም በምርጫ 1997 ኮረጆ (የሕዝብን ድምጽ) በመሥረቅ፤ ወያኔ ‹ኦሮምያ› ብሎ የሰየመውን ክፍለሃገር ሲገዛ ሃይማኖትን እንደ ዘር መከፋፈያ በማድረግ ያደረሰው ቀውስ፤ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር በነበረበት ጊዜ በሚኒስቴሩና በሥሩ ባሉ መ/ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን የቅንጅት አባላት ናችሁ በማለት ለወያኔ የደኅንነት ተቋም ስም ዝርዝራቸውን አሳልፎ ከመስጠቱ በተጨማሪ፣ በወቅቱ ቴሌ ኤጀንሲ ውስጥ ሲያገለግል የነበረና የአካል ጉድለት ያለበት (በሁለት የድጋፍ ምርኵዞች የሚንቀሳቀስ) ሠራተኛ ላፕ ቶፕ ኮምፒውተሩን (የአረመኔውን የመለስን ምስል የያዙ የካርቱን ምስሎችና የስላቅ ፎቶግራፎች ይሰበስብ ነበር) በካድሬዎቹ ጠቋሚነት በመውሰድ ለወያኔ ደኅንነቶች አሳልፎ መስጠቱን አንዘነጋም፡፡ (ግለሰቡ አሁንም በሕይወት ስላለ አንድ ቀን ወጥቶ ምስክርነቱን እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለኹ)  ግለሰቡ በወቅቱ ተከሶ ከብዙ መጉላላትና እስር በኋላ ነፃ ወጥቷል፡፡ ደኅንነቶቹ ለጁነይዲን ባለቸው ንቀትና ጉዳዩም የግሉ በመሆኑ ግለሰቡ ነፃ ቢወጣም ተሰሚነት ያለው ባለሥልጣን ቢሆን ኖሮ ሊገደል የሚችልበት አጋጣሚ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የትልቁ ሥዕል ጥቂት ማሳያ ፍንጮች እንጂ ይህ አቋም የሌለው፣ የተሰጠውን ሥልጣን እስከ ጥግ ድረስ አላግባብ በመጠቀም (excessive abuse of power) የሚታወቅ፣ በተመደደበበት ኃላፊነት ኹሉ ፊደል እንዳልቆጠረ ሰው ራሱን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ በራሱ የማይተማመን፣ መለስ በመጨረሻ ንቀት የሚመለከተው ማፈሪያ ሰው ነው ጁነይዲን ሳዶ፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ነውረኛ ነው የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች በክብር የሚቀበሉትና መጠለያ የሚሰጡት፡፡ ይህ ነው የዘር ፖለቲካ እብደትና ጭፍን መንጋ ደጋፊነት አንዱ መገለጫው፡፡ በነገራችን ላይ እነ አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርዐ ጽዮን፣ ታምራት ላይኔ፣ ስዬ አብርሃ፣ ጻድቃን ገ/ትንሣይ፣ አበበ ተ/ሃይማኖት ወዘተ አሁን መድረክ አገኘን እያሉ ቢያናፉም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርድ አያመልጡም፡፡

ይህንን አስተያየት እየጻፍኹ ባለሁበት ጊዜ ማኅበረ አንድነትንና ሀገራዊ ህላዌን በማናጋቱ ዕኩይ ተግባር የተጠመደው ወያኔ ትግሬ ‹ክልል› ብሎ የሰየመውን አፓርታይዳዊ የአትድረሱብኝ አጥር መከታ በማድረግ መንግሥት የሌለበት አገር ይመስል የራያ ወገኖቻችንን እያዋከበ ይገኛል፡፡ እስከ መቼ ይሆን እንዲህ ዓይነቱ ግፍ በ‹ክልል› ስም በዜጎቻችን ላይ ሲፈጸም የሚኖረው? በውሸት ‹ፌዴራል ሥርዓት› ስም በዝርፊያ ሀብትና መሣሪያ ያበጡ የመንደር ጉልበተኞች በዜጎች ላይ የሚያካሂዱትን የሽብር ድርጊት ማዕከላዊው መንግሥት እስከ መቼ ይሆን በዝምታ የሚያልፈው? ጥንቃቄው ቢገባንም ለዜጎች ደኅንነት ካለብን ኃላፊነት ጋር ማመዛዘኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔንና ግብር አበሮቹን በሚመለከት የፍትሕ ያለህ እያለ አጥብቆ የሚጮኸው ለህልውናው መሠረት በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

በመጨረሻም ዕርቅና ይቅርታን እና በፍርድ የሚገኝ ፍትሕና ርትዕ እርስ በርስ የሚጋጩ ሥርዓቶች ሳይሆኑ፣ ማኅበራዊ ሰላምና አንድነት ለማምጣት አንዱ ሌላውን የሚያጠናክር የሚያሟላ አድርጎ ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

Filed in: Amharic