>

"አቶ በረከት የኪራይ ሰብሳቢነት ፊታውራሪና ነፍስ አባት ናቸው" (አቶ መላኩ ፈንታ)

“አቶ በረከት የኪራይ ሰብሳቢነት ፊታውራሪና ነፍስ አባት ናቸው”

 አቶ መላኩ ፈንታ

ቢቢሲ
አቶ መላኩ ፈንታ* የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ በከፍተኛ ሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ለአምስት ዓመታት የታሰሩ ሲሆን ከእስር የተለቀቁት ከጥቂት ወራት በፊት ነው። በቀድሞ ፓርቲያቸው ብአዴን ውስጥ እየተወሰደ ስላለው እርምጃና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል:-

ጥያቄ፦ በአሁኑ ወቅት በብአዴን እየተካሄደ ያለው ለውጥ የምን ውጤት ነው ይላሉ?

አቶ መላኩ፦ እስር ቤት እያለሁ፣ ከወጣሁም በኋላ በብአዴንና በሌሎች ፓርቲዎች እንዲሁም በኢህአዴግ ውስጥ እየተደረጉ ያሉ ሁኔታዎችን ሳጤን በሕዝብ የመጣን ለውጥ አምኖ የመቀበልና ያለመቀበል የተለያየ ነገር ይታየኛል።

ለውጡን ተቀብለን እንምራ የሚል እና መቀበል ያልቻለም አለ።

ከዚህ አንፃር በቅርቡ ብአዴን እየወሰደ ያለውን እርምጃ፣ ስለ ውሳኔዎቹ የሚሰጣቸው መግለጫዎች፣ እንዲሁም ከአንዳንድ አባሎቹ ከምሰማው [ተነስቼ] ፓርቲው በትክክልም ሕዝብ ያመጣውን ለውጥ ተቀብዬ እመራለሁ ያለ ይመስለኛል።

ነገር ግን በዚህ ውስጥ ለውጥን በመቀበልና ባለመቀበል እንዲሁም በመተካካት ጉዳይ መሳሳብ፣ መገፋፋት ይታያል።

እስከማውቀው ድረስ የመተካካት ዕቅድ እኔ ከመታሰሬ በፊት የወጣ ነው፤ ትርጉም ባለው መልኩ ተፈፅሟል ማለት ግን የሚቻል አይመስለኝም።

ከተተካን መውጣት አለብን ብለው የወጡት አቶ ተፈራ ዋልዋ ብቻ ናቸው። ለእኔ እውነተኛ መተካካትን ተግባራዊ ያደረጉት [እርሳቸው ናቸው]። ሌላው ግን ከኋላ ሆኖ የመምራትና የመቀጠል ፍላጎት አለው።ይሄ ነገር ነው አሁን መሳሳብን እየፈጠረ ያለው።

የወጣቱን አዲሱን የፓርቲ አመራር አምኖ መልቀቅና መሰናበት ያለባቸው ሰዎች አሉ።በእርግጥ ለተፈጠረው ብዙ ጥፋት ተጠያቂ እንደረጋለን በሚል ስጋት ለውጡን የማይፈልጉት ያሉ ይመስለኛል። አንዳንዶቹ ደግሞ በታሪክ መኖር የሚፈልጉ ይመስለኛል። አንዳንድ ምዕራፎችን ለመዝጋት ታሪክ ጥሩ ነው።

ባለፈው የተከፈለ መስዋዕትነት አለ፤ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ነው።አሁን ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀው ነገር አለ።ወቅቱ ሕዝብ ልማት፣ ዲሞክራሲና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እየጠየቀ ያለበት ነው። በነጻነት ሐሳብ መግለፅ የሚቻልባት አገር ትፈጠር፣ የሞግዚታዊ ስሜትና አስተሳሰብ አይጫንብኝ እያለ ነው።

ይህን ነባራዊ ሁኔታ አምኖ መቀበልና ለዚህ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በብአዴንም [ኾነ]በኢህአዴግ እየተደረገ እንዳለው ለዚህ ዝግጁ የሆኑት መቀጠል አለባቸው፤ ያልሆኑት ደግሞ በክብር መሸኘት፣ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውም መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል።በፓርቲዎች እየተደረገ ያለው ፍትጊያ እነዚህን ማዕከል አድርጎ እየሄደ ይመስለኛል።

ጥያቄ፦ ስለዚህ ብአዴን በአቶ በረከት ስምኦንና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው እያሉ ነው?

