>

የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ጉብኝት፣ የአብን ክህደትና የወያኔ ታላቅ ድል!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ጉብኝት፣ የአብን ክህደትና የወያኔ ታላቅ ድል!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ (House resolution)128 እንዲጸድቅ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ክርስቶፎር ኤች ስሚዝ ያሉበት የአሜሪካ መንግሥት የልዑካን ቡድን በHR 128 የውሳኔ ሐሳብ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ ለመወሰን ለአሰሳ ቅኝት መጥቶ ከአገዛዙ አካላት በተጨማሪ “በቂ የቅኝት ጭብጥ ያስይዙኛል!” ብሎ ከገመታቸውና ከመረጣቸው ከአማራ እና ከኦሮሞ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመብት ተሟጋቾች ጋር ተገናኝቶና ተወያይቶ ትናንት ማምሻውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡
የልዑካን ቡድኑ ከነኝህ አካላት ጋር ምን እንደተወያየና ከነእርሱ ምን እንደተረዳ፣ ለውሳኔ የሚረዳውን ምን ሐሳብ እንዳገኘ ከልዑካን ቡድኑ መረጃ ማግኘት ባይቻልም የልዑካን ቡድኑ ከሰጠው ጠቅለል ያለ መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው ከአማራ እና ከኦሮሞ ድርጅቶች የተሰጣቸው መረጃ አገዛዙን ተጠቃሚ የሚያደርግ ምስክርነት እንደነበረ መረዳት ይቻላል፡፡
በእርግጥ ኦሮሞን ይወክላሉ ተብለው ከልዑካን ቡድኑ ጋር ከተወያዩ አካላት ይሄንን አሁን ያለውን የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ የለውጥ አራማጅ አድርገው ለልዑካን ቡድኑ መረጃ ቢሰጡ አይደንቀኝም፡፡ ምክንያቱም ከጠባብ ጎሰኛ ዓላማና ግባቸው የተነሣ የጎሳ ፌደራሊዝምን (የራስገዛዊነትን) ሙጥኝ ከማለታቸው ጋር በተያያዘ በወያኔ/ኢሕአዴግ ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚያስቡና ቀረን የሚሉትንም በዐቢይ ዘመን እንደሚያገኙ በጽኑ ያምናሉና ይሄ እንዲቀለበስ ስለማይፈልጉ ነው፡፡
አማራን ይወክላሉ ተብለው የቀረቡት ብን ያድርገውና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ነኝ የሚለው ፀረ አማራ ቁ. 2 ብአዴን ግን ዐቢይ “በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ጥቃት አልተፈጸመም!” ብሎ ወያኔ በረሃ እያለ ጀምሮ ሥልጣን ከጨበጠም በኋላ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ በመጠቀም በተጠናከረና በሰፋ መልኩ በስውርና በግልጽ በአማራ ሕዝብ ላይ ለ27 ዓመታት የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ጥቃትና የፍዳ የአሳር ዘመናችንን ሸምጥጦ ለካደው ለዚህ ወያኔ እና ኦነግ ሆኖ በሁለት ቢላ ለሚበላ አረመኔ ዐቢይ ወይም ለአሥተዳደሩ አዎንታዊ ምሥክርነት መስጠቱና የልዑካን ቡድኑ የዐቢይ አሥተዳደር ወይም አዲሱ የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ “በአማራ ሕዝብ አመኔታና ተቀባይነት ያለው ነው!” ብሎ እንዲያስብ ወይም እንዲያምን ወይም የተሳሳተ ግንዛቤና ድምዳሜ እንዲይዝ ማድረጉ ነው እጅግ አሳዛኙ ነገር፡፡
