>

የህወሓት ፋሽስታዊ መንገድ፡ በሰማዕታት ስም ወደ ጦርነት! (ስዩም ተሾመ)

የህወሓት ፋሽስታዊ መንገድ፡ በሰማዕታት ስም ወደ ጦርነት!

by Seyoum Teshome

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ባደረገው ውይይት፣ እንዲሁም ባለፉት ሦስት ቀናት በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተደጋጋሚ የቀረበለት ጥያቄ፤ “በከፍተኛ ሙስና እና ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የህወሓት አመራሮች ለምን አይታሰሩም?” የሚለው ነው። ጠ/ሚኒስትሩ ለጥያቄው በሰጠው ምላሽ አክራሪ አመለካከት ያላቸው፣ ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰሩ እንደሆነ በይፋ የሚናገሩ አንዳንድ የህወሓት ባለስልጣናትን ቢያስር ከትግራይ ሕዝብ ጋር ወደ አላስፈላጊ መቃቃር ውስጥ እንደሚያስገባው ስጋቱን ገልጿል። በመሆኑም እነዚህን አመራሮች ወንጀል ስለመፈፀማቸው 1001 ማስረጃ ቢኖረውም “የትግራይን ሕዝብ ላለማጣት” ሲል አለማሰሩን ተናግሯል። ነገር ግን፣ ይህ አካሄድ ምን ያህል አዋጭ ነው? አሁን ህወሓት የሚከተለው መንገድ የትግራይን ሕዝብ ወደዬት የሚወስድ ነው? በዚህ ፅሁፍ እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን በዝርዝር እንመለከታለን።

1. የህወሓት ፖለቲካ – “አንድ-አይነትነት”
ከላይ የተጠቀሰው የዶ/ር አብይ አካሄድ ምን ያህል አዋጭነት እንዳለው ለመገምገም በቅድሚያ የህወሓትን ባህሪ መገንዘብ ያስፈልጋል። የህወሓት ባህሪ በዋናነት ከሚከተለው የድርጅታዊ አመራር እና የህዝብ አስተዳደር ስርዓት አንፃር ማየት ይቻላል። በዚህ መሰረት የህወሓት መሰረታዊ ባህሪ በአንድ-አይነትነት (Oneness) እሳቤ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የሚከተሉትን ምክንያቶች እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

1ኛ፡- ህወሓት በድርጅት ሆነ በክልል ደረጃ የሚከተለው ስልት በፍፁም አህዳዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ ነው። በድርጅቱ ውስጥ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ጨርሶ የለውም። የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያንፀባረቁ የህወሓት አመራሮችና አባላት መጨረሻቸው ከአባልነት መባረር፥ ስደትና ሞት ነው። በዚህ ረገድ ከህወሓት መስራቾች ውስጥ በእነ ሙሴ እና አረጋዊ በርሄ፣ እንዲሁም በእነ ስዬ አብርሃና ግብሩ አስራት ላይ የደረሰውን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

2ኛ፡- ህወሓት የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸው ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ቡድን ወይም ድርጅት ከነጭራሹ እንዲኖሩ አይፈቅድም። ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የሚከተለውን ስልት ብንመለከት ከእሱ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖችን በማጥፋት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ ድርጅቱ የትጥቅ ትግል እንደጀመረ ቀድሞ ጦርነት የከፈተው በደርግ ሰራዊት ሳይ ሳይሆን በኢዲዩና ኢህአፓ ታጣቂዎች ላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በምስራቃዊ ትግራይ እና በኤርትራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የትግራይ ታጣቂ ቡድኖችን በጥምረትና ውህደት ስም በመቅረብ በአባላትና አመራሮቹን በአሻጥርና በጭካኔ መግደሉ የሚዘነጋ አይደለም። ሌላው ቀርቶ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ላይ ባደረገው ስብሰባ የዓረና ፓርቲን “በጠላትነት” ፈርጆ እንደነበር የድርጅቱ መስራች አቶ ገብሩ አስራት ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸው ይታወሳል።

