>
5:13 pm - Monday April 19, 7300

ክብር በየተሰማሩበት ዘርፍ ሃገራችንን ከፍ ላደረጉ ጀግኖች!!!

ክብር በየተሰማሩበት ዘርፍ ሃገራችንን ከፍ ላደረጉ ጀግኖች!!!

እምዬ ምኒሊክ 

“… “የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም :: የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም ::”
(ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ-ወልድ )
* “እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነት የምታወጧት ከሆነ ድርጊታችሁን እንደ ታላቅ በረከት በጸጋ እንቀበላለን”
ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም አድርገው ለገዳዮቻቸው የደርግ ወታደሮች የተናገሩት፤
ኤርትራን፣ አፋምቦን፣ ጋምቤላን ኦጋዴንንና ሌሎች የኢትዮጵያ ቀደምት ግዛቶች በበሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ እናት አገራቸው የመለሱ፤ ኢትዮጵያ አስተምሬ አብቅቻቸዋለሁ ብላ በደማቅ ቀለም ታሪካቸውን የምትጽፍላቸው በፍጻሜያቸው ግን የምታነባላቸው፤ የአገር ባለዉለታ ናቸዉ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ።
በመጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ/ም ነበር አክሊሉ ከአባታቸው የእንጦጦው ራጉኤል ቤተክርስትያን ሙሉ ደብተራ ከነበሩት ከአለቃ ሀብተወልድ እና ከእናታቸው ከእመት ያደግድጉ በደብረዘይት ከተማ የተወለዱት።
የአክሊሉ ሀብተወልድ እናት እመት ያደግድጉ ልጃቸው በመንፈሳዊው ትምህርት እንዲዘልቅ ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በታላቅ ወንድማቸው በአቶ መኮንን ገፋፊነት አክሊሉ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው የቀለም ትምህርታቸውን ሲማሩ  ከተከታተሉ በኋላ በ ፲፱፻፲፯ ዓ/ም ወደ እስክንድርያ ትምሕርታቸውን እዚያ በሚገኘው የ ፈረንሳይ “ሊሴ” ትምህርት ቤት እንዲቀጥሉ በ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ተላኩ። እስክንድርያም እስከ ፲፱፻፳፫ ዓ/ም ከተማሩ በኋላ የሊሴ ትምሕርታቸውን አጠናቀው ለከፍተኛ ትምሕርት ወደ ፓሪስ እና ታዋቂው ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ አምርተው የከፍተኛ የንግድ ሕግ እና ሽከታኪን (political science)  ትምሕርት ጀመሩ። ሶርቦን እስከ ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ድረስ ተምረው የመጀመሪያ ሲማክቶ ጉላፕ (BA degree ) በሸከታኪን እንዲሁም የ ሲማሕግ ጉላፕ (bachelors degree in law) ተመርቀው ወጡ። ወዲያው
ፋሽሽት ኢጣልያ ሀገራችንን ይወርና ወጣቱ አክሊሉ ሀብተወልድ ለውድ አገራቸው ነጻነት የአርበኝነት ትግላቸውን በቶፍካ (diplomacy)  እና በገቢ ሰብሳቢነት እዚያው ፈረንሳይ አገር ተሰማሩ።
አክሊሉ ሀብተወልድ ገና በሃያዎቹ እድሜ መጀመሪያ ሳለ በፈረንሳይ ሃገር ለስልጣን ይሟገቱ ከነበሩ ፓርቲዎች ዘንድ በታዛቢነት እየተገኘ ጸረ ፋሽስት የሆኑትን ፓርቲዎች ይደግፍ የፋሽስት ፓርቲነት ዝንባሌ ያላቸውንም ይሟገት ነበር:: ከዳግም ኢጣሊያ  ወረራ በኋላ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በስደት ባሉበት እንግሊዝ  እዚያው ካሉ ወዳጆቹ ጋር በመተባበር ኒውስ ኦፍ ኢትዮፕያ” የተሰኘ ጋዜጣ እያሳተመና መላው ሃገር ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተቻለ መጠን እንዲረዳ ይታገል ጀመር:: በዚህ በሳልነታቸው  ንጉሠ ነገሥቱ ስለሃገራቸው መወረር ለሚያደርጉት ሙግት በሊግ ኦፍ ኔሽን የፊትአውራሪ ተክለሃዋርያት ዋና ጸሃፊ አድርገው ሾሟቸው::
አክሊሉ በዚህ ሹመታቸው ወቅት “የላቫል ሆየት ፓክት” የተሰኘውንና ኢትዮጵያን እንደ ሶማሊያ በታትኖ የሚያስቀር ስምምነት ማክሸፋቸው ታላቅ ጀብድ ነበር:: የዚህ ስምምነት ፍሬ ነገር የመሃል ሃገሩን ከዳር ሃገር በመክፈል ለጣልያን ለመስጠት ያቀደ ነበር::ሆኖም ግን ይሄንን የውል ረቂቅ አክሊሉ ከወዳጆቻቸው ጋር በመተባበርና በሬዲዮ ሴራው እንዲለቀቅ በማድረግ የውል ስምምነቱ እንዳይጸድቅ አርገዋል::
ይሄንን እና ሌሎች ስራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩት አክሊሉ ሀብተወልድ በቀዳማዊ  ኃይለሥላሴ የኤርትራን ጉዳይ ከዳር እንዲያደርሱ ከፍ ያለ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው ብዙ ዓመት ከፈጀ ክርክር እና የሰላ የዲፕሎማሲ ጥረት በኋላ ኤርትራን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር ሊቀላቅሏት ችለዋል::ከዚህ በተጨማሪም የጋምቤላን የአፋምቦንና የኦጋዴን ግዛቶችን አስመልሰዋል።
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ በጣልያን ወረራ ጊዜ አምስቱን ዓመት ሙሉ በ ፓሪስ የ ኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጻሚ፤ በዠኔቭ በዓለም መንግሥታት ማኅበር የ ኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ፤  ከድል በኋላም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እና እስከ አብዮት ፍንዳታ ድረስም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።
በመጨረሻም በዘመነ ደርግ ህዳር 14 ምሽት ላይ ከወንድማቸው ከአካለወርቅ ሀብተወልድ ጋር ከሌሎች ሃምሳ ስምንት ሹማምንትን ጨምሮ በመትረየስ ጥይት ተረሽነዋል።
ሀገርና ትውልድ ቆይቶም ቢሆን የእነ አክሊሉ ሀብተወልድን መልካም ስራ ሲያዘክር ይኖራል::
.
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በዲፕሎማሲዉ መስክ ለአገራችን ባደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እጅግ እናመሠግናለን።

 

Filed in: Amharic