ወገን ወይም የአማራ ሕዝብ “አብን የሚባል የራሴ ተወካይ አገኘሁ!” ብሎ ደስታ ሊሞት ነው ተወካይ የተባለው ብአዴን ለስለላና ለማጃጃል የመሠረተው አብን ተብየው ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ አሳር ፍዳና መከራ ላዘነበው አሁን ጭንብል አጥልቆ በሌላ መልክ ለመጣው የወያኔ/ኢሕአዴግ መልካም ምሥክርነት ሰጥቶ አገዛዙ ከገጠመው ፈተና እንዲያመልጥ በመርዳት ወይም በአማራ ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት በመፈጸም የአማራን ሕዝብ በማጅራቱ ያርዳል፡፡
ዐቢይ “በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተፈጸመም!” ብሎ በአማራ ሕዝብ ላይ ነውረኛ አሳፋሪና ዓይን ያወጣ ታላቅ የዕብለት ክህደቱን ሲናገር አብን ተብየው መግለጫ አውጥቶ ያልተቃወመው ሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን በሕቡዕ ለብአዴን የሚሠራ ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡
ብአዴን ካድሬዎቹን ሰብስቦ አብንን ያቋቋመው ለሁለት ዐበይት ምክንያት ነው፦
1ኛው. የአማራ ሕዝብ እዚህ ሀገር ውስጥ የራሱን የሚወክለውን ትክክለኛ የአማራ ድርጅት ተጠምቶ “የወኪል ያለህ!” እያለ ለልጆቹ በመጮህ ሲጣራ ስለነበረና ይሄ የአማራ ሕዝብ እየጠራው ያለው ድርጅት በልጆቹ ተፈጥሮ ወይም ተመሥርቶ የሕዝቡ መከታ ከመሆኑ በፊት ለመቅደምና የአማራን ሕዝብ እራሳቸው ከጀርባ ሆነው ባቋቋሙለት ድርጅት ለመያዝ፣ እየደለሉ ለማጃጃል፣ ለማጭበርበር፣ ለማወናበድ ሲሆን፡፡
2ኛው. ደግሞ “”ከአማራ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ለማንነታቸው ነፍሳቸውን እስከመስጠት የቆረጡ ቆራጥ ወጣቶች ባጠቃላይ ከአማራ ልኂቃን እነማን ናቸው “የምናምነውን የራሳችንን የአማራ ድርጅት አገኘን ተቋቋመልን!” ብለው ለአማራነታቸው፣ ለማንነታቸው በመቆርቆር በመቆጨት፣ በአማራ ላይ ተለፈጸመው ግፍ ፍትሕ ሲሉ ወያኔ/ኢሕአዴግን ለመታገል ለመፋለም በስውር ወይም በድብቅ ድርጅቱን ለመርዳት፣ ከድርጅቱ ጎን ለመሰለፍ የሚንቀሳቀሱ?”” የሚለውን እየሰለለ መረጃ ለብአዴን እንዲያቀርብ ነው፡፡ ወገን ሆይ! ከፍተኛና አደገኛ ቁማር ነው እየተቆመረብህ ያለው፡፡
ምኞታችን የራሳችን ድርጅት የማግኘት የጋለ ፍላጎታችን ጋረደብንና እንዳናስተውል አደረገን እንጅ አብንን የመሠረቱት ከ90% በላይ የሚሆኑት የብአዴን ካድሬዎች መሆናቸው ብቻ ይህ ድርጅት የብአዴን መሆኑን ለመረዳት በቂ መረጃ ነበረ፡፡ ወገን ሆይ እንጠንቀቅ!!! ዋጋ መክፈላችን ካልቀረ በዚህ መልኩ ተቂለን ወይም እንደተቄልን እየጠረጠርን ሳይሆን ሙሉ እምነት ለምንጥልበትና ከንክኪ ነጻ ለሆነ የራስህ ድርጅት ቢሆን መልካም ነው፡፡ ፈተናውና መሰናክሉ በዝቶ አዘገየው እንጅ እየመጣልህ ነው እሱን ጠብቅ፡፡
አብን ለዐቢይ አሥተዳደርና “ተለውጧል!” ለሚለው ብአዴን በሌላ አነጋገር ለወያኔ/ኢሕአዴግ አጋር መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ አብን በአማራ ሕዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ ፍዳና መከራ ላደረሰ ወንጀለኛ ድርጅት (ወያኔ/ኢሕአዴግ) አጋር ሆኖ አልቆለት የነበረውን አንባገነን የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ በሌላ ጭምብል ሌላ የአገዛዝ ዘመን እንዲያገኝ በርትቶ እየሠራ እያለ በአማራ ሕዝብ ደምና እንባ እጃቸው የተነከረ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ተራ ነፍሰበላ ታጋይ ወንጀለኞች ድረስ ፍርዳቸውን እንዲያገኙ በማድረግ የአማራ ሕዝብ ደም መላሽ እንባ አባሽ ሲሆን ይታያቹህ!!! ኧረ እባክህን አትጃጃል ወገኔ???
