>

ትግራይን አየኋት!!! (ቢንያም ዘ ጨርቆስ)

ትግራይን አየኋት!!!!
ቢንያም ዘ ጨርቆስ
* እስከዛሬ ኢትዮጵያ ስትነድ፣ ስትፈርስ ዝም በማለቷ የምንገበገብባትን ትግራይን አየኋት። አየኋት ስለኢትዮጵያ ስታነባ፣ አየኋት ስለ ሀገሬ ደረቷን ስትደቃ። በጅግጅጋ ለታረዱ ካህናትና ምዕመናን ስታነባ አየኋት። በሻሸመኔ ተዘቅዝቆ ስለተሰቀለው፣ በደቡብ በቁማቸው በቤንዚን ተቃጥለው ስለሞቱት ሲያነቡ አየኋቸው።  
 የመቐለ የአቡነ ተክለሃይማኖት የዕረፍት በዓል አከባበር በተለየ መልኩ #በለቅሶና በምስጋና ነበር የተከበረው። ማኅሌቱና ውዳሴው እንዲሁም ወረቡ የደስታችን ምንጮች ነበሩ። ታላቁ ሊቅ ሊቀሊቃውንት ያሬድ ካሳ ስለ ተክልዬ ጽድቅና አገልጋይነት ከሕይወታችን ጋር እያስተሳሰሩ ሲያስተምሩ ሳለ ድንገት የጅግጅጋው የካህናት መጨፍጭፍ አንስተው ትምህርቱን አቁመው የእናታቸው ልጅ እንደሞተባቸው ዕንባ ተናነቃቸው! “ህ! ህ! ህ!” ብለውም አለቀሱ።
የቤተመቅደሱ መቃጠል፣ የካህናቱ መታረድ አንገብግቧቸው ከንፈራቸው ተንቀጠቀጠ። ያ ሁሉ ሕዝብም ዕንባውን መያዝ አልቻለም። በግፍ ስለሞቱት ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድ ቃል እዬዬ ብሎ አለቀሰ! በዘር ቢለያይ ኢትዮጵያዊነት ላስተሳሰረው ወገኑ የሚያለቅስ ይህ ሕዝብ ታላቅ ነው።
በዚህ ብቻ አልበቃም። ትምህርቱ አልቆ ለጸሎትና ቡራኬ ብጹዕ አባታችን አቡነ ኢሳይያስ ቀረቡ። እሳቸውም በቃለ ምዕዳናቸው ከተለያዩ ክልሎች ተሰደው የመጡትን እንድንረዳቸው። ዘመኑ ክፉ ነውና ስለ አንዲቱ ኢትዮጵያ እንድንጸልይ ከመከሩን በኋላ፣ በዚህ ዘመን ሰው በአደባባይ የተሰቀለባት አገር እንደሆነች በሐዘን ሲገልፁ ግን … አልቻሉም። አንገታቸውን ደፍተው አለቀሱ። ስለታረዱት ካህናት፣ በምሕረት ደጃፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ አውሬ ተጨፍጭፎ ስለተገደለው ምስኪን ሰው ለመናገር ቢሞክሩም እንዴት ይጨርሱት? ሰፈሩን ሁሉ በሚያናውጥ  ሞንታርቮ እዬዬያቸው ተሰማ። አጠገባችን የነበሩት እናቶች ጨርቃቸውን መጣል እስኪቀራቸው ድረስ ለአንድ ልጃቸው የሚያለቅሱ ያክል ስለማያውቁት ወገናቸው አለቀሱ። ማን ማንን ያፅናና? ሁሉም በዕንባ ታጥቧል።
ያኔ አባታችን ለቅሶውን በግድ ገትተው፣ ምኅላ ለመጀመር “እግዚኦ…” ብለው ሲጀምሩም ድጋሜ በለቅሶ አፋቸው ተያዘ። ሲቃቸው ሕዝቡ መሃል ገብቶ ምህላው ላይ ዕንባን ጨመረበት። የተለቀሰው ስለ አንድ የመቀሌ ልጅ ወይ ስለ አንድ ትግራዋይ አልነበረም። ብሔራቸው ለማናቀው የጅጅጋ ካህናት፣ በቋንቋ ለማይመስለን በግፍ ለተሰቀለው ወንድም፣ በዘር ለማይገናኘን በቤተ ክርስቲያን ለተጨፈጨው ኢትዮጵያዊው ወገናችን እንጂ። ሕዝቡ ታላቅ ነው ስልህ።
Filed in: Amharic