>

'ለምን' የማያውቅ ትውልድ ነፃነትን ሲለምን ይኖራል  (አንተንሳይ መስፍን)

‘ለምን’ የማያውቅ ትውልድ ነፃነትን ሲለምን ይኖራል
አንተንሳይ መስፍን

ዛሬም ችግር አለ። ዛሬም እንደ እስከዛሬው ችግሩ ችግሩን አለማወቅ ነው። አሁንም ችግሩ እውነተኛውን ጠላት ያለመለየት ነው። አሁንም ችግሩን ለመፍታት እየታገልን ያለነው በራሱ በችግሩ ነው። ከህልውና ጋ በተቆራኘው ፖለቲካዊ ስንክሳር፥ እሾህን በእሾህ ትርፉ የነጭ ሽብርን በቀይ ሽብር አይነት የዕውር ድንብር ዕልቂት ነው።

አሁንም የምንራገጠው በተሠጠችን ጠባብ የዘረኝነት ሜዳ ላይ ነው ። አሁንም ኳሱ ምኒልክ ነው። አሁንም ዳኞቹ ና አራጋቢዎቹ የጥንቶቹ ናቸው። ትልቁ ተቃርኖ ግን ለኛ አሁንም ጨዋታው አዲስ መምሠሉ ነው፤ ከቆየው ታሪክ ይቅርና ትናንትና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ዋና ሹም ከተናዘዙት እንኳ ለመማር ”አካሲ” ? ብለን ፋታ ወስደን አለማሠባችን ነው። እንኳን ‘ለምን’ ‘እንዴት’ ብሎ በመመርመር ማሠብ ይቅርና በአንዳንድ ቦታዎች የሚፈፀሙ ነገሮችን ላየ፥ ከናካቴው ማሠብ መቻላችንን ጥያቄ ውስጥ ይከትታል።

የሠሞኑ የሻሸመኔዎቹ ራምቦዎች ዓይነቶቹ ደግሞ እንኳን ስለህልውናቸው ‘ለምን’ ብለው እሚጠይቁበት፤ ልብሳቸውን እንደ ወጉ የሚለብሱበት ወይም ምግብ አስተካክለው በእጃቸው የሚጎርሱበት ማሠቢያ መኖራቸው ትንግርት ነው የሚመስለው።

ሌሎቻችንም ከነሱ እንሻል እንደሆነ እንጂ ብዙ አንርቃቸውም። ዘረኝነት ማንቁርታችንን ይዞ ሊያፈርጠን በተሠናዳበት በዚህ ሠዓት ዛሬም እንደትናንቱ ‘ለምን አማራ? ‘ ‘ለምን ምኒልክ?’ ብለን ጥቂት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተትረፈረፈን ጊዜ ቅንጣቷን እንኳን ወስደን ማሠብ አንፈልግም። ወይንም ማሰብ እንዳንፈልግ ተደርገን ተቃኝተናል ።

ለምንድን ነው የአገራችን ፖለቲካ ከቀደሟቸውም ከተከተሏቸውም መሪዎች በተለየ ሁልጊዜ በምኒልክ ዙሪያ የሚያጠነጥነው?

ለምን?
ኦነግ ቢነሣ -አፈሙዙን በስተ-ምኒልክ አዙሮ፤ ሻዕቢያ ዘራፍ ቢል -አፉን ወደ ምኒልክ አሞጥሙጦ፤ ህወሃት ጫካ ቢሸምቅ -ከንፈሩን ምኒልክ ላይ ነክሶ፤ ሣይበር-ሽፍታዎች ቢያኮርፉ -ለንቦጫቸውን ምኒልክ ላይ ጥለው፤
እንዴት? ለምን? እንዴት ?

ይኼ፥ ዘር ጠቅሶ የሶሎሞን እንጂ ወገን ጠቅሶ የእገሌ ነኝ፤ አገር ጠርቶ የኢትዮጵያ እንጂ ብሔር ጠርቶ የአማራ ነኝ ብሎ የማያውቅ ሠው፧ እንዴት የሁሉም የዘረኝነት ቁማርተኞች ገበታ ይሆናል?

