>

ኦህዴድና ትህነግ በማን ላይ ተስማሙ? (ጌታቸው ሺፈራው)

ኦህዴድና ትህነግ በማን ላይ ተስማሙ?
ጌታቸው ሺፈራው
~በእነ አብይ መንግስት ላይ ግንባር ቀደሙ አማፂ ትህነግ/ህወሓት ነው። ለዚህ ስራው የቀን ጅብ የሚል ስም ተሰጥቶታል። ከወንጀሉ ሁሉ በስተጀርባ አለበት እየተባለ ነው። ዶክተር አብይ አህመድ በሚኒሶታ ለተነሳለት ጥያቄ  ከአንዲት ከሁለት የትግራይ ተወላጆች የተነሳለትን ጥያቄ ከትህነግ/ህወሓት የመጣ እንደሆነ አድርጎ መልሷል።  ዶክተር አብይ አህመድ በሰጠው መልስ ከትህነግ ጋር እልህ ውስጥ  እንደገባ በግልፅ ያሳየ ነበር።
~ዶክተር አብይ ከአሜሪካ ከተመለሰ በኋላ በሶማሊ ክልል ለተፈፀመው ጭፍጨፋም የጅቦቹ እጅ እንዳለበት ከመገመቱ ባለፈ ፌደራል መንግስቱ በገዳዮቹ ላይ እርምጃ እንዳይወስድ በግልፅ መግለጫ የሰጠው  ትህነግ ብቻ ነው። ትህነግ  እንደፈለገ በሚጋልበው በሶማሊ ክልል ፕሬዝደንት ላይ  የሚወሰድ እርምጃ ፌደራል ስርዓቱን እንደሚያፈርስ አድርጎ ሲያስፈራራ ቆይቷል።
~ዶክተር አብይ አህመድ እና መንግስቱ በሶማሊ ክልል ለተፈፀመው ጭካኔ የሚገባውን ሳያደርግ አልፎታል። ጭራሹን በዚህ ወቅት ዶክተር አብይ በህይወት የመኖሩ ጉዳይ ሲያጠራጥር ቆይቷል። ታፍኗል፣ ታግቷል ከማለት አልፎ በሕይወት አለ ወይ ሲባል ሰንብቶ በይፋ የታየው ከደብረፅዮን ጋር ነው።
~ የግል ፀብ ያላቸው ያህል ማዶና ማዶ ሆነው አብይና ደብረፅዮን ከአብይ መጥፋት በኋላ አብረው መታየታቸው እንዲሁ የሚታይ አይደለም። በእርግጥ ዶክተር አብይ አህመድ “አንተም ተው፣ አንተ እረፍ” ብትል ከምትሰማው አሜሪካ ከርሞ ነው የመጣው። እነ ደብረፅዮን ወደ ኤርትራ ቢያንጋጥጡም ኢሳያስ “ከዛው እርጉ” ብሏቸዋል።  የትህነግ እና ኦህዴድ ግብግብ የዝሆኖች ግጥሚያ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ደብረፅዮን ከዶክተር አብይ ጋር ብቅ ብሏል
~ዶክተር አብይ አህመድ እና ደብረፅዮን አንድ ላይ የታዩት በየፊናቸው የእልህ፣ የፉክክር መግለጫ ሲሰጡ ከሰነበቱ በኋላ ነው። ከምንም በላይ የዶክተር አብይ መንግስት እና የደብረፅዮን ትህነግ በሶማሊ በውክልና ከተፋጠጡ በኋላ ነው።  ከዚህ ሁሉ ፍጥጫ እና ፉክክር በኋላ አብይ የጠፋው ታግቶም ይሁን በስራ ብዛት ላይ ሆኖ የሁለቱ መከሰት ግን በትህነግ እና ኦህዴድ መካከል ድርድሮች እንደነበሩ የሚያመለክት ነው።
~በተለይ በአማራው አካባቢ የሚደረገው እንቅስቃሴ መበርታቱ ትህነግ ጠላት ማብዛት እንደሌለበት ያሳሰበው ይመስላል። በወልቃይትና ራያ ያለው ፍጥጫ፣ ከኦህዴድ ጋር ያለው ፍጥጫ፣  የአማራው እንቅስቃሴ ሁሉም ተደማምሮ ሊቀብረው የደረሰ መሆኑ ያሰበው ትህነግ  የወቅቱን ብሶቱን ዋጥ አድርጎ ከኦህዴድ ጋር ለጊዜውም ቢሆን እርቅ ለማውረድ የተስማማ ይመስላል።
