>
5:13 pm - Sunday April 19, 2663

ኢሕአዴግ ገና አልተደመረም-  ኦነግና ግንቦት 7 ሳይቀድሙት አልቀረም!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኢሕአዴግ ገና አልተደመረም-  ኦነግና ግንቦት 7 ሳይቀድሙት አልቀረም!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
 
ዶ/ር አብይ የሚመሩት የለውጥ ኃይል የአገሪቱን ሙሉ የፖለቲካ ሥልጣን በእጅ አስገብቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ያፈነገጡ ክልሎች እና የገዢው ፓርቲ አባላት ወደ መስመር ካልገቡና ካልተደመሩ፣ የጸጥታና የመከላከያ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ መስራት ካልጀመሩ፣ በየሥፍራው ነውጥን የሚቀሰቅሱ፣ በሰው ሕይወት እና በሕዝብ ንብረት ላይ ውድመት የሚያደርሱ ኃይሎች በሕግ ጥላ ሥር ውለው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ካልተቻለ ለውጡ ግማሽ ብስል ግማሽ ጥሬ ነው የሚሆነው። ሌላው ወሳኝ ነገር በዶ/ር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል እና ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ተጣጥመው ነው ውይ እየሰሩ ያሉት የሚለው ጉዳይ ነው። እንደ እኔ ትዝብት ኢሕአዴግ ገና የተደመረ አይመስለኝም። ኦነግና ግንቦት 7 ሳይቀድሙት አልቀረም። ከሕዝብ ቁጣ ታድገው የሥልጣን እድሜዮን ያራዝሙልኛል ያላቸው ዶ/ር አብይ፣ የአቶ ለማ እና የአቶ ደጉ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር ተውጠው እና በሕዝብ ተፈቅረው ሌላ ደሴት ላይ ያሉ ይመስላል። ሕውኃት ወልዳ እና በባህሪዋ ቀርጻ ያሳደገችው ኢሕአዴግ ደግሞ ሌላ ደሴት ላይ ያለ ይመስላል።
ነገሩ እንዲህ ከሆነ የሰሞኑ የዶ/ር አብይም ከሕዝባዊ መድረኮች መሰወር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። አብዛኛዎቹ የዶ/ር አብይ የአደባባይ ንግግሮች፣ የፖለቲካ አስተሳሰባቸው እና ከሕዝብ ጋር እየፈጠሩት ያለው ግንኙነት በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር የሚታሰቡ አይመስሉም። ኢሕአዴግ የዶ/ር አብይን ራዕይም ሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመሸከም የሚያስችል ቁመና ያለው አይመስለኝም። ስለዚህ ድርጅቱ ለራሱ ህልውና ሲል ዶ/ር አብይ የሚነዱትን አዲስ የለውጥ ባቡር መቆጣጠርና ማስቆም ባይችል እንኳ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ዶ/ር አብይን ማርሽ ቀንስ ማለቱ አይቀርም። ዞሮ ዞሮ ሕዝብ ከዶ/ር አብይ ጎን እስከቆመ እና ሌሎቹንም የኃይል ምንጮች በአግባቡና በጥንቃቄ እስከተጠቀሙባቸው ድረስ ባቡሩ ፍጥነቱ ቢቀንስም ወደፊት መሄዱን ግን ማንም ሊያስቆመው አይችልም።
Filed in: Amharic