ለምን?
ወገንተኛም፣ ጠላትም፣ ገለልተኛም የታሪክ ፀሃፍት በዘመኑ የብዙዎች ወዳጅ መሆኑን የመሠከሩለት ይኽ ሠው ዘመኑ ካለፈ በኋላ ለምን የሁሉ ጠላት ሆነ?

‘ለምን?’ ማለት ዳገት ካልሆነብን መርዙ ከሁለተኛው የጣልያን ሽንፈት በኋላ መነስነስ እንደጀመረ እናያለን። በተለይ የዘውድ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት ላይ። ይኸ ወቅት ዳግማዊ ምኒልክ ከአድዋ ያስነሣው የእምቢኝ አልገዛም አውሎ ንፋስ ቅኝ አገዛዝን ዳግመኛ አማራጭ እንዳይሆን አንኮታኩቶት አብዛኞቹ ተገዢዎች በባዕድ ፊርማ ከመገዛት የተላቀቁበት ነበር።

ቅኝ ግዛትን በወሬ በወሬ ብቻ ስትሰማ የከረመችው አገራችን ደግሞ እንደ ኦነግ፣ ጀብሃ፣ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ)፣ ማገብት፥ ብዙም ሣይዘገይ ህወሃት እና ሌሎችም ቋንቋንና ጎጥን መሠረት ያደረጉ ”ነፃ አውጭዎች” ብቅ አሉ ። (ከነዚህ መሃል ህወሃት ኩርፊያውን በደርግ አረመኔያዊ አገዛዝ ቢያመኻኝም፤ የተመሠረተው ግን፧ ደርግ እንኳን ለአቅመ ግፍ – ለአቅመ መንግስት ባልደረሰበት ዓመት መሆኑ ና በወቅቱ የነደፈው ፕሮግራም እና ስያሜው ግን ትግሉ ለትግራይ ‘ሀርነት’ እንደሆነ ግልፅ እንደሚያደርግ ልብ ይሏል ።)

በሌላ በኩል ደግሞ በነዚሁ የፍፃሜ ዘውድ ዋዜማ አመታት በሠሜን አሜሪካ ና አውሮፓ የነበሩ ወጣት ተማሪዎች፤ በሚደንቅ ተቃርኖ፤ ያስጠጓቸው አገራት ለእራሳቸው በቀዝቃዛው ጦርነት በጥብቅ የሚዋጉትን የሶሻሊስት ርዕዮት አገልግል እንደዋዛ ለወስ ከተደረገች የብሔር አዋዜ ጋር በቀጥታ አጥቅሰው ና በእጅ አዙር አስጠቅሰው ወደ አገራቸው ሠደዷቸው።

እስኪ ‘ለምን’ ና ‘እንዴት’ እንበል እንደገና ለምን?
እስከ ዛሬም ለነበረው፧ ምናልባትም ለወደፊት ለሚመጣው የሚያስቀናው ያ እጅግ ንቁ ና መርማሪ ትውልድ ለምን ባገራችን የተገመደ የብሔር ይዘት ዉሃ የማያነሣውን የዘረኝነት ሊጥ አብኩተው ጋገረ? እንዴት?
ከኦሮሞና ከአማራ፣ ከትግራይና ከኤርትራ፣ ከጉራጌና ከወላይታ፣ ከወዘተ ና ከወዘተ ፤ እናትና አባት የተወለዱ ልጆች እንዴት የብሔር ፖለቲካ አንግበው መሪ ሆነው ፋኖ ተሠማሩ? እንዴት ሽምቅ ገቡ?
ለምን ና እንዴት?
“ማርታ ለምን ለምን ሞተች? -ዋለለኝ ለምን ለምን ሞተ?”ን የዘመሩ፤ መፅሀፍትን በትነው፣ አንቀፅን በልተው፣ ቃላትን ሰንጥቀው የሚሞግቱ ልጆች: ካፒታሊስቶች ሶሻሊዝምን የሙጢኝ ብለው አብዮት እንዲያፈነዱ “ሲያነቋቸው” ና ሲያስታጥቋቸው ‘ለምን’ የምትል ሶስት ፊደል እንዴት ከበደቻቸው?
በህብራዊነት የተጋገረች አገራቸው ላይ ይኼን ብላ ብለው የብሔርተኝነት ዱቄት ሲሰፍሩለት እንዴት ዝም ብሎ አቁማዳውን ይዞ ኮተት እያለ ተጠጋ? ዘረኝነት እንደሽንኩርት ስትለጠው ከስር ሌላ ሽፋል አለው።

