>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1933

የምናውቀውን አብይ እንፈልጋለን!  (መስፍን ማሞ ተሰማ)

የምናውቀውን አብይ እንፈልጋለን!

 መስፍን ማሞ ተሰማ

“ህልም በሥራ ብዛት ይታያል። እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል”

“ብዙ ህልም ባለበት ዘንድ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ሥፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ።” መፅሀፈ መክብብ ምዕ 5 ቁጥር 3 እና 7

አስቀድሞ ቃል ተነገረ፤ ቃሉም የአብይ ነበረ፤ ቃሉም ኢትዮጵያዊነትን ከወደቀበት ማንሳት ነበረ፤ ቃሉም በእኛ ዘንድ ህያው ሆነ፤ እነሆ ኢትዮጵያዊነትን ከመሪዋ ጎን ቆመን ከፍ አደረግን፤ ከአፅናፍ አፅናፍ ሆ! ብለን ተነሳን፤ በያደባባዩ ተመምን፤ መሪያችንን አብይን እንደ ጨው በተበተንባት ምድር ሁሉ ስሙን ጠራን፤ እነሆ ኢትዮጵያ መሪዋን ሙሴን አገኘች ስንል ብሥራት ተናገርን፤ እርሱም አላሳፈረንም፤ ሙሴነቱን እጃችንን ይዞን አቅፎንና ስሞን እንባችንንም አብሶና ደሙንም ለግሶን አልቅሶና አንሰቅስቆን ከሰቆቃና ከግርፋት ከእስርና ከስደት ነፃ አውጥቶን ወደ ነገይቷ ኢትዮጵያ መንገድ በመደመር ጉዞ መጋቢት 24 ቀን 2010 አስጀምሮን እስከ ሐምሌ መገባደጃው ከጎናችን ለቅፅበት ሳይጠፋ፤ ስንጀግን እየተደሰተ፤ ስናጠፋ እየወቀሰ፤ ስናኮርፍ እየመከረ፤ ስንበድል ይቅር እያለ፤ ወደ ሁዋላ ስናፈገፍግ እያበረታን፤ ስንቃወመውም እያዳመጠን ማዕበሉን እየቀዘፈና ባሻገርም እየተመለከተ ከጎናችንና ከፊታችን ከቶም ሳናጣውና ሳይጠፋብን ሳይርቀንና ሳንራራቅ መራን። ለአራት ወር ገደማ የምናውቀውና የሚያውቀን አብይ መሪያችን ይህ ነው።

ከእኛ ጋር ለመነጋገር፤ ችግራችንን ለመስማት በደላችንን ለመጋራት፤ ሀዘናችንን ለማፅናናት የምናውቀው መሪያችን አብይ ቀጠሮ አይዝም። ሀገር ስትታመስ፤ ገንጣይ ሲረባረብ፤  የዕምነት ቤቶች ሲጋዩ፤ ቀሳውስት ሲፈጁ፤ የሚወደው ህዝብ በጭንቅ ማጥ ውስጥ ገብቶ ሲዳክር፤ መውጫ መግቢያው ሲጨንቀው የምናውቀው አብይ ዝም አይልም። የምናውቀው አብይ ከተፎ ነው። በፈገግታ በታጀበ ፊቱ ፍካትን ፍቅርንና መቻቻልን እየናኘ፤ እንደ ሌሊት ተወርዋሪ ኮከብ በሚበራው አይኑ ብርሃንን ተስፋንና ዕምነትን እያሳየ አቧራ የቃመ ፀጉራችንን፤ እድፍ የተሸከመ ልብሳችንን የሻከረ እጃችንን ሳይጠየፍ የሚዳስሰን ሳይቀፈው የሚያቅፈንና የሚጨብጠን የምናውቀው ሙሴያችን አብይ መሪያችን የሩቅ ሰው ከሆነብን ሰነበተ። የምናውቀው አብይ መሪያችን የቅርብ እሩቅ ሆነብን። ብዙ መናገር ወይም ብዙ መፃፍ በወደድን። ሆኖም አሁን ላይ የኢትዮጵያን ህመም በብዕር ምጥ በቃላት ንግግርም ለዘመናት ሲያስተጋቡ የኖሩ ‘የታወቀ’ ስም ወይም የፖለቲካ ድርጅት ሥልጣን የሌላቸው ከመፃፍም ሆነ ከመናገርም ለመታቀብ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ እኛም የዚሁ አካል ነንና ከዚህ በላይ ብዙም አንል። የኢትዮጵያ ጭንቅ የሚያስጨንቀው ሁሉ ግና ይገባዋልና እንግባባለን።

