>

"ካገሬ ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም የመጣሁት"  (ታማኝ በየነ - ዶችቬሌ) 

“ካገሬ ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም የመጣሁት
 ታማኝ በየነ 
ዶችቬሌ
ታማኝ በየነ ከ22 አመታት በኋላ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ገባ። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ለአመታት አበክሮ ይወተውት የነበረው ታማኝ አዲስ አበባ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ፖለቲከኞች፣ ድምፃውያን እና በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎች በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ ታይተዋል።
ታማኝ በየነን ለመቀበል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተገኙ መካከል እናቱ አንዷ ነበሩ። ያራመደው አቋም በእሱ ብቻ ሳይሆን በባለቤቱ በድምፃዊት ፋንትሽ በቀለ ላይ ጭምር ተጽዕኖ ማሳረፉን ተናግሯል።
 “እናቴ እዚህ ድረስ መጥታ ተቀበለችኝ። አባቴን ግን መቅበር አልቻልኩም። እንኳን እኔ ባለቤቴ እናቷን መቅበር አልቻለችም” ያለው ታማኝ ለውጡ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ታማኝ  “ለውጡ ትንሽ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ እናቷን መቅበር ትችል ነበር። እኔ በወሰድኩት አቋም፤ እኔ ባመንኩት ነገር እሷም አብራ ተቀጣች። ግን ይኸ ሁሉ ቂም የሚያዝበት አይደለም። ወደ ፊት ሌሎች እናቶች እንዲህ እንዳይሆኑ አገራችን የሰላም የፍቅር አገር እንድትሆን ሁላችንም ድርሻ አለን” ሲል አሳስቧል።
ለ22 አመታት በአሜሪካን አገር የኖረው ታማኝ “ካገሬ ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም የመጣሁት” ሲል ተደምጧል። ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ “ትኬት ቆርጬ ዝም ብዬ አይደለም የመጣሁት። ለእኔ መምጣት ህይወት የከፈሉ አሉ፤ የተገረፉ አሊሉ፤ መከራ የተቀበሉ አሉ” ሲል ብሏል። “ያጣሁትን አየር አንዴ ስቤ፣ ወገኖቼን አግኝቼ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታውን ገምግሜ እመለሳለሁ” ያለው ታማኝ ወደ ፊት በዘላቂነት መኖሪያውን በኢትዮጵያ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ታማኝ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በሙያው ከበሬታን ወዳተረፈበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አቅንቷል። በዚያም የደመቀ አቀባበል ተደርጎለታል።
Filed in: Amharic