የልዑካን ቡድኑ መሪ ክሪስ ስሚዝ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል “ኢትዮጵያዊያን ዓለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ መንግሥታዊ ሥርዓት ይገባቸዋል የሚል እምነት አለን አሁን ይሄንን የመንግሥት ሥርዓት ያገኙ ይመስለኛል! ይሄንን ከተረዳንባቸው መንገዶች….. የሀገር ውስጡ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭ ያለውም ተቃዋሚ ተቀይሯል!” ነበር ያሉት፡፡
H.R. 128 እዚህ ላይ አከተመለት፡፡ ወያኔም በአስደናቂ ትጋትና ሴራ ይሄንን ያህል የተረባረበው ለዚህ ነበረ ዘመቻውንም በድል አጠናቋል፡፡ ለዚህ ሽንፈታችንም “ተደምሬያለሁ!” እያለ ሲንገላጀጅ የነበረው ምሁር ነኝ፣ ፖለቲከኛ (እምነተ አስተዳደራዊ) ነኝ፣ የመብት ተሟጋች ነኝ፣ ነጻ ዘጋቢ (ጋዜጠኛ) ነኝ፣ ጸሐፊ ነኝ፣ ስሉጥ (አክቲቪስት) ነኝ፣ የሚሉ ምድረ ነፈዝ ዘገምተኛና ደናቁርት ሁሉ ተጠያቂ ናቸው፡፡
ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ የለውጥ አሥተዳደር የተባለው የውሸቱ የዐቢይ አሥተዳደር ምን ያህል የማስፈጸም አቅም የሌለው አቅመቢስ ሽባ መሆኑን፣ ሕዝብን ለመደለል “ተጠያቂ አደርጋቸዋለሁ!” ያላቸውን የወያኔ ባለሥልጣናትን ሕግ ፊት ለማቅረብ ጉልበት አቅም ተደማጭነት የሌለው መሆኑን፣ እንኳን ሌላ ቀርቶ የራሱ ጠ/ሚ ተብየው ደኅንነትም በአሥጊ ሁኔታ ላይ ያለ እንደሆነ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከራሳቸው በሚለቀቁ መረጃዎች እንድንገነዘብ መደረጉን፣ በሕዝብ ላይ ለተፈጸመው የፈንጅ ጥቃት፣ ግጭትና ቀውስ ተጠያቂ የሆኑ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በነጻ እንዲለቀቁ መደረጉ፣ የኢ/ር ስመኘው ጉዳይ ተዳፍኖ እንዲቀር መደረጉ እነኝህና ሌሎች ጉዳዮች የሚያረጋግጡት ሐቅ ባጠቃላይ ይህ የዐቢይ አሥተዳደር የሚባለው በዚህ አቅሙ የትም መድረስ የማይችል፣ ፈጽሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ የማይችል አሥተዳደር መሆኑን ነው፡፡
ተጨባጩ ሐቅ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ዐቢይ ነጻ ቢሆን ወይም የወያኔ ድራማ (ትውንተ ሁነት) መሪ ተዋናይ ባይሆን ለልዑካን ቡድኑ ወያኔ ሊያሠራው እንዳልቻለ፣ ከአቅሙ በላይ እንደሆነና እንደማይችላቸው በዚህም ምክንያት የዲሞክራታይዜሽኑ ፕሮሰስ (መስፍነ ሕዝብን የማረጋገጡ ሒደት) ሊሻገረው የማይችለው ደንቀራ እንዳለበት ለልዑካን