>
5:13 pm - Tuesday April 18, 6293

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመንበራቸው በግፍ ተነስተው ወደ ስደት የተገፉበት ታሪካዊ ክንውን!!! (ከመልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ውቤ)

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመንበራቸው በግፍ ተነስተው ወደ ስደት የተገፉበት ታሪካዊ ክንውን!!!
 
ከመልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ውቤ
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጷዻዻሳት ዘኢትዮዽያ ለስደት መዳረግ አውነተኛው ታሪክ ይህን ይመስላል። በመጨረሻው ቀን ከእውነት ምስክርነት የበለጠ የሚያድን ሌላ መንገድ የለም።
ታሪክ እንደሚያስረዳው ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከፈተና ነጻ የሆኑበት ጊዜ ባይኖርም በዚህ ዘመን የደረሰው ፈተና ሲታሰብና ሲመረመር ግን ከዚህ በፊት ያልታየና ያልተሰማ ለወደፊትም ይደርሳል ተብሎ የማይገመት አሳፋሪ የታሪክ ጠባሳ ሁኖ ተገኝቷል ። ይህን ፈተና ልዩ የሚያደርገውም በራሷ በኢትዮጵያ ልጆች መፈጸሙ ነው ። ለጊዜው የሀገራችንን ጉዳይ ለታሪክ እንተወውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ወቅታዊ ችግር ብቻ ባጭሩ ለማስታወስ እንሞክር ።
እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ ለ17 ዓመታት የነበረው አስከፊ የርስ በርስ ጦርነት መጠነ ሰፊ የሆነ ችግር የፈጠረ ቢሆንም ፥ በተለይ ወደ መጨረሻው አካባቢ በተደረገው ከባድ ጦርነት በኤርትራ ፥ በትግራይ ፥ በጎንደር ፥ በወሎና በሰሜን ሸዋ ክፍላተ ሀገር ብቻ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ከነቅርሶቻቸው መውደማቸውን ፣ የአገልጋይ ካህናት ሕይወት መጥፋቱን በተመለከተ ኢሕአዴግ መላ ሀገሯን ከመቈጣጠሩ በፊት በተደረገው አጠቃላይ የመንበረ ፓትርያርክ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት በቅዱስነታቸው የሚመራው ጉባኤ በሰፊው ከመከረበት በኋላ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ግቢና በዙሪያቸው ከባድ የጦር መሣሪያ እያጠመዱ ለብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፍና ለአብያተ ክርስቲያናቱ ውድመት ምክንያት የሆኑት ወያኔዎች መሆናቸው ስለ ታመነበት ፥ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ አወገዛቸው ውግዘቱም በመገናኛ ብዙኃን ተነገረ  በልዩ ልዩ ጋዘጦች ላይም ወጣ ። በዚህም ምክንያት ወያኔ ከበርሀ ጀምሮ ቅዱስ ፓትርያርኩን እያወገዘና እየኮነነ ፣ በቤተክርስቲያኗ ላይም ጥላቻውን እየጨመረ መጣ ። ኢሕአዴግ አዲስ አበባ እንደ ገባ ቤተ ክርስቲያኗን በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ መሥራት ጀመረ። ካለፉት መንግሥታት ድክመት በደንብ ጥናት ያደረገው ኢሕአዴግ ፥ በጳጳሳቱ መካከል ሰርስሮ በመግባት አንድ የነበሩትን አባቶች ከፋፈላቸው ።
