>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1092

የጀግኖች ታላቅ አደራ — ለትውልድ !!!  (አሰፋ ሀይሉ)

የጀግኖች ታላቅ አደራ —  ለትውልድ !!!
አሰፋ ሀይሉ
ታሪኩን የሚዘነጋ ትውልድ፣ እንደዘነጋው ታሪክ፣ ከዘመን መዝገብ ይዘነጋል፣ አንድ ቀንም ደብዛው ይጠፋል!!! “Certainly, a people without history shall perish as a people!”
 
እነዚህ ጀግኖች አባቶቻችን ናቸው በባዶ እግራቸው ቆንጥር አሜከላ ሣይበግራቸው በዱር በገደሉ ተንከራትተው… ወጥተው ወርደው… በነፍስ በሥጋ በአጥንት በደም ታላቅን የማይተካ ክቡር መስዋዕትነት፣ ታላቅን ውድ ሕይወታቸውን ከፍለው… ዛሬ የምንቃዥበትን ምድር፣ ዛሬ የምንሸማቀቅበትን ነፃነት በደማቸው ያቆዩልን፡፡ ይህችን ሀገር ሊበትኑ ከመጡባት ጉልበተኞችና ጎምዢዎች ጋር… ለዘመናት ተናንቀው… ለዘመናት ያቆዩልንን ውድና በምንም የማትተካ ክቡር እናት ሀገራችንን… ዛሬ ያንኑ ፍላጎት ላነገቡ ወጠጤዎች መጫወቻ እንድትሆን አሣልፎ መስጠት… ታሪክ ይቅር የማይለው፣ አንገት የሚያሰብር ኃጢያት ነው፡፡
ዛሬ ሀገራችንን እንዳሻቸው ሊያደርጉ የሚፈነጩና የሚንፈራገጡ ታሪክ-የለሾችን ዝም ብሎ ማየት… ሀገርን መጫወቻ ሲያደርጉ እንደበዪ ተመልካች ምንተዳዬ ብሎ ከሩቅ ማየት… ማለት….  ለእነዚህ…. ከዚያችው ደሳሳ ጎጆአቸው በቀር…  ምንም ዋጋ ለውለታቸው ለማትከፍላቸው ለዚህች ሀገር ሲሉ… በባዶ እግራቸው ሀገሩን በዱር በገደል እያሰሱ…. ለትውልድ ነፃነትንና ሀገርን እናወርሳለን ብለው… የሞቱልንን፣ በጦር በጎራዴ የተሰየፉልንን፣ የደሙልንን፣ ላባቸውን ያንጠፈጠፉልንን… እኒህን እጅግ እጅግ እጅግ ትሪሊየን ጊዜ እንኳ ቢሰገድላቸው የማይበቃቸውን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንን ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ የእነዚህን አደራ ቸል ብሎ – ያባት ቤት ሲዘረፍ ዛሬ የበይ ተመልካች ሆኖ መዘባበት – የእነዚህን የነጻነትና የሀገር ትርጉሙ አስቀድሞ የገባቸውን ጀግኖች ቅድመ-አያቶቻችን የከፈሉትን የማይረሳ ታላቅ ሀገራዊ መስዋዕትነት እበት እንደመለቅለቅ ያለ የወራዳ ትውልድ ተግባር ነው፡፡
ይህች ሀገር የእነዚህ ጀግኖች አባቶቻችን፣ የጀግኖች ባለአደራ ልጆቿ ሀገር ነች፡፡ እነዚህ ጀግኖች አባቶቻችን ናቸው ደረታቸውን ለቅኝ ገዢዎች ሰይፍና ጥይት ሰጥተው – ይህቺን ሀገር እና ሕዝቦቿን በነፃነት ያቆዩልን፡፡ ዛሬ ይህ ሁሉ የውለታ ዋጋ የማይገባው ደነዝ ትውልድ፣ የዚህ ታላቅ የህይወት አደራ የማይገባው ነቀዝ ትውልድ፣ ያን ሁሉ አንገታቸውን ሰጥተው እኛ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንራመድ ያስቻሉንን አያት ቅድመአያቶቹን ያደራ ቃል አፈር አስበልቶ – በመጨረሻ የማይቀረው አፈር ይበላዋል!!!
የዚህች ሀገር ቀደምቶች አደራ ውስጡ ዘልቆ የሚሰማው የትኛውም ባለአደራ ትውልድ፣ እነዚህ ምስኪን ጀግኖች አባቶቹ የከፈሉለትን የነፃነት ዋጋ የሚረዳ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ትውልድ፣ ሀገሩን፣ ነጻነቱን፣ ሣሩን ከብቱን ልጆቹን ባንዲራውን ህጉን ሠማይ ምድሩን ሁሉ – እየተነሱ ያሻቸውን የማድረግ መብት ድንገት ከሰማይ የወረደላቸው የሚመስላቸውን – የአባቶቻችን ውድ አደራ እና ከፍለን የማንጨርሰው ውድ የሀገር ዕዳ ያለብን መሆኑን የማይረዱትን – የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ለመሆን የሚቃጣቸውን – በሀገራችን ሉዓላዊነትና በህዝቦች አንድነት ላይ ያን አባቶቻችን የተሰዉለትንና በድል ያጠፉትን የውርደት ካራ ለመምዘዝ የሚዳዳቸውን ወራዳ ትውልዶች – ከምንም በላይ ዛሬ – ነቅቶ መጠበቅና ሀገሩን፣ ሠላሙን፣ ሕብረቱን፣ ባንዲራውን፣ ነፃነቱን – በፈለገው ዓይነት ዋጋ ቢያስከፍል እንኳ – እስከመጨረሻዋ ጠብታ ድረስ – ቃል ለምድር ለሠማይ ብሎ – ለሀገሩ እና ለትውልዱ የኢትዮጵያዊነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