አቶ መላኩ፦ በእኔ እምነት የዘገየ ካልሆነ በቀር በጣም ትክክለኛ እርምጃ ነው። እንደ አቶ በረከት ዐይነቱ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ስለ ጸረ ሙስና ትግል የሚዘምሩ ናቸው፤ በመድረክ ላይ፤ በተግባር ግን የኪራይ ሰብሳቢነት ፊታውራሪና ነፍስ አባት ናቸው። ለዚህ ነው የተወሰደው እርምጃ ዘግይቷል የምለው። የሕዝብን ጥያቄ ይዤ እመራለው የሚል ኃይል እየተፈጠረ ነው።የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ቆርጦ የመጣ ፤ ከሞግዚታዊ አስተሳሰብ ልላቀቅ ያለ ኃይል በእነሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የዘገዩ ካልሆኑ [በስተቀር] በጣም ተገቢ ናቸው።

ጊዜው ሲፈቅድና በተረዱበት ጊዜ እርምጃ መውሰዳቸው አመራሮቹን ሊያስመሰግናቸው ይገባል። አመራሮቹ ይህን እያደረጉ ያሉት የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እስከሆነ ድረስ የብአዴን አባሎች፣ ሕዝብና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉ ሊደግፏቸው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

ጥያቄ፦ለአቶ በረከትና አቶ ታደሰ መታገድ ምክንያት በጥረት ላይ የፈፀሙት ጥፋት እንደሆነ ብአዴን አስታውቋል።እርስዎ ደግሞ ጥረትና ኤፈርትን ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ለማድረግ ቆርጠው መነሳትዎ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ግጭት ውስጥ እንደከተትዎ ቀደም ሲል ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረው ነበር? በእርግጥ ጥረት ግብር እንዲከፍል ማድረግ ችለው ነበር?

አቶ መላኩ፦መጀመሪያ ላይ ጥረትንም ሆነ ኤፈርትን ወደ ግብር ሥርዓት ማስገባት ተግዳሮት ነበረው። በመጨረሻ ግን ሁለቱንም ማስገባት ችለናል። የጥረት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዮሴፍ ረታ ነገሩ እንዲሳካ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል።ከሳቸው ጋር ተረዳድተን ጥረትን ግብር ሥርዓት ውስጥ ማስገባት ችለናል።

ታክስ ብቻ ሳይሆን የልማት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢም ስለነበርኩኝ ብድር በመክፈል እንደማንኛውም ተበዳሪ ወደ ሥርዓት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ሠርቼ ነበር።አሁን [ያለፉት]አምስት ስድስት ዓመታት መረጃ የለኝም።

መጀመሪያ ‘ኪራይ ሰብሳቢውን ሳትታገሉ ግብር ክፈሉ፣ ታክስ ክፈሉ እያላቹ ለምን ክንዳችሁ እኛ ላይ ያርፋል’ የሚል ሽፋን ነበር። የኛ ነጥብ ደግሞ ማንኛውም ግብር ከፋይ ነኝ ያለ፣ በሥርዓቱ ብድር ተበድሬ እከፍላለው ያለ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በሥርዓቱ መዳኘት አለበት የሚል ነበር።

አሁን እየሰማሁ እንዳለሁት ግን ግለሰቦቹ እየተጠየቁ ያሉት ጥረትን ይመሩ በነበረበት ወቅት ድርጅቱ ውስጥ በነበረ ሙስናና ብልሹ አሠራር ነው።

በርግጥ ከመታሰሬ በፊት የማውቀው ፣ እሰማ የነበረውና አባላትም ያነሱ የነበሩት ነገር ነው። በጥቅሉ ያደረጉትን የኦዲት ሪፖርት እና ጥናት ባላውቅም ለረዥም ጊዜ ድርጅቱ የቤተሰብ ቤት፣ ግለሰቦች እንደፈለጉ የሚመሩት ድርጅት ሆኗል ተብሎ ጥያቄ ሲነሳ ነበር።

የሕዝብ የሚባል ድርጅት የቤተሰብ ሆኗል ከተባለ በድርጅቱ ብልሹ አሠራር ለመንገሡ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ትንታኔ አያስፈልገውም።ውጤታማነቱም ከሌሎች ተመሳሳይ ኢንዶመንቶች አንፃር ሲታይ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ እንደነበር መገመት የሚቻል ይመስለኛል።

ጥያቄ፦ ብአዴን ለህወሓት ፍላጎት ይገዛ ነበር፤ ግንኙነታቸውም የአቻ ፓርቲዎች አልነበረም ይባላል።እርስዎ ፓርቲው ውስጥ እያሉ ግንኙነታቸው እንዴት ነበር?

