>
5:13 pm - Monday April 19, 3255

" ኢትዮጵያ መከራን ተሻግራ ፈተናን ተቋቁማ ብቅ የማለት ታሪክ ያላት እፁብ አገር ናት !!!" (ቴዎድሮስ ፀጋዬ)

” ኢትዮጵያ መከራን ተሻግራ ፈተናን ተቋቁማ ብቅ የማለት ታሪክ ያላት እፁብ አገር ናት !!!”
ቴዎድሮስ ፀጋዬ
ኢትዮጵያዊነት አንዱ በተፈጥሮ የሚጎናፀፈው ሌላው ደግሞ በቸርነት የሚመፀወተው እርከን ወይም ደረጃ ያለው ማንነት ነው ብዬ በፍጹም አላምንም፣ ሁሉም ዜጎች አሁን በታሪክ ክፉ እድል ከኛ የተነጠሉትም ጭምር እኩል ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ተጠራጥሬ አላውቅም። እርግጥ ነው ከአንድ ወይም ከሌላ ብሄር ወገን ነን የሚሉ ባእድና የማይገጥም ጽንሰ ሀሳብ ከየትም ተበድረው አገርን በመስራት ሂደት ውስጥ የተፈጠሩን ቁስሎች ቦርቡረውና ታሪክ አዛብተው፣ እንደ ብሄር የመጠቃትን ስሜት የፈበረኩና ያግለበለቡ፣ በዚህም ፍብርክ ስሜት መሰላልነት ወደ ስልጣን የወጡና አሁንም አዲስ ሌላ ድንክ አገር መመስረትን የሚያልሙ ለአገራች ህልውና የሚያሰጉ ብዙዎች መኖራቸውን አውቃለው እቃወማቸውምአለው። በዚያውም ልክ ግን ራሳቸውን ከሌላው ይበልጥ ኢትዮጵያውያን አድርገው የሚሾሙ ዘረኝነታቸውን ኢትዮጵያ በሚል ውብ ስም የሸሸጉ በተግባር ግን ሁሉንም የዘረኝነት ብየና የሚያሟሉ፣ ከነርሱ የተለየ ሀሳብ የያዘን ሁሉ በራሳቸው የዘረኝነት ሚዛን ሰፍረው ስም የሚሰጡ፣ ኢትዮጵያውያ የሚለውን የተቀደሰ ስም በአፋቸው የመደጋገማቸውን ያህል በነውራቸው የሚያራክሱ ውድና ውብ ለሆነው ሁሉንም ለሚያስጠልለው ኢትዮጵያውያዊ ብሄርተኝነት እንደ ስድብ የሚቆጠሩ በርካቶችንም አስተውላለው።
.
ከልዩነቱ ገደል ወዲህና ወዲያ ያሉ ዘረኞች የቆሙበት አንፃር ይለያይ እንጂ አፈራረጃቸው አስተሳሰባቸውና አፈፃፀማቸው በእጅጉ ተመሳሳይ ነው። በነዚህ ሁለቱ ውዝግብና ፍጭት ሳቢያ የሚመጣው ዳፋ የሚወድቀውና እዳው የሚተርፈው፣ እርስ በእርስ ላይለያይ የተሳሰረው እየተጋባ እየተዋለደና እየተገበያየ ዘረኝነትን እንደማይሻ በተግባር ሲያሳይ የኖረውና አሁንም እያሳየ ያለው ህዝቡ መሆኑ ግን ልብ ይሰብራል።
ኢትዮጵያ በዘውገኞች ቱማታ በውጭ ጠላቶች ጦር በተፈጥሮ አደጋም ሆነ በድህነት ህልውናዋ ይፈተናል ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ መከራን ተሻግራ ፈተናን ተቋቁማ ብቅ የማለት ታሪክ ያላት እፁብ አገር ናት። ነገር ግን ከመንግስት የጠመንጃ አፈሙዝ አሊያም ከአንድ ፖለቲከኛ የሃይማኖት ተከታይ ወይም የከያኒ ተከታዮች ጩሀት በቀር ሌላ የምትፈልቅበት የእውነት ምንጭ የለም በሚል እምነትና ያንን እምነት በተመረኮዘ የአፈና ተግባር ከቀጠልን ያኔ ነው ያገራችንን ትንሳኤና መዳን የምናርቀው።
.
በወላጆቼ በኩል ያገኘሁትን ማንነት መጣል ሳያስፈልገኝ ነገር ግን በምርመራ በምርጫና በውሳኔ ይበልጥ የማጎላቸውና የምገለጥባቸው ማንነቶች ያዋሃድኩ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ።እናም እኔ ከኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ስለተገኘሁ የማመሰግን ልበ ሙሉ ኢትዮጵያውያዊ ነኝ እኔ ዘንድ የትግራዋይነት ፋይዳ የሚለካው ኢትዮጵያውያዊነትን ለመፍጠር ባለው መዋጮና ኢትዮጵያውያዊነት ወደሚባል ታላቅነት ባለው መንገድነት ልክ ነው። እኔ በመቀሌ አፈር በሻሸመኔ ፀሃይ በደብረዘይት ነፋስና በአዲስ አበባዬ ውሃ የተሰራሁ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ከኢትዮጵያዊነት ቀጥሎ ራስህን እንዴት ትገልጣለህ ለሚሉኝ ሁሉ እነሆ መልሴ የዛች የሁሉ ጥላ የሆነች የምንግዜም የኢትዮጵያዊነት ሁነኛ ቋት የጣይቱ ከተማ ዜጋ የሆንኩ አዲስ አበቤ ነኝ።
