>

ኢትዮጵያዊ ከሃይማት ይልቅ ብሄሩን ያስቀድማል!!! (ኤርሚያስ ቶኩማ)

ኢትዮጵያዊ ከሃይማት ይልቅ ብሄሩን ያስቀድማል!!!
ኤርሚያስ ቶኩማ
 
* ሌሎች እኛን የሚያስቡን በሌላ እኛ እየሆንን ያለነው ሌላ!!!
 
ከላይ  ከላይ ሃይማኖተኛ እንደሆንን ይወራል እንጂ ለእምነታችን ከምንሰጠው ዋጋ ይልቅ ለብሄራችን፣ ለጎሳችን የምንሰጠው ዋጋ ይበልጣል። ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛ እንደሆንን እናወራለን ከእኛ አልፎ  በርካታ የውጭ ፀሐፊያን ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛ ናቸው ሲሉ ፅፈዋል። ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት የተፃፈው የግሪካዊው ደራሲ የሆሜር ኦሊያድ የተሰኘው መፅሐፍ ገና ከመግቢያው ላይ፣ የግሪኰች የአማልክት አምላክ የሚባለው “ዚየስ” ከርሱ በታች የሚገኙትን አመልክቶች ሁሉንም ይዞ ለአስራ ሁለት ቀናት ፍፁም ቅዱስ ወደሆኑት ኢትዮጵያውያንን ለመጐብኘት መሄዱ ተፅፏል፡፡
በዚሁ በሆሜር በተፃፈው ሌላኛው መፅሐፍ ማለትም በኦድሴይ ውስጥ ደግሞ ፓሲዶን የተባለው ገፀባህሪ፣ “ከሩቆቹ ኢትዮጵያዊያን ድግስ ላይ እጅግ ተደስቶ ቆየ” ይላል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ የነበረው የግሪኩ ሊቅ ዲዎደረስ ሲክለስ ሲፅፈ፣ ኢትዮጵያዊያን አማልክቶች ሁሉ የሚገዙላቸው፣ እንደውም የአማልክቶች ሁሉ ፈጣሪና አዛዥ መሆናቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ጽፏል፡፡ የቤዛንታይኑ እስጢፋኖስም “በአማልክት ማምለክን የጀመሩ እና ያስፋፉ ኢትዮጵያዊን ናቸው” በማለት እንደፃፈም ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ከአስጢፋኖስ ጋር ዘመንተኛ የነበረው ላክታኒሻስ ፕላሲደስ የተሰኘ ሌላ ደራሲ ይህንኑ ኀሳብ በማጐልመስ የሚከተለውን ጽፏል፡፡ “አማልክት ኢትዮጵያዊያንን የሚወዱበት ምክንያት ፍትሀዊ ስለሆኑ ነው፡፡
ፍትሀዊነት የእኩልነት ባህልና ሀቀኝነት ስላላቸው ጁፒተር ከሰማየ ሰማያት ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያዊያን እየሄደ ከነርሱ ጋር መዝናናት ያዘወትራል ሲል ሆሜር እንኳ ሳይቀር ጽፏል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ከማንኛውም ህዝብ የላቀ ፍትሐዊነት ስላላቸው አማልክቱ ከተከበረ መኖሪያቸው እየወጡ እነሱን መጐብኘት ያዘወትራሉ፡፡” ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚህ Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚያወሱት ኢትዮጵያዊያን ፍትሃዊ እና ሃይማኖት አጥባቂዎች እንደሆኑ ጥንታዊ ፀሐፊያን መግለፃቸውን አፅንኦት ሰጥተው ፅፈውበታል፡፡ በሦስተኛው ምዕት ዓመት ኢትዮፒካ በሚል ርዕሰ ሄሊዮዶሩስ የተባለው ደራሲ በፃፈው ልቦለድ ውስጥ የቀረቡት ገፀ-ባህርያት በሃይማኖታቸው የበቁ እና ወደ ፅድቅ መንገድ ላይ ያሉ ነበሩ፡፡ ይህንን የፅድቅ ኀሳብ በመከተል ይመስላል ሳሙኤል ጆንሰን የተባሉት ደራሲ ራሴላስ በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ የቀረበውን ኢትዮጵያዊ መስፍን ሐቀኛ፣ ቅን እና የበጐ ምግባሮች መፍለቂያ አድርገው የሳሉት፡፡ በእስልምናው ዓለምም ኢትዮጵያ ገናና ሀገር ሆና ትጠቀሳለች፡፡ የዓለም ሙስሊሞች ባብዛኛው ኢትዮጵያ የተከበረች እና በነብያቸውም የምትወደድ የሰላም ምድር መሆኗ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ሲራ በሚልር ርዕስ ስለ ነቢዩ መሐመድ የሕይወት ታሪክ ያዘጋጀው ኢብን ሒሻም የፃፈው በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ እርሱ ገለፃ፣ “ቁራይሽ” የሚሰኙት የመካ ገዢዎች የነብዩ መሐመድን ተከታዮች እያሳደዱ ቢያስቸግሩዋቸው፣ ለተከታዮቻቸው የሚከተለውን ምክር እንደለገሷቸው ሲራ በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ “ወደ ሀበሻ ሀገር ብትሄዱ፣ በግዛቱ ማንንም የማይጨቁን ንጉሥ ታገኛላችሁ፡፡ ያቺ ሀገር የጽድቅ ሀገር ናት፡፡
አሏህ አሁን ካለባችሁ ስቃይ ሁሉ የሚያሳርፋችሁ እዚያ ብትሄዱ ነው” በተለያዩ የእምነት እና የታሪክ መፅሃፍት የተፃፉት ሁሉ የሚያሳዩት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛ ለእምነታችን ተገዢ እንደሆንን ቢገልፁም ምግባራችን ግን እንደሃይማኖት ሰዎች አይደለም። እየሱስ ክርስቶስ ባለንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደደው እያለ እኛ ግን  የምንወደውን ሰው ብሔር እንመርጣለን። ነብዩ መሐመድ ዘረኝነት ጥንብ ናትና ራቃት እያሉን በዘር ስንሰባሰብ እንውላለን። አንድ የሀገር መሪ ሥልጣን ሲይዝ ቀድመን የምናጣራው ብሄሩን ነው፤ የተቸገረን ሰው ለመርዳት ብሄሩን እያየን የምንሰባሰብ ሰዎች ነን። ብሄራችን ከእምነታችን በላይ አእምሯችንን ተቆጣጥሮት ጎጠኞች ሆነናል። ጎሰኝነታችን በየእምነቶቻችን የታዘዝናቸውን መልካም ተግባራት እንዳናከናውን ጋርዶ ይዞናል። ሁላችንም ለየእምነት ስርአታችን ተገዢ ብንሆን ጎሰኝነትን ማክሰም እንችል ነበረ።
Filed in: Amharic