>
5:13 pm - Thursday April 19, 2745

መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታ አለበት ለዚህም ህብረተሰቡ ሊተባበር ይገባል – አቶ ለማ መገርሳ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦነግ ስም ያለግንባሩ እውቅና ዝርፊያና ህገ ወጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው መረጋገጡን የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አስታወቁ።

ከግንባሩ አመራሮች ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ በተደረገ ምክክር እየተፈፀመ ያለው ህገ ወጥ ተግባር ከእውቅናቸው ውጭ መሆኑን ነግረውናል ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ።

ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አክለውም በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር በአስመራ የተደረሰው እርቅም ውጤታማ ነበር ብለዋል።

ከኦነግ አመራሮች ጋር የተካሄደው ውይይት በኦሮሞ ስም የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ያለምንም ገደብ ወደ ሀገር ገብተው ሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንዲሰሩ በተደረገው ጥሪ መሰረት መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

ይህ የሆነውም የኦሮሞ ህዝብን በሚመለከቱ ታላላቅ አጀንዳዎች ላይ አንድ በመሆን የህዝቡን አንድነት ለማጠናከር መሆኑንም አስታውቀዋል።

አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ታላላቅ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ከስምምነት ተደርሷል ያሉት አቶ ለማ፥ ቀሪ ጥቃቅን ጉዳዮችን ደግሞ በሂደት አብረን እየፈታን ለመሄድ ተስማምተናል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ በዚህ ስምምነት ስም የተለያዩ ስህተቶች እና ወንጀሎች እየተፈፀሙ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገልፀዋል።

ይህ ደግሞ በስምምነቱ መካከል ስለሌለ እንዲህ አይነቱን ወንጀል እና ስህተት እየፈፀሙ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

መንግስትም የህግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታ ስላለበት ህብረተሰቡ ለዚህ አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ምክንያቱ ደግሞ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረሰው ስምምነት በዚህ ምክንያት ሊደናቀፍ ስለማይገባ ነው ብለዋል።

በኦሮሞ ስም መደራጀት ይቻላል ያሉት አቶ ለማ መገርሳ፥ ሆኖም ግን ሰላምን ማደፍረስ ክልክል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

Filed in: Amharic