በበርሀ ሳለ የደርግ ጳጳሳት እያለ ሁሉንም አባቶች በጅምላ ያወግዝ የነበረው አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ግን ጥላቻውን በፓትርያርኩ ላይ ብቻ አነጣጠረ ። ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋርም አብሮ እንደማይሠራ ከዚህ በታች በተገለጹት ባለሥልጣናት አማካይነት በተደጋጋሚ ገለጸ ።
1ኛ/ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ እንደ ገባ አቶ ኤፍሬም የሚባሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ መጥተው መንግሥት ከርሳቸው ጋር እንደማይሠራ ገልጸው ፥ ነገር ግን ቻርተሩ ሲጸድቅ የቤተ ክርስቲያኗ ተወካይ መገኘት እንዳለበት መመሪያ ዓይነት ትእዛዝ ሰጥተው ሄዱ ።
2ኛ/ አቶ ክንፈ ገብረ መድኅን የተባሉ የደኅንነት ኃላፊ ለብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ፣
3ኛ አቶ ታምራት ላይኔ የሽግግር መንግሥቱ ጠ/ሚንስትር 19 ለሚሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ፣
4ኛ/ አቶ አባይ ፀሐይዬ ልዩ ጽ/ቤት ስልክ ደውለው ለልዩ ጸሐፊው ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፣
5ኛ/ ኃየሎም የተባሉ የጦር ሰው በነዶክተር ማርቆስ ወ/ኢየሱስ አማካይነት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞችን ሰብስበው የመንግሥትን አቋም አሳውቀዋል። አምስቱም ባለሥልጣኖች መንግሥት ከፓትርያርኩ ጋር ፈጽሞ አብሮ እንደማይሠራና መወገድ እንዳለባቸው በግልጽ ተናግረዋል ።
በመቀጠልም በጡረታ ተገልለው በነበሩት በቄስ ሀብተ ማርያም ተድላ ሰብሳቢነት ጭቁን ካህናት በሚል ስያሜ መፈንቅለ ፓትርያርክ የሚያደርግ የካህናት ቡድን እንዲቋቋም ተደረገ ። በዶክተር ማርቆስ ወልደ ኢየሱስ ፥ በመምሬ ፍስሐ ተበጀና በቄስ ዳኛቸው ካሳሁን ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም የተጻፈ ፓትርያርኩን የሚከስ የሀሰትና የውንጀላ ደብዳቤ ለኢሕዴግ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቀርብ ሆነ ።
ቅ/ፓትርያርኩን ከመንበራቸው ጎትተው የሚያወርዱ ከ30 የማይበልጡ ጥቂት ሰዎች ጸጥ ሲል ቅዳሜ ቀን ከሰዓት በኋላ በታጠቁ ወታደሮች ታጅበው ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ መኖሪያ ቤት መጡ ። እኛም ሁኔታውን አስቀድመን ሰምተን ስለ ነበር በሮቹን ቆልፈን ስንጠባበቅ ፥ በቀላሉ መግባት እንደማይችሉ ሲረዱ የተቀደሰውን መንበረ ፓትርያርክ በከባድ መሣሪያ ደፍረው ፣ በርግማንና በጩኸት ግቢውን አርክሰው ተመለሱ ። የገንዘብ ጉድለት እናገኛለን ከሚል አስተሳሰብ በመነሣትም ከመንግሥት በመጡ የሒሣብ መርማሪዎች አማካይነት ከወር በላይ የፈጀ ከባድ የምርመራ ሥራ ተካሄደ ። ኢሕአዴግ በጥቅም ገዝቶ ባደራጃቸው በነ ቄስ ሀብተ ማርያም ተድላ አማካይነት ጥቂት ሰዎች ሰልፍ እየወጡ ቅ/ፓትርያርኩን እንዲራገሙና እንዲሳደቡ ተደረገ ።
 በሌላ በኩል ደግሞ ፥ ቅዱስ ፓትርያርኩን የሚደግፉ ሰልፎችና ስብሰባዎች ይካሄዱ ጀመር ።
ሀ/ በባሕታዊ አምኃ ኢየሱስ የተመራ ቅዱስ ፓትርያርኩን የሚደግፍ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ ፣ የመንግሥትም ጣልቃ ገብነት በብርቱ ተወገዘ ። እጁንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንዲያነሣ ተጠየቀ ።
