>

የሐረሬ ክልልነት- “ከብሔር መርጦ ለክልል” (ውብሸት ሙላት)

የሐረሬ ክልልነት- “ከብሔር መርጦ ለክልል”
ውብሸት ሙላት
የሐረሬ ክልል ሕገ መንግሥት ሊሻሻል እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ምን ምን ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ ይፋ አልሆነም፡፡ መሻሻል ስለሚገባቸው አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ስለ ክልሉ አከላለል የተወሰኑ ነጥቦችን መመልከቱ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ለመረዳት ይጠቅማል፡፡
የሐረሬ ክልል የተመሠረተበት ሁኔታ ነው፡፡ የሐረር ክልልነት ለብዙዎች ግራ ነው፡፡ ስለሐረር የጻፉ አብዝሃኛዎቹ የሐረር ጉዳይ ግራ አጋቢ እንደሆነ በመግለጽ ያልፉታል፡፡ የአመሠራረት ታሪኩን ስናይ በሕዝብ ብዛት አይሉት በ1999 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንኳን የክልሉ አጠቃለይ ሕዝብ 200,000 አይሞላም፡፡ ከዚህ ውስጥ የሐረሪ ብሔረሰብ አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ 32,000 አካባቢ ሲሆን በክልሉ የሚኖረው ወደ 16,000 የሚጠጋው ብቻ ነው፡፡
በዚህ ክልል ውስጥ 103,000 ኦሮሞና 42,000  አማራ እያንዳንዳቸው ከ7,000 የማያንስ ሶማሌና ጉራጌዎች ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ከ40 በላይ የሚሆኑ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሐረሬዎች የበለጠ የሕዝብ ብዛት እያላቸው፣ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ልዩ ወረዳ ወይንም ዞን መመሥረት እንኳን ሳይችሉ ሐረሬዎች ግን ክልል መሥርተዋል፡፡
በእርግጥ የተለያዩ ግምቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሐረር በኦሮሚያ ክልል የተከበበች ነች፡፡ ሐረር ክልል ካልሆነች ቀሪው አማራጭ በኦሮሚያ ክልል ሥር መጠቃለል ነው፡፡ በኦሮሚያ ሥር ለመጠቃለል ደግሞ ሐረሮች መስማማት መቻል አለባቸው፡፡ ከዚያ በትግራይ ወይም በአማራ ክልል ውስጥ እንደሚገኙት ብሔረሰቦች ይሆናሉ፡፡ እንደትግራይ ክልል ከሆነ ልዩ ዞን ወይም፤ልዩ ወረዳ ሳይኖራቸው፣ እንደአማራ ክልል ከሆነ ደግሞ ወይ ልዩ ዞን ወይም ልዩ ወረዳ ኖሯቸው ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ሥር ሆኖ መቀጠል ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከሌላው ብሔረሰብ በተለዬ ሁኔታ ከሌላ ብሔር ጋር ሳይዋሃዱና ሳይቀላቀሉ የተለዬ ማንነታቸውን ይዘው የቆዩ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ከታሪክ አንጻርም ቢታይ የጆገል ግንብ የተገነባው ከጠላቶቻቸው ለመከላከል ጭምር ነው፡፡ ጆገል ሲገነባ የሐረሮች በኦሮሞና በሌሎች ሕዝቦች ከመዋጥ ራሳቸውን ለመጠበቅ ጭምር ስለነበር በአንድነት በአንድ ክልል አብሮ ለመኖር የሐረሬዎች ዝግጁነት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
በተለይም ልዩነታቸውን ጠብቀው የማስቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት ካለና በሌላ ክልል ውስጥ ካለው ኅብረተሰብ ጋር በመቀላቀል ለመኖር ፍቃደኝነቱ ከሌለ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥትና ከእሱ በፊት በነበረው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት የብቻ ክልል መመሥረቱ አማራጭ የለውም፡፡
ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው የተለዬ አስተዳደር መኖር፣ የታወቀ የመሬት ይዞታ ያለቸው መሆኑ የብቻቸው ክልል የመመሥረት መብታቸው ቢጠበቅና ቢተገበር ከብዙ ጣጣ ሊታደግ ይችላል፡፡ እነሲዳማና ሌሎችም ብሔሮች ክልልነት ህልም ሆኖባቸው መቅረቱን ስናይ ደግሞ እውነትም ‘ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከብሔር መርጦ ለክልልነት’ ብንል ተገቢነቱ ያነሰ አይመስለኝም፡፡
