>

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ ልኡክ ወደ አማራ ክልል ሊመጣ ነው (ኤፍ.ቢ.ሲ)

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አማራ ክልል

ሙለታ መንገሻ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ የልኡካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንደሚመጣ ተገለፀ።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የሚመሩት ልኡክ በአስመራ ይገኛል።

በቆይታቸውም አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ ከአቶ የማነ ገብረአብ ጋር የኤርትራውያንንና የኢትዮጵያዊውያንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ላይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት በቅርቡ በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ እንዲጓዝ መስማማታቸውንም አቶ ንጉሱ ገልፀዋል።

እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲሚመጣ ከስምምነት መድረሳቸውም አቶ ንጉሱ ያስታወቁት።

በአማራ ክልል በተለይም በጎንደርና በባህር ዳር በርካታ ኤርትራውያን ይኖራሉ ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በ2011 ዓ.ም. ከተለያዩ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተለይም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጠንካራና ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማካሄድ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰራም ገልፀዋል።

አቶ ንጉሱ አክለውም በአስመራ ቆይታቸው፥ መቀመጫውን ኤርትራ ያደረገው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ ወደ አማራ ክልል ገብቶ በሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ላይ በመወያየት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።

ከንቅናቄው አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት የአማራን ህዝብ መብት እና ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ ሁኔታ ለመታገል የሚያስችል ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታ መፈጠሩን በመገንዘብ በሰላማዊው መድረክ ለመታገል ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

 

ብ.አ.ዴ. እና አ.ዴ.ኃ.ን ስምምነት ላይ ደረሱ
አማራ መገናኛ ብዙሀን 
በክልሉ መንግስትና በአዴኃን መካከል ሁለተኛው ምዕራፍ የድርድር ውይይት ዛሬ በአስመራ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ከንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች ጋር አንድ ቀን የፈጀ ውይይት መደረጉንና የአማራን ህዝብ ጥቅም እንዲሁም አንድነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
ተጨማሪ ድርድሮችን የሚጠይቁ አንዳንድ ነጥቦች ቢኖሩም  ልዩነቶችን በማቻቻል የክልሉን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ወደፊት በጋራ በሚሰሯቸው ስራዎች ላይም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውም ተገልጿል፡፡
የኤርትራ መንግስሰት ይህንን የውይይት መድረክ በአስመራ እንዲደረግ ላደረገው ቀና ትብብርም የአማራ ክልልን በመወከል የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ.ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአዴኃን ሊቀመንበር ተፈሪ ካሳሁን በበኩላቸው የንቅናቄው ጥያቄ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል መሆኑን ገልጸው ይህ እንዲቀየር ላለፉት 8 ዓመታት በኤርትራ በረሃ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣም ድርጅታቸው የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ንቅናቄው ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራትና ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሱን ነው አቶ ተፈሪ የገለጹት፡፡
ይሁን እንጂ ስምምነቱ የአማራ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ብለን የተስማማነው ሳይሆን የክልል የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እስኪመለሱ ድረስ ከብአዴን ጋር ሆነን በጋራ ለመታገል የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
Filed in: Amharic