የብሔሩን ሽፋል ዛሬ ብትለጠው ከውስጥ የጎሳ ሽፋል ብቅ ይላል፤ እሱን ብትልጠው የጎጥ ይጠብቅሃል። ሽንኩርት ደግሞ በላጥከው ቁጥር ይበልጥ እየለበለበህ ነው የሚሄደው። በተለይ ህቡዕ ባለአጀንዳ እና ቦናፓርቲያዊ ግለሠቦች ከተመሠጡበት መጨረሻው የት እንደሚሆን የሚያውቀው አንድ ሰይጣን ብቻ ነው። ከእግዜርማ፧ ገና ሠው በወገን በወገን ስትሸነሽን ተለይተሃል። ዛሬ ለእኛ የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ የሠጡን ሃገራት አውራ የሆነችው ሀገር ፤ ከየአቅጣጫው ተሠብስበው የተቀየጡ ህዝቦች ድምር ነች። አማራጭ እንደሌለውም ስለምታውቅ፤ የብዝሃነትን ስብ አጣጥማ እየመጠጠች ዛሬም መደመርን አልጠገበች። ዘረኛም ይሁን ሠውኛ መሪ ብትሾምም ብዝሃነቷን የመፈታተን ዕድል አትሰጠውም። ምክንያቱም ህዝቧ ‘ለምን’ ስለሚል።

ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ
ለእኔ መነጣጠልን ስታስታቅፈኝ “ለአንቺ ለጠብደሏ የከበደሽን ዳውላ ለኔ ለውስቢሮው ለምን ታሸክሚኛለሽ?”
የማልላት ? ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ አምባገነን መሪዎችን በይፋ እያወገዘች ፤ እነርሡኑ በአደባባይ በገንዘብና በሙያ ስትደግፍ እያየሁ ከጎኔ ነች ብዬ የማስበው? ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ ዲሞክራሲን አፈር ግጠው እጃቸው ያስገቡን እንደ ቦሊቪያ ና ዛምቢያን የመሠሉ አገራት በሰዓታት ዘመቻ እጓዳቸው ገብታ ወደ ነበሩበት አፈር ድሜ ስትመልሳቸው እያየሁ፤ ለኔ ነፃነት ትቀረቆራለች ብዬ የምገምተው? ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ የሠው ልጅ በቆዳው ቀለም ብቻ ተለይቶ የውሻ ጥርስ መሞረጃ እስከመሆን የደረሰበትን የአፓርታይድ ስርዐት ለይስሙላ እያወገዘች በአሾገር ትንከባከብ የነበረች አገር ፤ እንዴት ነው የኔ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ይከነክናታል ብዬ የምገምተው? ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እሳት አጥሯ ጥግ እስኪደርስ ድረስ ናዚ ጀርመንን በትጥቅና በስንቅ እያደረጀች ሂትለርን ስታፍለቀልቅ የነበረች አገር ለኔ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ስታለቅስ የማምናት?bይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴbየዘረኛውም ፣ የዲሞክራሲያዊ ብሔርተኛውም ፣ የሥልጣን ጥመኛውም እጅ አንድ ምኒልክ ላይ ሲቀሰር ‘ለምን’ ብዬ የማልመረምረው? ይኼን ያህል ሞኝ ነኝ እንዴ
አንድ ለእግሩ ጫማ ያልነበረው ንጉስ በዚህ ሁሉ ብሔር ላይ ‘ግፍ’ ሠርቶ ፤ ከኛ በመለስ ያለው ጥቁሩ፣ አረቡ፣ ሞንጎሉ፣ላቲኑ ፣ ወዘተው የሚቁለጨለጭበትን ከየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚያንፀባርቅ የነፃነት ህንፃ፧ ትኋኑ በተራገፈ ጋሻ ና የደጅ መሸጎሪያ ሆኖ በከረመ ጦር ብቻ አድዋ ላይ እንዴት ሊገነባ ቻለ ብዬ የማልጠይቀው?
ምን ያህል ብንታወር ነውvበአሉላ አባ ነጋ ገድል እየተኩራራን፤ ትግሬ ላይ ጣት የምንቀስረው ? ምን ያህል ብንደነቁር ነውvበፊታውራሪ ገበየሁ ኤታማዦርነትና ምኒልክ በብዛቱም በጥራቱም በሚመኩበት የኦሮሞ ፈረሰኛ ጦር (ገበየሁ ከወደቀ በኋላ የወሎው ራስ ሚካኤል በመሩት) የላቀ ድርሻ ድል የነሣንበትን ጦርነት እያቅራራንበት በኦሮሞ የምንዘባበተው?
ምን ያህል ብንደነዝዝ ነው
በአባ መላ ሀብቴ የጦርና የዲፕሎማሲ ብስለት ተደግፈን ከጭራቅ ቅኝ ገዢዎች የብልጣብልጥ ‘አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ’ የባርነት ወጥመድ ስንቴ እንዳመለጥን እያወቅን በጉራጌ የምንሳለቀው?
ምን ያህል ብንሸነገል ነው