ለ/ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስትዳዳሪዎች በቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተሰብስበው ለቅዱስ ፓትርያርኩ ድጋፋቸውን ገለጹ ፣ የመንግሥትንም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በጽኑዕ ተቃወሙ ።
ሐ/ በወቅቱ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ ቤት ዲን በነበሩት በአሁኑ ሰዓት የሕጋዊው ቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የተዘጋጀ ጽሑፍ በአዲስ አበባ ከተማ ተበተነ ። የጽሑፉም ዓላማ እየተሠራ ያለው ሁሉ ሕገ ወጥ እንደ ሆነና ፓትርያርኩ ወደ መንበራቸው በአስቸኳይ መመለስ እንዳለባቸው የሚገልጽና ድርጊቱን በጽኑ የሚያወግዝ ነበር።
መ/ በጎንደር ርእሰ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ ከ30 በላይ ከሚሆኑ አድባራትና ገዳማት ተወክለው የመጡ 156 የአድባራትና የገዳማት አለቆች ፣ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ተመራጮች ፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በተገኙበት ሰኔ 22 ቀን.1984 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአባ ገብረ ሥላሴ ጥበቡ ሰብሰቢነት በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተሰብስበው ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ፓትርያርክ መሾም አይቻልም ፣ የሲኖዶሱንና የፍትሐ ነገሥቱን ሕግ ስለሚያፋልስ ቀኖናችን አይፈቅድም ስለዚህ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ ሊደረግ የታሰበውን ሕገ ወጥ ሹመት በአጽንኦት እንቃወማለን ሲሉ በሙሉ ድምፅ ወሰኑ ። ውሳኔያቸውንም በዜና ማሰራጫ እንዲተላለፍ በማድረግ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን እንደሚደግፉ አረጋገጡ ።
ቢሆንም ግን የኢሕአዴግ ዓላማ ቅዱስ ፓትርያርኩን ከሥልጣን ማስወገድ ስለ ሆነ ፥ በቀጥታም በተዛዋሪም ያለ ዕረፍት ሥራውን ቀጠለ ። በዚህም መሠረት አቶ ሰገድ ደባልቀው የተባሉ ከፍተኛ የወያኔ ባለሥልጣን ፥ ከጳጳሳቱ መካከል ሥልጣን ይፈልጋሉ ፣ ወንበሩን ይሻሉ ተብለው የተጠኑ ጳጳሳትን ለየብቻ እየጠሩ የፓትርያርክነት ሥልጣኑ እንደሚሰጣቸው በቤተ መንግሥት ውስጥ በምሥጢር እያነጋገሩ እንደ ሆነ ታወቀ። በዚህም አደገኛ አካሄድ ጥቂት አባቶች ተማርከው የወያኔን መሰሪ ዓላማ አስፈጻሚና ፈጻሚ ሁነው ተነሡ ። በመከፋፈል እድለኛ የሆነው ወያኔ አባቶችን በቊጥጥሩ ሥር ካደረገ በኋላ በራድዮና በቴሌብዥን በቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ የስድብ ናዳ ያወርድ ጀመር ። ከጳጳሳቱ መካከልም ቀድሞውንም የውስጥ አርበኞች በመሆን ስንታገል ነበርን የሚሉ ብቅ አሉ ። ራሳቸውንም እንደ ኃላፊ በመቊጠር በሕገ ወጥነት ይሠሩ ጀመር ። ደጋፊ ለማብዛትና ቅዱስ ፓትርያርኩን ለማውረድ ሲሉም በጡረታ ተገልለው የነበሩትን ጳጳሳት ወደ ሥራ እንዲመለሱ አደረጉ ።