አቶ መላኩ፦ይህን ነገር በሁለት መንገድ መመልከት ይቻላል።በአንድ በኩል ብአዴን በራሱ ለክልሉ ሕዝብ ተጠቃሚነት ያደረጋቸው ነገሮች [እንዳሉ ሁሉ] ተጠያቂ የሚሆንባቸው ነገሮችም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የህወሓት የበላይነት የሚታይበት ሁኔታ ነበር።እናም ይህን ሕዝቡም አባላቱም ያነሱት ነበር። ይህን ያነሱ ብዙ አባላት ስደትና እስራት ደርሶባቸዋል።

የህወሓትን የበላይነት ተልእኮ ወደ ብአዴን ይዘው የሚመጡት ደግሞ እንደ አቶ በረከት ያሉት ነበሩ።አሁን ላይ ቆሜ ሳየው በዚህ መልኩ ብዙ ተልዕኮዎችን አስፈፅመዋል።

እንደሰማሁት የብአዴን አባላት እንዲሁም የሌሎች ፓርቲዎች አባላት በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የህወሓትን የበላይነት ጉዳይ አንስተው ተወያይተዋል።ይህ ጊዜው ሲፈቅድ የመጣና አከራካሪ ጉዳይ ነበር።ይህ ሕዝብ ያመጣው ለውጥ ከዚያ እውነታ የተነሳም ነው።

የህወሓት የበላይነት የለም ብሎ መደምደም አይቻልም።በተመሳሳይ ብአዴን ሙሉ በሙሉ ለህወሓት ተገዥ ነበር ማለትም አይቻልም። በጥቅሉ ግን አሁን የህወሓት የበላይነት ጉዳይ የፓርቲዎች ትልቅ የትግል አጀንዳ እንደሆነ ይሰማኛል።

ጥያቄ፦ ከዚህ ቀደም አሁን ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከታገዱት አቶ በረከት ስምኦን ጋር ስለተነካካችሁበት ነገር ተናግረው ነበር።እሳቸውም ሰሞኑን እርስዎን በግል ለማጥቃት ያደረጉት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።ይልቁንም የእርስዎ ምክትል የነበሩት አቶ ገብረዋህድ ገብረመድህን ‘ሰዎችን እያስለቀሰ ነው፤ አንድ ነገር አድርግ’ እንዳልዎ ነው እየገለፁ ያሉት።እዚህ ላይ የሚሉት ካለ?

አቶ መላኩ፡- ይህን ማለታቸውን አልሰማሁም፤ ግን ከባህሪያቸው አንፃር ቢሉም አይገርመኝም።የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም አባሉ ስለ መላኩ ጉዳይ ይገለፅልን፤ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተመረጠው ከሙስና የፀዳ ተብሎ ነው ሲላቸው፣ ‘ሙስና ውስጥ ገብቷል፣ መረጃ አለ፤’ እያሉ ሲያብራሩ የነበሩት እሳቸው ናቸው።ስለዚህ የአሁኑ እሱ ላይ አጀንዳ የለኝም ማለታቸው የማይመስል ነገር ነው።

ወደ ሙስና ገብቼ አጥፍቼም ከሆነ ማወቅ ያለበት ጉዳዩ ቀርቦ መገምገምም ያለብኝ፣ የፓርቲው ሊቀ መንበር ምክትሉም አውቀው መድረክ ላይ ነበር።ነገር ግን አብዛኛው የብአዴን አመራር ነገሩን የሰማው ከሚዲያ ነው።እሳቸው ግን የጀርባ ፈላጭ ቆራጭ ስለነበሩ ያኔ ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር።

የአቶ ገብረ ዋህድን ጉዳይ [በተመለከተ] እውነት ነው አንስተውልኛል፤ እሳቸውም ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የህወሓት አመራሮች [አንስተውልኛል]።እኔ ግን ጉዳዩ ላይ ተጨባጭ ማስረጃ ስላላገኘሁ ለሾመው አካል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቤያለሁ ብያቸዋለሁ።በድጋሚ ይህንኑ ጉዳይ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አንስተውብኝ ‘ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳወቅ የሚጠበቅብኝን አድርጌያለሁ’ ብዬ መልሼላቸዋለሁ።

