>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3262

''መደመር" እና  የምርኮው ፖለቲካ  (ጌታቸው ሺፈራው) 

”መደመር” እና  የምርኮው ፖለቲካ
 ጌታቸው ሺፈራው
ባለፉት 27 አመታት ከአገዛዙ በተቃራኒ የቆሙ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ። በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያሉ/የነበሩ፣ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የሚታገሉ ቡድኖች ከአገዛዙ ጋር የነበራቸው ልዩነት ሰፊ ነው። ይሁንና ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ከኦነግ ውጭ  ያሉት የፖለቲካ ቡድኖች “ተደምረናል” ብለዋል። ተደምረዋል ሲባል አንድ ከገዥዎቹ ጋር መሰረታዊ ልዩነት ያለው ቡድን  የሚያደርገውን ድርድር ሳያደርጉ ነው።
ድርድር በአንድ ወቅት የሚታየው ክስተት፣ መልካም ሁኔታ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ቀጣይነቱም ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት በውጭም በሀገር ውስጥም ለነበሩት ቡድኖች የሰጠው ተስፋና፣ “ተደምረናል” ያሉበት የመጀመርያው ነገር “ስለ አንድነት፣ ስለ ነፃነት” መሰል ነገሮች መስበክ ነው።  በተጨማሪም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት መጀመራቸው የፖለቲካ ቡድኖቹ ያለ መሰረታዊ ድርድር “ተደምረናል” እንዲሉ ያደረጓቸው ምክንያቶች ናቸው።
በተለይ በትጥቅ ትግል የቆዩት አሉን የሚሏቸው ወታደሮች የወደፊት እጣ ምን መሆን እንዳለበት እንኳ በቅጡ ሳይነጋገሩ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተውታል። ኦነግ ብቻ በጎን ድርድር እያደረገ ይገኛል።  ከጫካ ጀምሮ ትህነግ/ህወሓትን የሚያውቀው ኦነግ “ተደመር” ሲባል እነ ዶክተር አብይን ዘሎ  በማቀፍ ብቸ አልተመለሰም። ወይንም በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ወታደሮቹ ወደፊት የሚኖራቸውን እጣና ሌሎችም ጉዳዮች ተደራድሯል።  በድርጅቱ ውስጥ ነበሩ የተባሉት ወታደሮች፣ አባላትን የወደፊት የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ ድርድር ማድረጉ እየተነገረ ነው። ይህ ከአንድ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጣ ድርጅት ከመንግስት ጋር ሊያደርገው የሚገባ ትንሹ የድርድር ጉዳይ ነው።
 አርበኞች ግንቦት 7 እና አዴኃንን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖች ግን የወታደሮቻቸው ቀጣይ እጣ ምን መሆን እንዳለበት  እንኳ ከመንግስት ጋር ቁጭ ብለው አልተወያዩም።  ወታደሮቹ ቤታቸውን ጥለው ትግል ላይ የቆዩ ናቸው። አውሮፓና አሜሪካ የቆየ፣ ወይንም ኤርትራም የነበረና ኑሮው የማይናጋ፣ በፖለቲካ አመራርነት የሚቀጥል ሁሉ ወታደሩ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ጎዳና ላይ ይውደቅ፣ የቀን ስራም ይስራ ሳያስጨንቀው ከመንግስት ጋር መተቃቀፉን ቅድሚያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተበላሸው ትህነግ/ህወሓት በሚባል ቡድን ነው። ይህ ቡድን አሁንም ባህሪውን አልቀየረም። እነ አብይ ከትህነግ ጋር ነው የሚሰሩት። እነ ዶክተር አብይ ትህነግ እስካሁን ይከተለው ከነበረው የተለየ የሚመስልና ተስፋ ሰጭ አካሄድ ስለጀመሩ ብቻ ተስገብግቦ ከማቀፍ በፊት ትህነግ የሚባለው ክፉ ድርጅት ከዚህ ባህሪው መቆጠቡን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። በእርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶቹ በጭብጨባ በተጠመዱነት ወቅት  ትህነግ እነ አብይ የጀመሩትን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲጥር ታይቷል። ለእነ ዶክተር አብይም፣ ለተቃዋሚዎችም ሆነ  ለኢትዮጵያ ይጠቅም የነበረው ቀጣይ የፖለቲካ ግንኙነቶች በድርድር ቢወሰኑ ነበር። ዶክተር አብይ “ኑ ግቡ” ብሎ ያመጣው ድርጅት ተስፋው ዶክተር አብይ እንጅ ሕግ አልሆነም። እነ ዶክተር አብይ ቢሸነፉ ትህነግ/ህወሓት “ጨዋታ ፈረሰ” ለማለት የሚያመቸውን እድል አግኝቷል። ዛሬ ይቅርና በቀደመ ፖለቲካ የተኳረፉ፣ ይቀናቀኑ የነበሩ ቡድኖች ግለሰቦች ተማምለው፣ በሽማግሌ ተደራድረው ነው ቀጣይ እጣቸው ይወስኑ የነበረው።
የእነ ዶክተር አብይ አህመድ መደመር ያልተፃፈ ህግ ነው። አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ተብሎ የተፃፈ ሕግና አፈፃፀም አልተቀመጠለትም።
Filed in: Amharic