በጡረታ ላይ ከነበሩት መካከል ደብረ ሊባኖስ ገዳም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ብቻ ታሪኬን አላበላሽም ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አልጥስም ፥ ቤተ ክርስቲያኔን አላፈርስም ብለው ጥሪውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል ። እኒህን ታላቅ አባት እኛም አንረሳቸውም ፥ ታሪክም እንደነ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ሲያስታውሳቸው ይኖራል ። የሚገርመው ግን ይደልዎ ይደልዎ ብለው የሾሟቸውን ፓትርያርክ ከመንበራቸው በግፍ እንዲወጡ ማድረጋቸው አንሶ ያልታመሙትን እንደ ታመሙ ፣ ያልተናገሩትን እንደ ተናገሩ ፣ ሥልጣኑን በፈቃዳቸው እንደ ለቀቁ ተደርጎ በራዲዮና ፥ በቴሌብዥን፥ እንዲነገር በልዩ ልዩ ጋዜጣ እንዲወጣ መደረጉ ነው ።
ይሁን እንጂ የጠ/ቤተ ክህነት ሠራተኛ ሕጋችን አይጣስም ፣ ቀኖናችን አይፈርስም ፣ ፓትርያርካችን ያለ በቂ ምክንያት አይወርዱም በማለት እየተቃወመ በመሆኑ ለሦስት ወራት ያህል ደመወዙ በመንግሥት ትእዛዝ ታግዶ ቆየ ። እየተቃወመ ያለውን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኛ ወደ ጳጳሳቱ ጎራ ለማሰለፍ ሲባል ሐምሌ 27 ቀን 1983 ዓ.ም በአቶ ታምራት ላይኔ ፊርማ በቊጥር 60/ሐ2/02/44 በተጻፈ ደብዳቤ የታገደው በጀት ሲኖዶሱ በሚወክለው ሰው ፊርማ ወጭ እንዲሆን ተፈቀደ ።
ቅዱስ ሲኖዶሱም ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ፓትርያርኩ ስለ ታመሙ እስኪሻላቸው ድረስ ቡራኬና ጸሎት እያደረጉና ስማችው እየተጠራ እንዲቆዩ ፣ ሥራውን ሲኖዶሱ እንዲሠራ ሲል ወሰነ ።  ከአንድ ወር በኋላም መስከረም 28 ቀን 1984 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የሚል በቊጥር
69/398/84 በተጻፈ ደብዳቤ ታዘዘ ።
በቀጣይነትም በቃልም በስልክም ተገደው ተዋርደው ከሚወጡና ችግር ላይ ከሚወድቁ በአስችኳይ መንበረ ፓትርያርኩን ለቀው እንዲወጡ የሚል የማያቋርጥ ግፊት ከተለያየ አቅጣጫ ይጎርፍ ጀመር ። ሁኔታው እጅግ አደገኛ በመሆኑ መስከረም 30 ቀን 1984 ዓ.ም ከመንበረ ፓትርያርኩ ወጥተው በአዲስ አበባ ከተማ ተሰውረው እንዲቀመጡ ሆነ ።  በመቀጠልም ቅዱስ ፓትርያርኩ ወርደዋል ሳይባል ከቀኖና ውጭ አቡነ ያዕቆብ የተባሉ ኤርትራዊ ጳጳስ ዐቃቤ መንበር ተብለው ተሾሙ ። ሕገ ወጡ ሥራም በስፋት ስለቀጠለና እየተከናወነ ያለው ሁሉ እጅግ አደገኛ በመሆኑ ቅዱስነታቸው ጥር 15 ቀን 1984 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ ። የደብዳቤው ይዘትም እንደሚከተለው ነበር ።
«በሁላችንም በነበረው ግንዛቤ መሠረት እስከ አሁን በትዕግሥት የጠበኩት በወቅቱ የነበረው የውዥንብር ጊዜ እስኪያልፍና መላው የኢትዮጵያ ካህናትና ምእመናን ሁኔታውን በእርጋታ እስኪመለከቱትና እስኪያጤኑት ፣ ቅ/ሲኖዶሱም ከታሪክና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ትክክለኛውን ፍትሕ ተመልክቶ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠቃሚ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤ አስኪያገኝ ድረስ ዕድል ለመስጠት ነበር ። በተጨማሪም ሥልጣኑን የያዘው አካል እጁን ከቤተ ክርስቲያኗ ላይ እንዲያነሣና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞችን ደመወዝ እንዲለቅ የማሰቢያ ጊዜ ለመስጠት ነበር ። ይሁን እንጂ እንደ ታሰበው ሳይሆን ለዘመናት ተከብሮ የኖረውን የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና የሚጥስ ፣ ሕጓን የሚያፋልስ አደገኛ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል ።
