>
5:13 pm - Monday April 18, 8444

የጃዋር መልስና አንድምታው (መላኩ አላምረው)

የጃዋር መልስና አንድምታው
መላኩ አላምረው 
* ጃዋር መሃመድ ለታማኝ በየነ ጥሪ በፌስቡክ ገጹ መልስ ሰጠ፡፡ (አማራነትን ትታችሁ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ስበኩ ለምትሉም የጃዋርን/ኦሮሞን በተለየ እና የሌሎችን ብሔሮች አቋም በጠቅላላ ያሳያል!!!
-›
‹‹ታማኝ ‹ለኢትዮጵያ ህዝብ ታገል› በማለት ያቀረበልኝ ጥሪ ከቅንነት የመነጨ ይመስለኛል። ነገር ግን በጣም የዘገየ ጥሪ ነው። በትግላቻን አምባገነናዊ ስርዓቱን ፈረካክሰን የኢትዮጲያን ህዝብ ሁሉ ከአፈና ነጻ ካወጣነው በኋል ዘግይቶ የቀረበ ጥሪ ነው። በተጨማሪም የ ‘ትግል’ ጥሪው የትግል ፖሊቲካን (resistance politics) በድል አጠናቀን ወድ አስተዳደራዊ ፖሊቲካ ( governance politics) ከተሸጋጋርን በኋል አመሻሽቶ የደረሰ ጥሪ ነው። ልክ በተዋጣለት ስትራቴጂ አይበገሬ የተባለለትን አምባገነናዊ ስርዓት እንደደረመስነው አሁንም ህብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ዴሞክራቲክ ኢትዮጲያን ለመገንባት በከፍተኛ ፍጥንት እና ጥንቃቄ እየሰራን ነው። ይህን ስናደርግ ደግሞ ‹ማንነታችንን ፍቀንና ብሄራችንን ክደን› አይደለም። ትላንትም እንደ ኦሮሞ ታግለን ከሌሎች ብሄር ታጋዮች ጋር ተበበረን ይሄንን ለውጥ አመጣን። ትግሉ በቄሮ፣ በፋኖ እና ዘርማ ቢካሄድም የተገኝው ለውጥ እየጠቀመ ያለው ሁሉንም ያሀገራችን ህዝብ ነው። ትላንት በብሄር መደራጀት ሀገር ያፈርሳል ሲሉ ሀገርን ከመፈራረስ አድነትን አሳይተናል። ሰላማዊ ትግል አማባገነናዊ ስርዓትን ለመቀየር አያስችልም ብለው ሲያላግጡብን የነበሩትን በተጨባጭ በስራ አሳይተናቸው የድሉ ተጠቃሚ እንዳደረግን ሁሉ ወደፊትም ውጤት ተኮር አመራር መስጠቱን እንቀጥላበታለን።››
-›
ቁልፉ የጃዋር መልእክት… ዝም ብሎ ‹‹ኢትዮጵያዊ ብቻ ነኝ እያሉ በኢትዮጵያዊነት ለመታል ጊዜው አይፈቅድም፡፡ ከኦሮሞ ጋር በአንድነት ለመጓዝ በአማራነት ተደራጅ፤ አሁን እናንተን የኢትዮጵያዊነት ታጋዮችንም ነፃ ያውጣናችሁ እኛ ብሔርተኞች ነን፡፡ አሁንም በድል አጠናቀን እየመራን ያለነው እኛ ነን እንጅ እናንተ አይደላችሁም፡፡ እኛ ብሔርተኞች በፈጠርንላችሁ ነፃነት ተጠቀሙ…›› ነው፡፡ ይህ ማለት ጃዋር ተሳስቷል ማለት አይደለም፡፡ ጃዋር የኦሮሞ ብሔርተኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ለኦሮሞ ቅድሚያ መስጠቱም (‹ኦሮሞ ፈርስት› ማለቱም) ቢሆን ልክ ነው፡፡
-›
ሐቁን እንቀበል፡፡ ትናንት ‹‹ኢትዮጵያዊነት ብቻ›› ሲል የኖረው አማራ ነው፡፡ ነገም ኢትዮጵያን እስከመጨረሻ የሚፈልጋት በዋናነት አማራ ነው፡፡ አማራ ይፈልጋታል ማለት ሌሎች አይፈልጓትም ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የሚፈልጓት እስካ ድረስ አማራም በኢትዮጵያዊነቱ አለ፤ ይኖራልም፡፡ በአማራነት እንደራጅ፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ማንም አይወስድብንም፤ ከእኛ በላይ አይፈልገውምም፡፡
ከአሁን በኋላ በአማራነት ሳይደራጁ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ማቀንቀን አማራን ሌሎች ብሔርተኞች እንደጀመሩት አፈናቅለውና አሳደው ሕልውናውን ያሳጡት ዘንድ ተስማምቶ እንደመቀመጥ ይቆጠራል፡፡
አማራነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን የአንድነቷ ዋስትና ነው የምንለው ዝም ብለን አይደለም፡፡ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እያየን እንጅ፡፡