~በሌላ በኩል የትህነግ ሰዎች “የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ እያደረገብን ነው” የሚሉትን ኢሳትን እና አምርሮ ይጠላናል የሚለውን የዳያስፖራውን የፖለቲካ ሀይል መግባት ከአማራው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በስጋትነት ያዩታል። ከአንድነቱ ኃይል ባሻገር ክዶናል ከሚሉት ኦህዴድ ጀርባ አለ የሚሉትን የኦሮሞ ብሄርተኛ መደርጀትና ከኦህዴድ ጋር የማይነጠልበት ደረጃ ላይ መድረስ በኢህአዴግ ላይ ያላቸውን ልዕልና  የሚያሳጣ አድርገው ሳይወስዱት አልቀሩም። ከሶስቱ ኃይሉ የተነጠለ ወይንም በጋራ የማይዘምትባቸውን ኦህዴድ በቅርብ ርቀት መቆጣጠር ለጊዜው አዋጭ አድርገው ሳይወስዱት አልቀሩም።
~ለዚህ ደግሞ የዛሬው ክስተት አንድ ምሳሌ ይሆናል። የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ለቅሶን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ በተነሳ የግለቦች ፀብ ተገደሉ ለተባሉት የትግራይ ተወላጆች ትህነግና የትግራይ ተቃዋሚዎች በአንድ ላይ በአማራው ላይ  የጦርነት ነጋሪት መትተዋል። እጅግ የከረረና የዘመቻ መግለጫ አውጥተዋል። የትግራይ ኮምንኬሽን  ባወጣው መግለጫ  በትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በትግርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ያነጣጠረ ነው በሚል የሻዕቢያንም አግዘን ማለቱ ማስታወስ ይቻላል። ዛሬ   የትግራይ ተወላጆች ኦሮሚያ ውስጥ መገደላቸውን የትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ አክቲቪስቶች ቀዝቀዝ አድርገውት አልፈዋል። ይህ ሁነት ማዶና ማዶ ሆነው ሲዘላለፉ ከነበሩት የትህነግና የኦህዴድ ሰዎች  ሰሞን ያደረጉትን ስምምነት ላለማጠልሸት የተደረገ ይመስላል።
~ጃዋር ሞሃመድ ወደ ትግራይ ሊሄድ የነበር ሲሆን በትህነግ መካከል ጃዋርን ለመቀበል መከፋፈል ተፈጥሯል። እነ ጌታቸው ረዳ ለመቀበል ፍላጎት እንደነበራቸው፣ እነ ደብረፅዮን በበኩላቸው መቀበል እንዳልፈለጉ ተገልፆአል። እነ ደብረፅዮን ከጃዋር ይልቅ ያሳደግነውና በወቅቱ “የከዳን” ብለው የሚያምኑት ኦህዴድ ጋር መታረቁን የመረጡ ይመስላል። በተለይ ጃዋር መሃመድ ከእነ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጋር መታየቱ፣ ከአሁን ቀደም ዶክተር አብይ አህመድ የወልቃይት ጉዳይ የመሰረተ ልማት እንጅ የማንነት ጥያቄ አይደለም ሲል ከአማራ አክቲቪስቶች ቀድሞ ተቃውሟል። ይህ ተቃውሞው ለምንም ይሁን ለምን ትህነግ አትፈልገውም። ባህርዳር ላይ ከእነ ኮ/ል ደመቀ ጋር መገናኘቱ ደግሞ ለትህነግ የሞት ሞት ነው።