ስለዚህ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ያለብኝን መንፈሳዊ ኃላፊነትና ተግባር ለማከናወን የሚያግድ የጤናም ሆነ የሌላ ችግር የሌለብኝ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስም የሚያውቀው ሀቅ ስለ ሆነ ፥ ቅ/ሲኖዶስ ሁኔታውን በጥንቃቄና በአትኩሮት አይቶ ያለውን አቋም በአስቸኳይ እንዲገልጽልኝ እጠባበቃለሁ። ወደ መንበሬም እንድመለስ ውሳኔውን እንዲያሳውቀኝ ይህን ማስታውሻ አቀርባለሁ» በማለት ጽፈዋል ። ግልባጭም ለሚመለከታቸው አድርገዋል ።
1ኛ ለአቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳንት፣2ኛ ለአቶ ታምራት ላይኔ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ፣ 3ኛ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ነገር ግን ለተጻፈው ደብዳቤ መልስ ከመስጠት ይልቅ በታሪክ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች በተቀደሰው ግቢ ያለ ሐፍረት ይከናወኑ ጀመር ። የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የኢሕአዴግ ደጋፊ በሆኑ ጥቂት ጳጳስትና ከባድ መሣሪያ በታጠቁ ወታደሮች ታሸገ ። በመቀጠልም በፈቃዳቸው ወርደዋል በማለት በተለያየ የዜና ማሰራጫ እንዲደመጥ ተደረገ ። መንግሥት ያቀደውና የፈለገው ተሳካለት ።
አስቀድሞ የመረጣቸው የአባ ጳውሎስ ሕገ ወጥ ሹመት ተፈጸመለት። ሕገ ወጡ ሹመት ከተፈጸመ በኋላም በማከታተል ቅዱስ ፓትርያርኩ ይጠቀሙበት የነበረው ሬንጅሮበር መኪና በአስቸኳይ እንዲመለስ በደብዳቤ ታዘዘ ። ፓትርያርኩም እንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ካሉት ትንንሽ ቤቶች ባንዱ ሂደው እንዲቀመጡ የሚል ቀጭን ትእዛዝ ደረሰ ። በሌላ በኩል ደግሞ ሥልጣኑን እንዲለቁ በሦስት ዓይነት መንገድ የማያቋርጥ ግፊት ቀጠለ ።
1/ ሥልጣኑን በፈቃዳቸው ፈርመው እንዲለቁና በሰላም ተከብረው እንዲኖሩ የሚያግባባ ፣2/ ወደው ሳይሆን ተገደው ሥልጣኑን እንደሚለቁ የሚያስፈራራ፣ 3/ በአስቸኳይ ሥልጣኑን ካለቀቁ በሕይወት መቆየት እንደማይችሉ በግልጽ የሚያስጠነቅቅ፣ 4/ ግን የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና መጣስ የሚቆጫቸውና የቅዱስነታቸው ሕይውት ያሳሰባቸው ከኢሕአዴግ ጋር የሚሠሩ ውስጠ አዋቂዎች የሚልኩት መልእክት ነበር ። መልእክቱም የሚያስረዳው ቅዱስ ፓትርያርኩ ባፋጣኝ ከሀገር ካልወጡ ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን በጥብቅ የሚያስገነዝብ ነው ።
