>

ጠ/ሚ አቢይ አሕመድ አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድየ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

FBC 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድየ በዓልን በማስመልከት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው የመልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድየ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና የወንድማማችነት ህያው ማስረጃ!

በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን የሀገራችንን ህዝቦች እንዳይበታተኑ ያስተሳሰሩ፤ እንዳይለያዩ ያጣመሩ፣ እንዳይፈርሱ ያማገሩ በርካታና ጠንካራ ማጎች በሀገራችን ሁሉም ጫፎች በክብር እና በፍቅር እዚም እዚያም አሉ። ህዝቦቻችን በጋብቻ ተዛምደው፣ በማንነት ተዋህደው የኖሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው።

ልክ እንደ ምስራቁ፣ ደቡቡና ምእራቡ ህዝባችን ሁሉ የሰሜን የሃገራቸን ህዝቦችም በባህል፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ወዘተ ተሰናስልው፤ ተዋደውና ተዋህደው የኖሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ስለመሆናቸው በርካታ የታሪክ፣ የባህል፤ የእምነት እና የቋንቋ ማስረጃዎች ማቅረብ የሚያስፈልገው ሁነት ሳይሆን በህይወታቸው ውስጥ ከተረበረቡ እልፍመገለጫዎቻቸው የሚስተዋል ግሩም እውነት ነው።

የዚህ አንድነትና የጋራ ማንነት- የዚህ ዘመንን እንኳ የሚያስገብር ከነፍስ የተሸመነ እውነት ማሳያ ከሆኑ የማህበረሰባችን እሴት ባህሎች ውስጥ ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኩናማ እና የኢሮብ ህዝቦች መመሳሰልና መተሳሳርን የሚያሳየው የአሸንዳ/ ሻደይ ክብረ በአል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ነው።

የዚህን በአል አከባበር ለሚመለከት የውጭ ታዛቢ የሰሜን ህዝቦቻችን በሁሉም መለክያ አንድ ህዝብ እንጂ ሁለት ወይም ሶስት ሆነው ሊታዩት እንደማይችሉ እሙን ነው።
የሰሜኑ ክፍል የሀገራችን ህዝቦች ልክ እንደ ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምእራቦቹ ህዝቦቻችን ከሚያለያዩዋቸው ይልቅ አንድ የሚያደረጉዋቸው እንደሚበዙ ብዙ ከማስረዳት ይልቅ የአሸንዳን አንድ ሰበዝ በፍቅር ማሳየት ሁሉን ነገር ይገልጸዋል።

ስለ አንድነታቸው ከመግለጽ ይልቅ ስለ ለዩነታቸው ለመግለጽ ይቸገራሉ። ምክንያቱም አንድ የሚያደርጓቸው መገለጫዎች ከሚያለያያቸው ይበዛሉና ነው። አንዱን ከአንዱ ለይቶ ለመረዳት ማንነቱንና ብሄሩን በመጠየቅ ከአንደበቱ መስማት ካልሆነ በስተቀር፣ ከአመጋገቡ፣ ከአለባበሱ፣ ከባህሉ፣ ከእሴቱና አኗኗሩ እንዲዚሁም ከክብረ በአላቱ ተነስቶ ማንም ይህ ከዚህ ነው፤ ያ ከዚያ ነው ለማለት አይችልም።

የህዝቦቻቸን ትስስር፣ በማንም ጫና ወይም አስገዳጅነት ሳይሆን ከህዘቦቹ የገራ ማንነትና የጋራ ታሪክ የሚቀዳና የትላንት ታሪካቸውም ሆነ የዛሬ እውነታቸው ነው፡፡

የነዚህን ህዝቦች የአብሮነት ታሪክ እና ባህል ስንመረምር የምናገኘው የአሸንዳ/ ሻደይ በአላቸውም በየትኛውም የዘመን ሀዲድ ላይ የትኛውም መንገራግጭና ንትርክ ቢኖር እንኳን በሁልጊዜ ህይወታቸውም ሆነ በታሪክ መሰውያቸው ላይ ያለው እውነት አንድ እንደሆኑ የሚናገር፤ በሚመጣውም ዘመን አንድ ሆነው እንደሚቀጥሉ የሚያመለክትበርካታ ህያው ምስክር ያለበት ውብ ሰነድ ነው።

የአሸንዳ/ ሻደይ በአልን የመሳሰሉት የጋራ እሴቶቻችን ከቀደምት አባቶቻችን ጋር በመንፈስ የሚያስተሳሱሩን ድሮች፣ ወደፊትም አብረን እንድንጓዝ የሚያደረጉን መንገድ እና አጓዦቻችንም ጭምር ናቸው።

ስለ ትላንት፣ ስለ ዛሬና ስለነገ አንድነትና አብሮነት ከሚናገሩ ህያው ምስክሮች አንዱ ይጾመ ፍልሰታ ለማርያምን መፈታት ተከትሎ ከነሃሴ 16 ጀምሮ ቀጥሎ ባሉ ቀናት በተለያያ እድሜ ደረጃ ያሉ ሴቶች በዋናነት ግን በወጣቶችና ልጃገረዶች የሚከበረው የአሽንዳ/ ሻደይ በኣል ነው።