መሻሻል ስላለባቸው፣ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጾች
ማሻሻያ -አንድ– መግቢያውና የሥራ ቋንቋ
የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥትን መግቢያውን አንብቡት፡፡ ዓመተ ምህረት ሳይቀር በመጥቀስ ማን በደል እንደፈጸመበት ይናገራል፡፡ አሁንም ቢሆን ያ ድርጊት በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚህ መልክ ዓመተ ምህረት ሳይቀር ገልጾ እንዲህ ሆነን ነበር የሚል ሕገ መንግሥት በሌሎች ክልሎች ላይ እንኳን አይገኝም፡፡
በመግቢያው መረዳት እንደሚቻለው፣በተግባርም እንደሆነው፣የክልሉ ባለቤት የሐረሪ ብሔረሰብ ነው፡ ፡ ኦሮሞ በሁለተኛ ደረጃነት ይከተላል፡፡ በሕዝብ ቁጥር አንጻር ግን ቀደማው ኦሮሞ ሲሆን አማራ ይከተላል፡፡ ሐረሪ ሦስተኛ ነው፡፡ ሌሎቹ ብሔረሰቦች በአንድነት ሲደመሩ ደግሞ ከሐረሪ ይበዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከመግቢያው የምንረዳው ሁሉ ነገር የሐረሪ፣ኦሮሞ በተወሰነ መልኩ የሐረሪ ወዳጅ ወይም አጋዥ እንደሆነ ነው፡፡ ሌሎቹን ብዙም አያካትትም፡፡ ይህ ዓይነቱ ደረጃ ያበጀ መግቢያ ግጭትና ውጥረት ከመጥራት በስተቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ስድስት ላይ እንደተገለጸው የክልሉ የሥራ ቋንቋዎች ሐረሪና ኦሮምኛ ናቸው፡፡ በእርግጥ ሁለት የሥራ ቋንቋዎችን ከመተግበር አንጻር በአገራችን ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከሐረሪ ወደ ሦስት እጥፍ የሚሆን ቁጥር አማራ እየኖረ አማርኛን ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ አለማድረግ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ የፌደራሉ የሥራ ቋንቋ ስለሆነ ብዙም ወጭ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ሕገ መንግሥቱ በሦስት ቋንቋ ነው የሚታተመው፡፡ ከሐረሪ እና ኦሮምኛ በተጨማሪም በአማርኛ፡፡ በሁለቱ የሥራ ቋንቋዎች በታተሙት የሕገ መንግሥት ቅጂዎች መካከል  ልዩነት ካለ ተቀባይነት የሚኖረው የአማርኛው ነው፡፡ ይህ አንቀጽ 80 ላይ ተገልጿል፡፡
በክልሉ በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አማራን ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ወይም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ተጨማሪ በነገራችን ላይ፣ክልሉ በዚህ መልክ እንዲተዳደር፣አማራም ከክልሉ እንዲገለል በፊታውራሪነት ከተሳተፉት መካከል አንዱ አቶ ታምራት ላይኔ ናቸው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ የሚፈልግ ከሐረር መረጃ መሰብሰብ ይችላል፡፡ እኔ የዛሬ ሁለት ወር ተኩል ገደማ ሐረር ሄጄ የተረዳሁት የሄንኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ እሱም የክልል ሕገ መንግሥቶች ተጽፈው ወደ ክልል የሚላኩት ከአዲስ አበባ መሆኑ ነው፡፡ የክልሉ ነዋሪዎች የመከሩባቸው አይደሉም፡፡ ነዋሪዎቹ ይቅርና የክልሎቹ ምክር ቤቶች ጊዜ ወስደው የመከሩባቸው አይደሉም፡፡  አዲስ አበባ ላይ ይጻፋሉ፤ክልል ምከር ቤት ሄደው ይጸድቃሉ፡፡
 እኔ በክልል ምክር ቤት ሳይጸድቁ፣ ቁጥር ሳይሰጣቸው በእጄ የገቡ ሕገ መንግሥቶች አሉ፤በ1987 የወጡት ሳይሆኑ ኋላ ላይ ከ1994 ጀምረው የተሻሻሉት፡፡ ስለሆነም የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥትም ሕዝቡ ሌላውን ለማግለል ሆነ ብሎ ያደረገው ነው ማለት አይቻልም፡፡ ውጥረትና ግጭትን የሚፈለጉ ሕገ መንግሥት ጸሐፊዎች ያደረጉት እንጂ፡፡ ስለሆነም የሐረሪ ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ ከግምት በማስገባት መግቢያውንና የክልሉን የሥራ ቋንቋ ያሻሻለዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ማሻሻሉ ለሁሉም እጅግ ይጠቅማል፡፡
ሌሎች መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ይቀጥላል…
Filed in: Amharic