 በተለይም በራዲዮና በቴሌብዥን በየቀኑ የሚሰማውና የሚታየው ሁሉ ሰብአዊነት የጎደለው ፣ ደም ደም የሚሸት መጥፎ ዜና ለታሪክም የማይመች ፣ ለቤተ ክርስቲያኗም የማይጠቅም አደገኛ አካሄድ እየሆነ መምጣቱ በግልጽ ታወቀ ። የኢሕአዴግ እጅ በረቀቀ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኗ ሰዎች ላይ መታየት ጀመረ ። ከሳሽ ቡድን መቋቋሙ በይፋ ተረጋገጠ ። የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሞት ዓይነት እንደ ቀረበ መረዳት ተቻለ ። ይህ በእንዲህ እያለ ሀገር ውስጥ መቀመጡ የጅል ሞት መሞትና ደመ ከልብ ሁኖ መቅረት እንደ ሆነ በግልጽ ታወቀ ። በመሆኑም ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመው ቅዱስ ፓትርያርኩ ነጻነት ወደ አለበት ሀገር ተሰደው በሕይወት ቢቆዩና ፥ የተፈጸመው ስሕተት እውነት መስሎና ሕግ ሁኖ እንዳይቀጥል ፣ ቤተ ክርስቲያኗም በየጊዜው የሚነሡ የፖለቲከኞች መሣሪያና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ሁና እንዳትቀር ፣ እውነቱ በግልጽ እንዲታወቅና ስሕተቱ እንዲጋለጥ ቢደረግ የተሻለውና አማራጭ የሌለው ቅዱስ ሥራ መሆኑ ታመነበት ። በመሆኑም መስከረም 30 ቀን 1985  ዓ.ም ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ የስደቱ ጉዞ ተጀመረ ።
ስደቱን በድፍረት እንድንገባበት ከረዱን ምክንያቶች አንዱ በወቅቱ በኬንያ የናይሮቢ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩት በአሁኑ ሰዓት በሲያትል የሚኖሩት ብፁዕ አቡነ ሉቃስና ፥ መልአከ ብርሃናት አባ ገረ ሥላሴ የኋላእሸት ፥ ቅዱስነታቸው ወደ ኬንያ ቢመጡ ሁሉ ነገር እንደ ተመቻቸና ችግር እንደሌለ በመግለጽ የጻፉልን ደብዳቤ ዋናው አሳማኝ ምክንያት ነበር ።
የስደቱ ጉዞና ቀጣይ ሕይወት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሞት የተጣሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ፥ አሁንም እንዳይደገም ከሀገር መውጣቱ አስፈላጊ ሁኖ ስለ ተገኘ ፥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል ሥራው በጥንቃቄ መጠናት ተጀመረ ። በመጀመሪያ የተደረገው ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀው ሰው ወደ ሞያሌ በመሄድ አስፈላጊውን ጥናትና የመጓጓዣ ሰነዶችን አመቻችቶ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ለጉዞው የሚያስፈልጉ እንደ መኪና ፥ ሹፌርና መንገድ ጠቋሚ ወዘተ እንዲመቻቹ አደረገ ። ለጉዞው የተሻለ ይሆን ዘንድ በቤተ ክህነት አንድ ታላቅ ስብሰባ የሚደረግበት ዕለት ተመረጠ ። ይህም ታላቅ ስብሰባ በሚጀመርበት ዕለት መስከረም 30 ቀን 1985 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ከአዲስ አበባ በመነሣት በወቅቱ 14 የፍተሻ ጣቢያ ያለበትን አስቸጋሪ ጉዞ እግዚአብሔርን በማመን በድፍረት ተጀምሮ በሰላም ሞያሌ ለመድረስ ተቻለ ።
ይሁን እንጂ እጅግ አስፈሪውና አሳሳቢው ጉዳይ ደንበሩን (ቦርደሩን) እንዴት መሻገር እንደሚቻል ነበር ። ግን ዝርዝሩን መግለጽ ለጊዜው ይቆየንና ባጭሩ በገባንበት ዕለት ጨለምለም ሲል በፈጣሪ አጋዥነት እንደ ተአምር በሚቈጠር መልኩ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቦርደሩን እንዲሻገሩ ተደረገ ። በማግስቱ ጧት ከቦረናና ከገሬ ተገዝተው ለእርድ ወደ ናይሮቢ በጭነት መኪና ተጭነው ከሚሄዱ ከብቶች ጋር ተጭነን ሽፍታና ነፍሰ ገዳይ የሚፈራረቅበትን የበርሀ ጉዞ ነፍሳችን ለግዚአብሔር አደራ ሰጥተን ገባንበት ። ቅዱስ ፓትርያርኩን ግን ለሹፌሩ የሆነ ነገር አድርገን ጋቢና ውስጥ እንዲሳፈሩ ሆነ።