ቡድኑ በግለጥ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲተባበሩትና ነገሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ይጠይቃቸው ነበረ እንጅ የቸገረው ነገር እንደሌለ፣ ሀገር ሰላም እንደሆነ፣ ሁሉም ነገር በቁጥጥሩ ስር እንዳለ አድርጎ ለልዑካን ቡድኑ በመወሽከት የልዑካን ቡድኑ “በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመሥርቷል!” እስኪሉ ድረስ የሌለ ቅዠት እንዲናገሩ እጅግ የተሳሳተ ግንዛቤ በማስያዝ፣ የHR 128 የውሳኔ ሐሳብ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ በማድረግ ቀሪ እንዲሆን ማግባባት ምን ማለት ነው የሚመስላቹህ ተደማሪ ነኝ የምትል ምድረ ደናቁርት ሁሉ???
ዐቢይ እውነተኛ የለውጥ ሰው ቢሆን HR 128 የውሳኔ ሐሳቡ ቶሎ ጸድቆ እነኝህ ከሕግ በላይ ሆነው ሀገር እያወኩ፣ ተጠያቂ እንዳይሆኑ እየበጠበጡ፣ የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነትንና ህልውናን አደጋ ላይ የጣሉ የወያኔ ግፈኛ ባለሥልጣናት እንዲቀፈደዱ፣ በውጭ ሀገራት ባንኮች (ቤተንዋዮች) ያከማቹት የተዘረፈ የሕዝብ ሀብት እንዲያዝባቸው የውሳኔ ሐሳቡ እንዲጸድቅ ግፊት ያደርግ ነበር እንጅ የዳያስፖራውን (በግዩራኑን) እና የሀገር ውስጡን የተለያየ የፖለቲካ ኃይል እየደለለ HR 128 የውሳኔ ሐሳቡ ወደ ሴኔቱ (የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ) እንዳይቀርብና በሴኔቱም እንዳይጸድቅ ጥረት ያደርግ ነበረ ወይ ምድረ ነፈዝ ሁላ???
ከዚህ ከዚህ የምንረዳው ይሄ ሁሉ ነገር የወያኔ ድራማ (ትውንተ ሁነት) መሆኑን፣ ዐቢይ የድራማው መሪ ተዋናይ መሆኑን፣ ወያኔ “የለውጥ ኃይል እንቅስቃሴ!” ብሎ ለአራት ወራት ሲተውንብን የከረመው ድራማ HR 128 የውሳኔ ሐሳብ ሴኔቱ ላይ ቀርቦ ሕግ ሆኖ እንዳይጸድቅና የወያኔ ባለሥልጣናት እንዳይቀፈደዱ፣ በውጭ ባንኮች (ቤተንዋዮች) ያከማቹት የሕዝብ ገንዘብ እንዳይያዝባቸው ለመከላከል በከፍተኛ ብቃት የተደረሰና የተተወነ ትውንተ ሁነት መሆኑን ነው፡፡
በመጨረሻም ወያኔ እራሱን አትርፏል!!! መቀመቅ ሊያወርደው የነበረውን ፈተና ምድረ አህያውን፣ ነፈዙን፣ ደንቆሮውን፣ ዘገምተኛውን፣ ሆዳሙን…. ሁሉ ይዞ በመዝመት ሊያልፈው ሊሻገረው ችሏል፡፡ ሌላ የ27 ዓመት የፍዳ ዘመንም ይጠብቀናል፡፡ እያንዳንድሽ የዚህን ውጤት ሩቅ ባልሆነ ጊዜ የምታገኛት ይሆናል ጠብቂ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic