>

በረከት ለፍርድ መቅረብ የሚገባው ሰው ነው  'ወ/ሮ አና ጎሜዝ

በረከት ለፍርድ መቅረብ የሚገባው ሰው ነው

 ‘ወ/ሮ አና ጎሜዝ

ጥያቄ፡- ሰሞኑን አቶ በረከትን ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸው ነበር። ‘ወ/ሮ አና፣ ‘እባክዎ አርፈው ይቀመጡ’ ብለዎታል፡፡ እንዲያውም እኚህ ሴት‹‹የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት አስተሳስብ አልለቀቃቸውም››፤ ሲሉ ነው አስተያየት የሰጡት።

ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ለእንዲህ ዓይነት የወረደ ሐሳብ መልስ መስጠት አልሻም ነበር። አገሬን መስደባቸው ግን ትክክል አይደለም። እኔን እና አገሬን ከቅኝ ግዛት ጋር ማያያዛቸውም አሳፋሪ ነው። በፖርቹጋል እኔ የምታወቀው በጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎዬ ነው። ያውም ቅኝ ግዛትን መጻረር ፈታኝ በሆነበት ዘመን ነው የምልህ። ሕይወቴንም አደጋ ላይ ጥዬ ነው ይሄን ያደረገኩት። ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ነው ይሄን ተጋድሎ የፈጸምኩት። ታሪኬ የሚያስረዳውም ይህንን ነው።

«ወይዘሮ ጎሜዝ፤ እርስዎ አያገባዎትም! አርፈው ይቀመጡ በልልኝ»

አቶ ታደሰ ካሳ፡ “…ወሎዬ ነኝ፤ መታወቂያዬም አማራ የሚል ነው”

ያለመከሰስ መብት ለማን? እስከምን ድረስ?

ጥያቄ፡- ሁለታችሁን እንዲህ የቃላት ጦርነት ውስጥ የሚከታችሁ እኛ የማናውቀው ነገር አለ?

አና ጎሜዝ፡- ነገሩ በ2005 እኔ የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢ ቡድንን መምራት በጀመርኩበት ጊዜ የሆነ ነው። እሱ ያኔ የመንግሥት ተወካይ ነበር። ከእኔና እኔ ከምመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጋር እሱ ነበር በየጊዜው የሚገናኘው። የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትርም ነበር። በዚያ የታዛቢ ቡድን አማካኝነት እኔና የቡድኔ አባላት የተደረገውን ማጭበርበር ስላጋለጥን ነው በእኔ ላይ ቂም ይዞ የቆየው።

ከበረከት ስምኦን ጋር በጁን 8፣ 2005 የነበረንን ንግግር መቼም አልረሳውም። በመሐል አዲስ አበባ የተደረገውን ግድያ ሰምቼና ሆስፒታሎችን ጎብኝቼ ወዲያውኑ አገኘሁት። የጎበኘኋቸው ሐኪሞችና ነርሶች እያለቀሱ ነበር [በጥይት የተመቱትን] የሚያክሙት፡፡ ሁኔታው አስቆጥቷቸው ነበር። ባየሁት ጉዳይ ላይ መግለጫ እንደምሰጥ በረከትን ነገርኩት። እርሱ በዚህ ውሳኔዬ ተበሳጨ፡፡ ይባስ ብሎ ለተፈጠረው ግድያ ተጠያቂው የአውሮፓ ኅብረት ነው አለኝ። ይህ ብሽቅ የኾነ ሐሳብ ነው።

ጥያቄ፡- በቀደም ለታ የትዊተር ገጽዎ አቶ በረከትን ‹‹ርህራሔ የሌለው፣ ዋሾና፣ ጨካኝ›› ብለውታል። አልበዛም? የተጠቀሟቸው ቃላቶች የዲፕሎማት ቋንቋ አይመስልም።

አና ጎሜዝ፦ እውነት ስለሆነ ነዋ፣ እውነት ስለሆነ ነው፥ እርሱ ጨካኝና ውሸታም ነው። በ2005 በደንብ አውቀዋለሁ ሰውዬውን። ባህሪው እንደዚያ ነው። እኔ ከአገሪቱ ጋር ምንም ችግር የለብኝም። የኔ ችግር ሁልጊዜም ከአምባገነኖች ጋር ነው።

ጥያቄ፡- አሁን ነገሩ ረዥም ጊዜ ሆነው እኮ፤ ለምን አይረሱትም ግን እርስዎ?

አና ጎሜዝ፡– ለምን እረሳለሁ?! በ2005ቱ ምርጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል። የነርሱ ቤተሰቦች ይህን የሚረሱ ይመስልኻል? ስለዚህ እኔም አልረሳም። የሰው ሕይወት ነው የጠፋው፤ ለግድያው ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ሰዎች አሉ፤ አንዱ አቶ በረከት ነው።

ይህን ጉዳይ የግለሰቦች ጉዳይ ለምን ታደርገዋለህ። እኔ በግል ከሰውየው ጋር ምንም ችግር የለብኝም እኮ። ፖለቲካዊ ነው ጉዳዩ። በርካታ ሰዎችን የጨፈጨፈውን ሥርዓት ሲያገለግል የነበረ ሰው ነው። እኔ ለማወቀውና ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ይሁን ነው እያልኩ ያለሁት። ብቸኛው ተጠያቂ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ሆኖም አንዱና ዋንኛው ነው።

ጥያቄ፡- ለማለት የፈለኩት ከእርስዎ ጋር ምርጫውን የታዘቡ፣ የኾነውን የተመለከቱ ብዙ ዲፕሎማቶች ነበሩ፤ አንዳቸውም በእርስዎ መጠን መንግሥት ላይ ትችት ሲሰነዝሩ አልሰማንም። እርስዎ ለምንድነው አንዲህ ነገሩን ለዓመታት የሙጥኝ ያሉት?

አና ጎሜዝ፡– ዲፕሎማቶች የተፈጠሩት እንዲዋሹ አይመስለኝም። ዝም አልልም፤ ለምን ዝም እላለሁ፤ በመለስና በአቶ በረከት ትእዛዝ የተገደሉ ሰዎችን አይቻለሁ፤ ስለምን ዝም እላለሁ? አሁንም ላረጋግጥልህ የምፈልገው፤ አሁንም ወደፊትም ዝም አልልም።

ሌሎች ዝም ብለዋል ላልከው እኔ ያኔም ያስተጋባሁት የ200 የቡድኔን አባላት በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ያዩትን ነው። ያወጣነው ሪፖርት ደግሞ ከካርተር ሴንተር ካወጣው ሪፖርት ጋር የሚመሳሰል ነው። ነገር ግን ሁሉም ሰው ለአንድ ጉዳይ የሚሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። እኔ ባየሁት ነገር እጅግ ተቆጥቻለሁ። የመለስና የበረከት መንግሥት የሕዝብን ድምጽ ያጭበረበረበት መንገድ አናዶኛል። የአውሮፓ አገራት ይህንን መንግሥት እሹሩሩ ያሉበት መንገድ አበሳጭቶኛል።

አሁንም ዝም አልልም፤ ወደፊትም ዝም አልልም፤ በእጃቸው የሰው ደም ያለባቸውን እንደ አቶ በረከት ያሉ ሰዎችን በዝምታ አላልፋቸውም።

Filed in: Amharic