ዛሬ ቋፍ ላይ ያንሸራተትነው ህብራዊነት አገራችን እስከወዲያኛው ልትውለሸለሽ ባለችበት የመሣፍንት ዘመን ፤ በተለይ ከአማራ ከኦሮሞ ከትግሬና ከሌላውም ብሔር ድር ሸምና ጎንደር ላይ ኢትዮጵያዊነትን የሸመነችው አርቆ አስተዋይዋ እቴጌ ምንትዋብ እንደሆነች እያወቅን፤ አማራን የምናብጠለጥለው?

ማሠብ ከቻልን
በተቃርኖ ማመሣከሪያ (proof by contradicton) ሚኒልክን ማብጠልጠል የፖለቲካ አጀንዳው የመጀመሪያ ገፅ ላይ የከተበ ድርጅትም ሆነ ግለሠብ ዐብይ ጥያቄው መገንጠል ከሆነ ምኒልክ ማለት ህብረት መሆን አለበት።
አሁንም ማሠብ ከቻልን ዘረኝነት የተሠጠን እንጂ የተወለደን አይደለም። እንኳን ዘረኝነት ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይሏት ነገር ራሷ ቅዱስ ሠይጣንነት የሚባል አይነት ትርጉምአልባ ሐረግ ናት።
አሁንም ሀገራችንን ፥ በሀገራችንም ራሳችንን ለማዳን አልረፈደ እንደሆን ፤ የተገራ ዲሞክራሲ እያራመድን ነው የሚሉ ወዳድል አገራት “የደገፉት” ና ሁለት ሦስት ትውልድ የበላው የትጥቅ ትግል ለ'”ድል'” ካበቃን በኋላ የነሡ “ድጋፍ” እና ሙገሣ ሳይለየን እስካሁን ግን የዲሞክራሲን ገንፎ ማሽተት እንጂ ማጣጣም አለመቻላችን ‘ለምን?’ ለማለትና እውነተኛው ጠላታችንን ለመለየት ቀላል ነው።
ያልተጠየቀ ጥያቄ መልስ አይኖረውም እንጂ፤ መልሱ ቀላል ነው። በተለመነ ፖለቲካ የግለሰብ ከርስ እንጂ የብዙሃን አገር አትሞላም ።
ለዚህም ነው በተማመንባቸው መሪዎች እንኳ ያልጠበቅናቸው ና መልስ የማናገኝላቸው ዘግናኝ እንከኖች የምናገኘው። ዘዋሪው ከግቢ ውጭ ስለሆነ።
ስግብግቡ የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሲበሰብስ እና በአዲስ እና የተጠናከረ ሌላ ስግብግብ ስርዐት ሲተካ፤ የጥቅም ግጭት ተፈጥሮአዊ ህግ ያስገድደዋልና ፤ መጀመሪያ መደለዝ ያለበት የቀደመውን ስርዓት ወዳበሰበሰው አካል ነው ። – – -ዳግማዊ ምኒልክ ልደታቸው ሲታሰብ ይኖራል። እንኳንም ተወለዱ፤ እምዬ።
Filed in: Amharic