ይህ በአል በሀገራችን ከሚከበሩ ደማቅና ሀሴትን ከሚሞሉ በአላት አንዱ ሲሆን፤ ከሌሎች በአላት የሚለየውም የበአሉ ባለቤቶች ሴቶች በተለይም ወጣት ሴቶች መሆናቸው ነው።

ይህ በአል የሴት ልጆች በተለይም ወጣት ሴቶች አንገታቸውን አቀርቅረው በሚሄዱበትና በአደባባይ ወጥተው ፍላጎታቸውን በማይገልጹበት ወቅት ሁሉ በሙሉ ነጻነት ይልቁንም በጋራና በአደባባይ የወደዱትን የሚያሞጉሱበት፣ የጠሉትን ሃሳብና ተግባር በነጻነት የሚያወግዙበት ድንቅ በአል ነው።

የአሸንዳ/የሻደይ በአል ዜጎቻችን ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ከፈቀድንና ባህል ካደረግነው የሚያስፈራንና የሚያስደነግጠን ሳይሆን በአሸንዳ/ /ሻዳይ በአል ላይ እንደሆነውና እየሆነ እንዳለው እጅግ ማራኪና ውብ የሆነ የጥንካሬና የነጻነት መገለጫ ሆኖ በመኖር በፍቅር የምናከብረው ብቻ ሳይሆን ለአብሮነታችን ማሰረገጨ ማህተብ ሆኖ ከየልባችን የምናኖረው ባህላዊ የአብሮነት ሙዳያችን ነው።

ልክ በአሁኑ ሰአት በአሸንዳ/ሻደይ እንደምንደሰተው ሁሉ ልጆቻችና ቀጣዩ ትውልድ ሃሳብን በነጻነት በአደባበይ የመግለጽ ባህል ስለአወራስናቸው ሲያሞግሱን ይኖራሉ።

አሸንዳ/ ሻደይ የሴቶች ውበት፣ ክብር እና ነጻነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን ነጻነት ራሷ ነጻ የምትወጣበትና በአደባበይም ስጋ ለብሳ የምትታይበት ታላቅ ቀን ነው።

አሸንዳ/ሻዳይ ስለ ሴቶች ክብር፣ ስለባህሎቻችን ውበት፣ ስለህዝቦቻችን ወንድማማችነትና አንድነት የሚናገር ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም መስክ ህዝቦቻችን ነጻ ቢሆኑ፤ ሃሳቦቻቸውን በነጻነት ነገር ግን በሰላም በአደባበይ የሚገልጹበት ሁኔታ ቢፈጠር ምንኛ ውብና ድንቅ ሃገር ሊኖረን እንደሚችል አፍ አውጥቶ የሚነገር ህያው ትእምርት ከመሆኑም ባሻገር ለዘመናዊው የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታችንም ከባህላዊው ድንቅ ሀብታችን ብዙ የምንመነዝርበት ድንቅ ሀብታችን ነው። አሸናዳ//ሻደይ ከሀገራችን አልፎ ለአለም ቅርስነት የሚበቃ የማይዳሰስ ሃብት ነው።

ይህ ሀብት ከሰሜን ኢትዮጵያ አልፎ በደቡብ ኤርትራም ጭምር የሚከበር ውብ በአል ሲሆን፤ ልናከብረው፣ ልንንከባካበው፣ እና ታሪካዊ እሴቱን ሳይለቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ልናስተላለፈው የሚገባን መሆኑ አጽንኦት ሰጥቼ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

በአሉ የህዝቦቻቻንን ትስስር አጉልቶ የሚያሳይ የጋራ ጸጋና ህዝባዊ በረከት እንጂ የምንጣላበት፣ እንደ አላቂ ሃብት በድርሻ- ድርሻ የምንካፈለው አይደለም። ይህ አስደሳችና አስዳናቂ ባህል፣ የሰሜን የሀገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ህዝቦች፤ የኢትየዮጵያውያንም ብቻ ሳይሆን የአለም ሀብትና ቅርስ መሆን እንዲችል በአለም በማይዳሰስ ሀብትነት እንደሚዘገብ አጥብቀን መስራት ይኖርብናል።

በአሉን የምናከብረውና የምንንከባከብው የውጭ ሃገር ቱሪስቶችን ለመሳብ፣ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን ራሳችንን፣ ክብራችንን፣ ታረካዊ እሴቶቻቸንንና በልዩነቶቻቸን ውስጥ ያለውን የማይናወጥ አንድነት ለማሳየት ነው። ነገር ግን ይህንን ማድረግ የሚቻለው እና አሴቶቻቸንን ከራሳችን አሳልፈን የአለም ማድረግ የምንችለው በዋናነት ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር ሲኖርና ተደምረን ጠንካራ ህዝቦች ስንሆን ብቻ ነው።

ስለሆነም ልክ እንደ ባህላዊ እሴቶቻችንና በኣላቶቻችን ሰላማችንን፣ ሃገራዊና አንድነታችንን እና አብሮነታችንን ልንንከባከብ፣ ልናጎለብት እና አጥብቅን ልንጠብቅ ይገባል።

ለሁላችንም መልካም የአሸንዳ/ ሻደይ በዓል እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ

Filed in: Amharic