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ 500 ኪሎ ሜትር አስቸጋሪ የበረሃ መንገድ ተጉዘን ‘ኢሲኦሎ’ ከሚባለው ከተማ ገብተን ለማደር ቻልን በማግስቱ ከከብቶቹ ተለይተን አራት ሰው በምትይዝ መኪና ተሳፍረን ናይሮቢ ከተማ ለመግባት ቻልን ። ናይሮቢ ከተማ እንደ ደረስን አንድ ያልጠበቅነው ችግር ተፈጠረ ። ከኢሲኦሎ ናይሮቢ የወሰደን ሹፌር በቀጥታ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ሆቴል ወስዶ ዘመዶቻችሁ እነዚሁላችሁ ገንዘቤን ስጡኝና ውረዱ አለን። እጀ ረዥሙ አሳዳጃችን በየት ቀድሞን መጣ ብለን እንደ መደናገጥ አልን ። ሁኖም ግን ግራ መጋባታችን የተረዳው ኬንያዊው ሹፌር እኔ እኮ ወደዚህ ያመጣኋችሁ ከወገኖቻችሁ ጋር እንድትቀላቀሉ በማሰብ ነው ሲለን ፥ የለም እኛ የምንፈልገው የተሻለ ሆቴል ነው ። ወገኖቻችን ሌላ ቀን እናያቸዋለን አልነውና መሀል ከተማ ወስዶን የሌላ ሀገር ዜጋ የሆነ ሆቴል ለመያዝ ቻልን ። የሚገርመው በሌላ ጊዜ ስናረጋግጥ ለካ መጀመሪያ የሄድንበት ያ ሆቴል የወያኔ ሆቴል ነበረ ።
 ሆቴላችን ከያዝን በኋላ ከሀገር ለመውጣት ምክንያት ለሆኑን ሰዎች ስልክ ደውለን ለመገናኘት ቻልን ። ከነሱም ጋር በመመካከር ለኬንያ መንግሥትና ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ክፍል ማንነታችን ገልጸን ተመዘገብን ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ክፍልም ከናይሮቢ ወጣ ብሎ ጫካ ውስጥ ከሚገኝ የአንገሊካን ቸርች ሀብት ከሆነ ልዩ ስሙ ቅዱስ ዩሊያንስ ገስት ሀውስ ከተባለ ቦታ ወስዶ ከብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ጋር ቀላቀለን ። ይህም ቦታ የሀገራችን ገዳም የሚመስል እግዚአብሔር ያዘጋጀው ለጸሎት የሚመች ስፍራ ነበር ። ሁለቱም ታላላቅ አባቶች ለዓመታት የጸለዩበትና የባረኩት የተቀደሰ ቦታ ነው ።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ በወቅቱ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነት በተቋቋመው ኢዴሀቅ በሚባለው ድርጅት አማካይነት አሁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ፓትርያርክ እኔ ነኝ ሲሉ በራዲዮ መግለጫ ሰጡ ። በመንግሥት ፈቃድና በጠመንጃ ኃይል የተደረገው ሹመት ቀኖና የጣሰ በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው ሲሉም አወገዙ ። ይሁን እንጂ የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ ሌሎች በወቅቱ ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለ ነበራቸው ተቃዋሚውን ለማዳመጥና ጥገኝነት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም ። ስለዚህ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ5 ዓመታት ያህል በምድረ ኬንያ እንዲቆዩ የተደረገው ከዚህ የተነሣ ነው ።
