>

የለውጥ ጉዞው ደጋፊ እንጂ እንቅፋት አይደለንም!!! (ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል)

የለውጥ ጉዞው ደጋፊ እንጂ እንቅፋት አይደለንም!!!
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
በዛይድ ተስፋዬ –  ፋና ብሮድካስቲንግ
ህወሓት ህገመንግስትን መሰረት አድርጎ ለሚደረግ የለውጥ ጉዞ ደጋፊ እንጂ እንቅፋት አይደለም
– ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህወሓት ህገመንግስትን መሰረት አድርጎ ለሚደረግ የለውጥ ጉዞ ደጋፊ እንጂ እንቅፋት አይደለም የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ።
በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ሊቀመንበሩ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ ከተመዘገቡ የልማት ስኬቶች በተጨማሪ በርካታ ጉድለቶች ታይተዋል ብለዋል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ብሎ በመወሰን ለሌሎች የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ምሳሌ የሆነ ጥልቅ ግምገማ አካሂዶ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን እና እርምጃዎች መወሰዱን አስታውሰዋል።
ዶክተር ደብረፅዮን በመግለጫቸው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት ድርጅቱ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችለው አቋም ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ምሁራን በስፋት በክልላቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ዕድል ተመቻችቶ የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
በዚህ ወር የሚካሄደው የድርጅቱ 13ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ታሪካዊ የለውጥ ጉባኤ ይሆናል ያሉት ሊቀመንበሩ፥ በጉባኤው እስካሁን የተደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ወደተግባር ሊለውጥ የሚችል ብቁ አዲስ ትውልድ ወደ አመራርነት ይመጣል ብለዋል።
በሀገሪቱ የታዩ ጉድለቶችን ለመፍታት ለውጥ ያስፈልጋል ብሎ የሚያምነው ህወሓት ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ እና የተገኙት ስኬቶችን እንደመነሻ የሚጠቀም የለውጥ ጉዞ አጋዥ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ባለፉት አመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን በመደምሰስ እንዲሁም አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርአት እና ህገመንግስት በመፃረር ለውጥ ሊመጣ አይችልም ያሉት ሊቀመንበሩ፥ በዚህ አካሄድ የሚደረግን የለወጥ ጉዞ ህወሓት አይደግፍም ብለዋል።
ሀምሌ 21 እና 22 በክልሉ በተካሄዱ ሰልፎች አስመልክተው ሊቀመንበሩ በሰጡት ሀሳብ ህዝቡ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ሀገራዊ አጀንዳዎች መሆናቸው ጠቅሰው የትግራይ ህዝብ ለሌሎች ብሄሮች ያለው ክብር ያንፀባረቀበት ሰልፍ እንደነበር ገልፀዋል።
ዶክተር ደብረፅዮን መቐለ በተካሄደው ሰልፍ ባስተላለፉት መልእክት “ያለን አማራጭ ተከባብሮ መኖር አልያም መበታተን ነው” ማለታቸው ትግራይን ለመገንጠል ከሚል የመነጨ ሳይሆን የሀገሪቱ የፌደራሊዝም ስርአት እኩልነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ለመጠቆም የተነገረ መሆኑ አስረድተዋል።
እርስ በርስ መከባበር ከሌለ ሃገሪቷ ወደ መበታተን ታመራለች ያሉት ሊቀመንበሩ ይህ እንዳይሆን ግን የፌደራሊዝም ስርአቱን ማሰጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
Filed in: Amharic