~ከምንም በላይ ደግሞ ትህነግ ካሳደገው ኦህዴድ ጋር እልህ በተጋባ ቁጥር ኦህዴድ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ከሚገኘው ተቃዋሚ ጋር ያለው ግንኙነት እየጠበቀ አቅሙን  እያበረታ፣ ቅቡልነቱን እያገኘ መሆኑ አሳስቦታል።  ይህን የኦህዴድን ጉዞ ከወዲሁ ለመግታት ትህነግ ከጎን ከጎኑ መከተል አለበት። ጃዋርን መቀሌ ላይ አልቀበልም ብሎ ከአብይ ጋር አዲስ አበባ መገኘት አለበት። ሌሎች ተቃዋሚዎች ሲመጡም፣ በለውጡ ሂደት ትህነግ ከኦህዴድ ጎን ሆኖ ማርሹን ለማስቀየር መጣር አለበት። መራቅ እንደማይጠቅመው፣ ከኦህዴድ ጋር መጣላት  የትኛውንም ሀይል በአንድ በኩል ተሰልፎ ትህነግ ላይ ለመዝመት ወደኋላ እንደማይል በመገመት ለጊዜው ከኦህዴድ ጋር ያለውን እልህ ዋጥ ለማድረግ የተገደደ ይመስላል። በተለይ የሞት የሽረት ያደረገውን የወልቃይትና ራያ ጉዳይ ቀሪውን “ጠላት” ሁሉ ገለል አድርጎ ፊቱን ወደ አማራው ማዞር እንዳለበት የወሰነ ይመስላል።
~እነ ዶክተር አብይ በትህነግ ላይ በጀመሩት ፉክክር አማራው ትልቅ እገዛ አድርጓል። ዶክተር አብይ አህመድ የቀን ጅብ ስያሜን ካወጣ በኋላ በአማራው ዘንድ የባሰውን ተወግዘዋል። የባህርዳሩን ሰልፍ እስካሁን እያወገዙ ነው። ብአዴን ውስጥ ሆነው በቀዳሚነት ለትህነግ ይሰሩ የነበሩት  አመራሮች አማራ ክልል ድርሽ እንዳትሉ ተብለዋል። ሰሞኑን ደግሞ የአቅርቦት እቀባ ተጀምሯል። በወልቃይትና ራያ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአማራው ብሔርተኝነት ከመቸውም ጊዜ በላይ ለትህነግ አስጊ ሆኗል። ይህ ስጋት ለእነ አብይም አስጊ ሆኗል። የአማራ ብሔርተኝነቱ እየበረታ ቢሆንም እስካሁን እውቅና የሰጡት አይመስሉም። በአንድ በኩል ከአንድነት ሀይሉ፣ በሌላ በኩል ከሌላው ብሔርተኛ ጋር እየተደባበቁ የአማራውን ንቅናቄ ለማለፍ ጥረዋል። ይህም  ትህነግና ኦህዴድን በመጠኑም ቢሆን ያቀራርባቸዋል።
~ትህነግን ደግሞ የትኛውንም አጋጣሚ ተጠቅሞ አንገቱን እንደሚያንቀው የሚሰጋውን የአማራውን ንቅናቄ፣ ቀጥሎም    ባለፊት 27 አመት በስፋት ሲያፍነው የነበረውን የአንድነት ሀይልና ሚዲያ ከእነ ዶክተር አብይ ጀርባ ሆኖ የሚጥልበትን አደጋ እንዲሁም ኦህዴድን ከጀርባ በመግፋት ኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ሚና የሚያኮስስበትንና ኦህዴድን የበለጠ ፅንፍ ያስይዘዋል ብሎ የሚፈራውን የኦሮሞ ብሄርተኛ ለመከላከል ከኦህዴድ በቅርብ ርቀት ለመሆን ድርድርን የመረጠ ይመስላል። እነዚህ ሶስት አካላት በአንድ ላይ እንዳይዘምቱበትም በኦህዴድ ኪስ ውስጥ የለመደ እባብ ለመምሰል እየጣረ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
Filed in: Amharic