እንደሚታወቀው ሁሉ ኬንያ ውስጥ ለመቆየት እጅግ ከባድ ነው ። ምክንያቱም የሕይወት ዋስትና የለም። ብዙ ሰዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል ። የብዙ ሰዎች ሕይወት በጠራራ ፀሐይ ተቀጥፏል ። ብዙ ሰዎች መንግሥት ባለበት ሀገር በዋና ከተማው ሳይቀር በሚዘገንን ሁኔታ ይደበደባሉ ፣ ያለ ምክንያትና ያለፍርድ ይታሰራሉ ። ከዚህ የተነሣ የነበረው ጭንቀት ፈጽሞ ሊረሳ የማይችል መጥፎ ትውስታ ነው ። በዚህ አጭር ጽሑፍ ተገልጾ የሚያልቅም አይደለም ። የሚገርመው በዚያ በርሀ 500 ኪሎ ሜትር አብረውን የመጡት ከብቶች በቀናት ውስጥ በናይሮቢ ከተማ ቄራ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው ሲያልፍ ፥ እኛ ግን ክብር ለስሙ ይሁንና እግዚአብሔር ጠብቆን እስከ አሁን በሕይወት አለን ።
ሁኖም በሰው እጅ ከመሞት ብናመልጥም በሹፌርነት ይዞን የወጣውን ቆራጡ ወንድማችን መሐሪ ይባቤን ሳናስበው የኬንያ ወባ በሽታ ድንገት ነጠቀን ። ይህም ያልተጠበቀ ሁኔታ ሁል ጊዜ ሲያሳዝነን ይኖራል ። እጅግ በጣም የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር ደግሞ ለ5 ዓመታት ያህል በምድረ ኬንያ ስንቆይ ቅዱስ ፓትርያርኩ አንድ ቀን ሐኪም ቤት ሳይሄዱ ፥ በጸሎትና በጾም ተወስነው ገዳማዊ ሕይወት ኑረው የተፈቀደላቸው ሱባኤ ሲያልቅ በመንፈስ ልጆቻችው አማካይነት ወደ አሜሪካ ሲያትል ሊገቡ መቻላቸው ነው ።
አሜሪካ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን ስደታቸውን እግዚአብሔር ባርኮላቸው ቤተ ክርስቲያናችን በውጭው ዓለም አብባ ፣ ከዕለት ወደ ዕለት አገልግሎቷ እየሰፋ ጳጳሳት ፥ ካህናትና ዲያቆናት እየተሾሙ ፣ ስብከተ ወንጌል እየተስፋፋ ፣ የምእመናን ቊጥር እየጨመረ ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እየተከፈቱ ታላላቅ ካቴድራሎች
እየታነጹ ፣ ሁለገብና መጠነ ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት እየተከናወነ ይገኛል ።
በመጨረሻም ፣ ሁኔታወች ሲፈቅዱ እኛም ታሪክም የሚያስታውሳቸው ፥ በስደት ዓለም ቅዱስ ፓትርያርኩን በገንዘብ ፥ በጉልበት ፥ በሐሳብ የረዱ ብዙዎች መኖራቸውን እያስታወስኩ ፣ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጓ ፈርሶ ፥ ቀኖነዋ ተጥሶ ፥ ሕጋዊው ፓትርያርያርኳ በግፍ ተሰዶ ፣ ሕገ ወጥ ፓትርያርክና ሲኖዶስ ተቋቁሞ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ክፉኛ ተናግታ ፣ ካህናቶቿና ምእመናኖቿ ተመሰቃቅለው ፣ የዓለሙ ሁሉ መዘባበቻ ሁነው ፣ በተለይም የሕጓን መፍረስና የቀኖነዋን መጣስ ተከትሎ የተፈጠረው መለያየት የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ልብ ክፉኛ የሰበረና በቀላሉ የማይጠፋ የአእምሮ ሕመም መሆኑ ለሁሉም ይታወቃል ። ይህም አጋጣሚ ለውጭና ለውስጥ ጠላት መግቢያ በር ፣ ለቅርሶቿ ምዝበራና ውድመት ፣ ለሥነ ሥርዓት ጉድለትና ለሥርዓት አልበኝነት መከሠት ዋና ምክንያት ሆኗል ።
ዛሬ ይህ ሁሉ ታሪክ ተቀይሮ ጊዜ ያነሳውን ጊዜ ጥሎት በክቡር ጠ/ምኒስትር አብይ ያላሰለሰ ብርቱ የቤተክርስቲያኒቷም አንድነት የቅዱስነታቸውም ወደ ቀደመ መንበራቸው ከነ ሙሉ ክብራቸው መመለስ እውን ሆኗል ።
እግዚአብሔር የሀገራችንና የቤተ ክርስቲያናችንን ትንሣኤ፣ የሕዝቦቿን አንድነትና ፍቅር እንዲያሳየን ፈቃዱ ይሁንል አሜን
Filed in: Amharic