ሆኖም ማንነትህን በብሄር በኩል ካልነገርከኝ አይገባኝም ለሚለኝ ተላላም እነሆ ምላሼ አዲስ አበቤነቴ በወላጆቼ በኩል ያገኘሁትን የትግራዋይነት ጸጋ አይገፈውም ምክንያቱም ለኔ ትግራዋይነት ኢትዮጵያን እንደ ሰፌድ ባስባት ሰበዙ ሊሰበዝ የጀመረበት አካባቢ ማለት ነው። ትግራዋይነት ለኔ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ክርስትናና እስልምና የሚሰኙ ታላላቅ ሀይማኖቶች ወደሀገሬ የገቡበት በር አካባቢ መፈጠር ማለት ነው ትግራዋይነት ለኔ ኢትዮጵያ የምትሰኝ ቤት ስትሰራ መሰረቷ በተቆፈረበት ስፍራ መገኘት ማለት ነው። ትግራዋይነት በኔ መዝገበ ቃላት ኢትዮጵያዊነት ሲወጠን ማለት ነው። የሰለባነት እንጉርጉሮ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት መድረክ ላይ አቀንቃኝ ማለት ነው። ያውም የማለዳ የዳር አገርነት ባይተዋርነት ሳይሆን ኢትዮጵያን የመሰለች አገር መስራች የመሆን ታሪካዊ እድል ባለቤትነት ነው።
.
ትግራዋይነት የኢትዮጵያዊነት እልፍኝ እንጂ ዘውገኞቹ እንደሚሰብኩት ከኢዮጵያዊነት የሚያሸሽ መውጫ በር አይደለም። ኢትዮጵያዊ ማንነት በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ዜጎች እኩል የሚደርስ ለሁሉ ጥላ ለሁሉ ቤት የሚሆን ማንነት እንጂ አንዳንዶች እንደሚስሉት እነኚህ በደማቸው የሚዘዋወር እነኛ ደግሞ ከላይ የሚለብሱት አሊያም የሚታረዙት የኪራይ ወይም የውሰት ልብስ አይደለም።
ከእድሜዬ ማለዳ አንስቶ ዛሬ ድረስ ሲጠና እንጂ ሲላላ ያላየሁት ሲበረታ እንጂ ሲደክም ያላስተዋልኩት ኢትዮጵያዊነቴ ነው። በልጅነት እንደ ወተት የጠባሁት፣ እንደ አፈር የቃምኩት፣ እንደውሃ የተራጨሁት፣ እንደ ጠበል የተረጨሁት ማንነት ኢትዮጵያዊነትን ነው።
.
ይህም ማንነቴ የወረስኩት ብቻ ሳይሆን የመረመርኩት የተቀበልኩት ብቻ ሳይሆን ያዳበርኩት ያውጠነጠንኩት ብቻ ሳይሆን የኖርኩትም ጭምር ነው። በደም ከተዋጀ ነፃነቷ ነፃነቴን ሰርቻለሁና በመስእዋትነት ከፍ ካለው ሰንደቅ በራስ እግር መቆምን በራስ ጥበብ ቀለምና ታሪክ መኩራትን አውቄያለውና የሰርክ የዜግነት ጸሎቴ ይህ ነው፣ “እርሷው በለገሰችን ልብ ውስጥ እርሷው የተቀረጸችበት፣ እርሷም በፈተለችው ማንነታችን ድርና ማግ እርሷው የተሸመነችበት ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ትኑርልን። ከየሰሞንኛ ግርግርና ከባለዘንጎች ቁርቁስ በላይ የሆነች ኢትዮጵያ፣ ከፖልታኪዎች ሴራና ከተዛነፈ ትወራ በላይ የሆነች ኢትዮጵያ ሁልግዜም ትኑርልን። ጥላነቷ ከአውሬ የሚታደግ፣ ቤትነቷ ከሰውነት ቁር የሚከልል ፣ ስበትነቷ ልጆቿን የሚያዋህድ፣ አበቅየለሽ ኢትዮጵያ ሁሌም ለዘላለም ከፍ ትበልልን። በድህነቷ ከናትነት የማትፋቅ፣ በዘረኝነት ድቤና በጠባብነት ነጋሪት የማትሸበር፣ በአምባገነን ጭነት የማትቀጭ፣ በሚፈራረቅ ውዝግብና ጦርነት መሰረቷ የማይናወጥ፣ አለች እስካልን ድረስ ያለች የምናባችን ፈጣሪ፣ የምናባችንም ንግስት እርሷ ራሷ ምናባችን የሆነች ኢትዮጵያ ሁሌም ዘወትርም ትኑርልን አሜን።

 

Filed in: Amharic