ከአቶ ገብረዋህድ ጉዳይ ጋር አዳብለው ያነሱልኝን ጉዳዩች ግን ህሊናቸው ያውቃል።ለሚዲያ አካላት ማስታወቂያ በመስጠት ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ እንደ አቶ ከተማ ከበደ ያሉ ባለሐብቶችን፣እየሱስ ወርቅ ዛፉ፣የህብረት ባንክ ፕሬዝዳንት የነበሩትንና ሌሎችን ‘የታክስ ጉዳይ ፈልገህ እሰር’ ብለውኝ፣ ‘በታክስ ፈልጌ አላስርም’ ብያቸዋለሁኝ። ‘የኮሚኒኬሽን ኃላፊ እርስዎ ነዎት፤ ሚዲያ ሕግም አለዎት፤ ራስዎ የሚያደርጉትን ያድርጉ’ ብያቸዋለሁ።ይህን ያሉኝ የቀድሞ የደኅንነት ኃላፊውን ይዘው ነበር።

በወቅቱ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቤም ነበር። የባንክ ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ሌሎች ሌሎች ሰዎችንም በተደጋጋሚ እሰር ብለውኝ እምቢ ብያቸዋለሁ።

በተቃራኒው ታክስን ተፈፃሚ ላደርግ ስል ‘ይሄ እኮ ልማታዊ ባለሐብት ነው’ እያሉ ቢሮ ድረስ አስጠርተው አነጋግረውኛል።ይህንንም የብአዴን ሥራ አስፈፃሚ ሂስና ግለ ሂስ መድረክ ላይ አቅርቤያለሁ።

ጥያቄ፦ ወደ ፖለቲካ የመመለስ ሐሳብ አለዎት?

አቶ መላኩ፦ ትበሰብሳታለህ ተብዬ ነበር የገባሁት፤ እንድበሰብስ ተፈርዶብኝ የሄድኩ ሰው ነኝ። እስከዚህ ድረስ ነበር ነጻነታችንን አጥተን የነበረው። በአገሪቱ የመጣው ለውጥ ትልቅ ነው።በዚህ ውስጥ አገሬንና ሕዝቤን መርዳት እፈልጋለው። ግን ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ነው? ሌሎች መንገዶች አሉ? የሚለውን እያሰብኩ ነው።ለራሴም ጊዜ እየሰጠሁ ነው። ክብር ለሰጠኝ፣ ፍቅር ለሰጠኝ ሕዝብ የማገለግለበትን መንገድ ዐይቼ የምወስን ይሆናል።

ጥያቄ፦ ወደ ብአዴን መመለስን ያስባሉ ታዲያ? በዛሬው ብአዴን ውስጥ ራስዎን ሊያዩ አልሞከሩም?

አቶ መላኩ፦ወደ ፖለቲካ መመለስን በማይበት ጊዜ አንደኛው አማራጭ እሱ ስለሆነ አስበዋለው።

ጥያቄ፦ በአሁኑ ወቅት ከብአዴን አመራሮች ማለትም ከቀድሞ ጓዶችዎ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ነው ያለዎት?

አቶ መላኩ፦ተቋማዊ ባይሆንም ከብአዴን የቀድሞ አዲስ አመራሮች እንዲሁም ከአባላቱ ጋር በስልክም በአካልም እገናኛለሁ። እንደተፈታሁም ሁሉም በአካልም በስልክም እንኳን ደስ አለህ ብለውኛል። ‘ያንተ የለየለት መታሰር ቢሆንም ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት እኛም ታስረን ነበር።የከፈልከውን መሰዋዕትነት አንረሳም፤ ሥራ አስፈፃሚው ውስጥ እንዳለህ ነበር የምናስበው’ ብለውኛል።

ያለፈውን ትቼ ወደፊት እንድሄድ ምክርም ማበረታቻም ይሰጡኛል፤ እኔም ከማያቸው ከምሰማቸው ነገሮችም በመነሳት እንዲህ ቢሆን ባይሆን እያልኩ አስተያየቴን እሰጣቸዋለሁ፤ እንወያያለን።

Filed in: Amharic