ሀገርን የፈጠሩልን ያሁን ወጠጤዎች አይደሉም፡፡ ነጻነትን ያወረሱን ያሁን ባለጊዜዎች አይደሉም፡፡ ከዘመን ዘመን ተጋድለው እንደሀገር እንደ ሕዝብ ያሸጋገሩን ያሁን አደራቢስ ገባሮች አይደሉም፡፡ ከአባቶቻችን የተረከብናትን ነጻ ሀገር፣ ካያት ከቅድመአያቶቻችን የተረከብናትን ነጻነት፣ ከዘመን ዘመን በተከፈለ ታላቅ ክቡር ዋጋ የተላለፈችልንን ይህቺን የከበረች ሀገራችንን – ማንም አይሰጠንም – ማንም አይነሳንም – ማንምም መጫወቻ ሊያደርጋት ሲመኝና ሲንፈራገጥ – ዝም ብለን እጃችንን አጣጥፈን ከሩቅ አንመለከትም፡፡ ኅበረታችን ሁላችንንም ያገባናል፡፡ ነፃነታችን ሁላችንንም ያገባናል፡፡ ሀገራችን ሁላችንንም ያገባናል፡፡
ነጻነታችን፣ ደህንነታችን፣ ሠላማችን፣ ሉዓላዊነታችን፣ የማንገሰስ የማንደፈር ታላቅ ክብር ያለን የምድሪቱ ኢትዮጵያውያን ፍጥረት መሆናችን ሁላችንንም ይመለከተናል፡፡ ይህችን ሀገራችንን ለዋልጌዎችና ቀማኞች አሳልፈን የሰጠን ዕለት – በታሪክ ለሺህ ትውልድ አንገተ-ሰባራ ገባሮች ብቻ ሆነን እንቀራለን፡፡ ነጻነትን የወደድን፣ ሀገርን የወደድን፣ ከሀገሬ ያስቀድመኝ ያልን ዕለት ደግሞ – የተከበረች፣ የተባበረች፣ ነጻነትና እኩልነት የሰፈነባት፣ እና ምድሪቱን የረገጠ ማንኛውም የሰው ልጅ ሁሉ የሰውነት ክቡር ጸጋው የተረጋገጠባት፣ የነጻነት ምኩራብ ሀገራችንን ለራሳችን ለዛሬ ዘመነኞቹም ማቆየት – አንገቱን ቀና አድርጎ በነጻነት ለሚመላለስ ኢትዮጵያዊ መጪ ትውልድም ማስተላለፍ የምንችል – ኩሩ የነጻነት ባለአደራዎች እንሆናለን!!! የአባቶቻችን ታላቅ አደራ ይክበደን!!! ሀገር ትክበደን!!! ሕዝባችን ይክበደን!!! እና አደራችንን ሸጠን ገባርነትን በምናወርሰው መጪ ትውልዳችን ፊት የሚሰማን የታሪክ ውርደት ይክበደን!!!
ታሪኩን የሚዘነጋ ትውልድ፣ እንደዘነጋው ታሪክ፣ ከዘመን መዝገብ ይዘነጋል፣ አንድ ቀንም ደብዛው ይጠፋል!!! “Certainly, a people without history shall perish as a people!”
ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ለኢትዮጵያ እናት ሀገራችን ጀርባችንን አንስጥ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችንን የሚመለከት ነገር ሁሉ ሁላችንንም ልጆቿን ይመለከተናልና!!! በዚህች የአደራ ምድራችን ላይ ማናችንም ባዳዎች አይደለንም!! አምላክ ልቦናውንና የሀገር ፍቅሩን ይስጠን!! አምላክ አደራ-በላ ትውልድ አያደርገን!!!! እምዬ ኢትዮጵያ ሀገራችን – ከነመላ ጀግኖች ሕዝቦቿ – ከነመጪ ታላላቅ ትውልዶቿ – በፍቅር፣ በአደራ፣ በኅብረት፣ በነጻነት፣ በሙሉ ልቦና፣ በአይበገሬነት ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡
አበቃሁ፡፡
የጀግኖቹ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አበጋዞች አስገራሚ ፎቶግራፍ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
«Chiefs with war adornment, Ethiopia, ca.1951-1952 – Ti Getta saved to Ethio»
Filed in: Amharic