በአማራነት መደራጀት የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የቅንጦት ፖለቲካ ጨዋታ አይደለም፡፡ ሌሎች ብሔርተኛ ስለሆኑ ብሔርን የመፈለግ ጉዳይም አይደለም፡፡ ሌሎች የመገነብጠልና ራን የመቻል አላማ ይዘው ነው ብሔርተኛ የሆኑት፡፡ አማራ እንዳይጠፋ ራሱን ከተደገሰለት ጥፋት አድኖ ሕልውናውን ለማስቀጠል ነው፡፡
የሕልውና ጉዳይ እና የመገንጠል አላማ ተለይተው ካልታዩ አንግባባም፡፡ በብሔርተኝነታው የከሰሩ አሉ፤ እውነት ነው፡፡ የከሰረ አላማ ይዘው የተነሱት ከስረዋል፡፡ የመገንጠል አላማ ይዞ የሚነሳ ሁሉ ሊያተርፍ አይችልም፡፡ አማራ የመገንጠልም ከኢትዮጵያዊነት የመሸሽም ሐሳቡም ሕልሙም የለውም፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ሕልውናው አደጋ ስለተጋረጠበት ተደራጅቶ ለመመከት እንጅ ማንንም ለመበቀልና ለመገንጠል አይደራጅም፡፡ ማንንም ብሔር ጠላት አድርጎ አይነሳም፡፡ ከሁሉም ጋር በሕብረት ኢትዮጵያን ያስቀጥላል እንጅ ከኢትዮጵያ ስንዝር አይሸሽም፡፡
—›
በአማራነት መደራጀት ማለት የሌለን/ያልነበረን አማራ መፍጠር አይደለም፡፡
አማራ ትናንትም ከትናንት በፊትም በአማራነቱ ነበር፡፡ ልዩነቱ መደራጀት/አለመደራጀቱ ብቻ ነው፡፡ ትናንት አማራው በኢትዮጵያዊነት ነበር መደራጀትን የሚመርጠው፡፡ ፓርቲም አቋቋመ ሌላ ድርጅት ኢትዮጵያዊ ስም ሰጥቶ ነበር፡፡ ግን ኢትዮጵዊ ስም ሰጥቶ ሲደራጅ ያው ከአማራ ውጭ ማንም አይደግፈውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በተግባር ፈርሳ ሕገ መንግሥቱም ለብሔርተኞች ብቻ ስለተሰጠና በኢትዮጵያ ስም የሚመጣ ሁሉ ‹‹ትምክህተኛና የድሮ ሥርዓት ናፋቂ አማራ›› ተብሎ ስለሚፈረጅ፡፡
ሁሉም በየብሔሩ ተደራጅቶና አማራን በጠላትነትም በቅኝ ገዥነትም ፈርጆ ለበቀል በተግባር እየሠራ እያለ… አማራን አትደራጅ ማለት ማንም ያጥፋህ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሎ አደረጃጀት በተግባር እንደደሌለ እየታወቀ እንዴት ነው ኢትዮጵዊ ሆኖ መብቱን የሚያስከብረው….
አማራ መሆን ኢትዮጵያዊ ከመሆን አያግድም አይጎረብጥምም፡፡ የሌሎች ብሔርተኝነት ለመገንጠል ነው፡፡ የአማራ ግን ሕልውናን አረጋጦ ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ለመሸሽ ፈጽሞ አላማ የሌለው ብሔርተኝነት ነው የአማራ ብሔርተኝነት፡፡ ለቅንጦት ሳይሆን ለሕልውና ነው ስንል… ዛሬም በየሚኖርበት እየተሰቃየ ያለ ሕዝብ ነው ማታችን ነው፡፡ መፈናቀሉም መገደሉም ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብቻ ከመሆን በአማራነቱ ቆሞ ኢትዮጵያዊ መሆንን የመረጠው ወዶ አይደለም፡፡ ተገዶ… ተገፍቶ… ነው፡፡ መሬቱም ማንነቱም እየተወሰደበት ያለው ‹‹ኢትዮጵያዊ ብቻ ነኝ›› ብሎ በሀገር ፍቅርና ክብር ብቻ እየኖረ እያለ… ‹‹የለም ዘርህም ስነ ልቦናህም አማራ ነህ›› እየተባለ ነው፡፡ የአማራ ሕልውና አደጋ ላይ መሆን ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በአውነት ለኢትዮጵያ የሚጨነቅ ካ የዚህን ኢትዮጵያዊ የሆነን ሕዝብ ግፍ ለማስቆም ይትጋ፡፡ ያኔ በኢትዮጵያዊነት ቀድሞት የሚቆመው አማራ መሆኑን በተግባ ያያል፡፡ እንጅ አትደራጅ አይበል፡፡
===>
የታማኝ አይነት በኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚታገሉ መኖራቸው ለአማራ አይጎረብጥም ነበር ፡፡ ችግሩ በኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚታገሉት በሌሎች ብሔሮች ዘንድ ‹‹አማራ ናቸው›› ተብሎ ተፈርጆ አልቋል፡፡ እርግጥ በኢትዮጵያዊነት ለሚቆሙ ሁሉ ድጋፍ የሚያገኙት ከአማራ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለዶ/ር ዐቢይም እንኳን ከአማራ በላይ ድጋፍ የሰጠ ማንም የለም፡፡ ሐቅ ሐቅ ነው፡፡
Filed in: Amharic