ይህ የመደመር ጉዞ ጠቢቡ መክብብ ‘ብዙ ቃል ባለበት ሥፍራ ብዙ ከንቱ ነገር አለ’ እንዳለው ዛሬ በኢትዮጵያችን በተለይም አብያችን ከአሜሪካ ጉዞው ከተመለስ ወዲህ  አብይ በሌለበት ምድሪቱ በብዙ ከንቱና አብያዊ ጉዟችንን በሚያጨናግፉ ዲስኩሮችና የድል አጥቢያ አርበኝነት አባዜ ተወርራለች። ከቦሌ እስከ ሚለንየም አዳራሽ የሚሰማው ፉከራና ትርምስ አስደንግጦናል። የሁሉም ተቃዋሚ ‘ተፎካካሪ’ ድርጅት/ፓርቲ ዝግጅት ለዚህ ከቦሌ እስከ ሚለንየም አዳራሽ ለሚደረግ የአቀባበልና የዲስኩር ‘ገድል’ ሆኗልና ወይም ይመስላልና። ኢትዮጵያንና አብይን እንዴት ‘እንታደግ?’ የሚል ዝግጅትና መንፈስ የውይይትና የተግባር መድረክም አይታይም። ሁሉም ለየራሱ ገድልና ታሪክ ጥድፊያ ላይ ነው!! ከወዲያ ማዶም ነጋሪቱ ከጥቂት ወራት በፊት ባልታየ ድምፀት በህወሃት አጋፋሪዎች እየተጎሰመብንና እየተፎከረብን ይገኛል። በዚህ ሁሉ ሆያሆዬ የምናውቀው አብይ ከጎናችን የለም። አለ ብለው ከቤተመንግሥት በአፈቀላጤዎቹ በኩል (እንደ በፊቱ በቀጥታ አይደለም) የሚያሳዩን የፎቶ ምስሉን እንጂ የምናውቀውንና የሚያውቀንን አብረን የተጓዝነውን ሰዋዊውን አብይ መሪያችንን አብይ ወንድማችንን አብይ ልጃችንን አይደለም።

እኛ ቀቢፀ ተስፈኞች አይደለንም። በሃያ ሰባት አመት የስደትና የፅናት ዘመን፤ ለአንዲትም ደቂቃ ለህወሃትና ህወሃታውያን ለጎጠኞችና ለሀገር በታኞች አጎብድደን አልያም ተመሳስለን ኖረን አናውቅም። የሴራ ፖለቲካም የእኛ ቁማር አይደለም። አብይን የደገፍነው ጎርፉ ሲያስገመግምም አይደለም። ‘አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’ እንዲሉ እኒያ አብናቶቻችን የለማንና የአብይን ጉዞ ገና ከጠዋቱ በአደባባይ የደገፍነው አያያዝና አካሄዱን ለይተንና አይተን  የህወሃትን ‘ጭብጦ’ (ሥልጣን) ለመንጠቅም ብቸኛው መንገድ የእነርሱ መሆኑን ተረድተን እንጂ። እና እኛ ሴረኞች ወይም የሴራ ፖለቲካ አራማጆች አይደለንም። በነፈሰበትም አንወዛወዝም። ግን ደግሞ ሰሞኑን ከምኒሊክ ቤተ መንግሥት የሚተላለፈውን ‘ድብብቆሽ’ ለማወቅና ለመረዳት ደግሞ የህይወት ተሞክሮ ብቻ በቂ ነው። ከዚህ በላይ ብዙ ማለት አያሻንም። እና ድብብቆሹ ይብቃ!!! አብይ ናፍቆናል!! የምናውቀውን አብይ ማግኘትና ማነጋገር እንፈልጋለን!!! ወደ ጨለማው ዘመን እንዳንመለስ ከተፈለገ አብይ፤ የምናውቀው አብይ፤ በነፃነት የሚፍለቀለቀው አብይ አደባባይ ወጥቶ እንዲመራንና ከጎኑም እንድንቆም በነፃነት ልናገኘው እንፈልጋለን!!! የሚሰማ ጆሮ የሚያስተውል ልብ ያለው ይስማ ያስተውልም!! ጊዜው ሳይሄድ ምልሽ እንፈልጋለንና!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!

ነሀሴ 2010 ዓ/ም

ኦገስት 2018

ሲድኒ አውስትራሊያ       

mmtessema@gmail.com

 

Filed in: Amharic