3ኛ፡- ህወሓት በትግራይ ክልል ነዋሪዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንዲኖር አይፈቅድም። ለህወሓት የትግራይ ህዝብ በሙሉ አንድና ተመሳሳይ ነው። የክልሉ ሕዝብ በአጠቃላይ “ተጋሩ” የሚል የወል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ ወንዶቹ “ትግራዋይ”፣ ሴቶቹ “ትግራዋይት” ይባላሉ። ከዚህ በተረፈ በትግራይ ተወላጆች ወይም ተጋሩዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንዲኖር አይፈቅድም። በእርግጥ ተጋሩዎች ከክልሉ ውጪ ይኖራሉ። ነገር ግን፣ ትግራይ ውስጥ የሚኖሩት በሙሉ ግን “ተጋሩዎች” ናቸው። ስለዚህ ትግራይ ውስጥ በቋሚነት የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን አይቀበልም። ”ተጋሩ” ከሚለው የወል ማንነት ውጪ የራሳቸው ማንነት፤ የተለየ ባህል፥ ቋንቋ፥ ታሪክና ስነ-ልቦና ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች በክልሉ መኖራቸውን አይቀበልም። ለምሳሌ የወልቃይት እና ራያ ተወላጆች የሚያነሱት የማንነትና የራስን ዕድል የመወሰን መብት ጥያቄ ህወሓት እስካለ ድረስ በፍፁም ተቀባይነት አያገኝም።

4ኛ፡- በትግራይ ሕዝብ እና በህወሓት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም። ቀንደኛ የህወሓት አባላትና አመራሮች እንደሚሉት፤ “ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ ማለት ደግሞ ህወሓት ነው።” በዚህ መሰረት ለህወሓት ጥሩ የሆነ ነገር ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ነው፣ ለፓርቲው መጥፎ የሆነ ነገር ደግሞ ለህዝቡ መጥፎ ነው። ስለዚህ ከፓርቲው አመራሮች የተለየ ሃሳብና አመለካከት ማንፀባረቅ፣ የድርጅቱን ሥራና አሰራር መተቸት፣ የህወሓት ተቃዋሚ የሆነ ፓርቲ መመስረትና አባል መሆን፣ በአጠቃላይ ከህወሓት ፍላጎትና ፍቃድ ውጪ መደራጀትና መንቀሳቀስ በትግራይ ህዝብ ላይ እንደተፈፀመ ክህደት፥ ጥፋትና ውርደት ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ ትግራይ ውስጥ “ጥሩ” እና “መጥፎ” (Good & Evil) የሚለው እሳቤ በራሱ ከህወሓት ፍላጎትና ምርጫ አንፃር የተቃኘ ነው።

2. “አንድ-ዓይነትነት” እና ፍፁም አምባገነንነት
በአንድ የፖለቲካ ማህብረሰብ ውስጥ የተለየ አቋምና አመለካከት ያለው ግለሰብ ወይም የአማራጭ የፖለቲካ ቡድን ከሌለ፣ በህዝብ መካከል፣ እንዲሁም በሕዝቡና በፓርቲ መካከል ልዩነት ከሌለ፣ ፖለቲካዊ ስርዓቱ በአንድ-ዓይነትነት (Oneness) ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በአንድ-ዓይነትነት እሳቤ ላይ የሚመሰረት ፖለቲካዊ ስርዓት ፍፁም ጨቋኝና አምባገነን (totalitarian) ነው። ይህን አስመልክቶ “Hannah Arendt” የተባለችው ፀሃፊ “On the Nature of Totalitarian: An Essays in Understanding” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፏ ጉዳዩን በዝርዝር ታስረዳለች። እንደ እሷ አገላለፅ እ.አ.አ. በ1930 ሩሲያ፣ እ.አ.አ. በ1938 ደግሞ በጀርመን ወደ ስልጣን የመጡት አምባገነናዊና ወታደራዊ ፋሽስት መንግስታት እንደ ህወሓት የአንድ-ዓይነትነት ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ናቸው። እነዚህ ጨቋኝና ጨፍጫፊ የሆኑ መንግስታት በሕዝቡ ውስጥ የአንድ-ዓይነትነት (Oneness) ፖለቲካን የሚያሰርፁት በሽብር (terror) አማካኝነት እንደሆነ ትገልፃለች፡-

“Terror freezes men in order to clear the way for the movement of History. It eliminates individuals for the sake of the species; it sacrifices men for the sake of mankind—not only those who eventually become the victims of terror, but in fact all men insofar as this movement, with its own beginning and its own end, can only be hindered by the new beginning and the individual end which the life of each man actually is. With each new birth, a new beginning is born into the world, and a new world has potentially come into being…. Terror fabricates the “oneness” of all men by abolishing the boundaries of law which provide the living space for the freedom of each individual.” Hannah Arendt (____): On the Nature of Totalitarian: An Essays in Understanding

ከላይ በተገለፀው መሰረት በአንድ-ዓይነትነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት በሽብርና ፍርሃት መርህ የሚመራ ነው። በማህብረሰቡ ላይ ሽብርና ፍርሃት በመንዛት ሁሉም ግለሰቦች አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በግለሰብ፥ ቡድንና ማህብረሰብ ደረጃ የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንዲኖር አይፈቅድም። በስልጣን ላይ ካለው የፖለቲካ ቡድን የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው የፓርቲ አባላት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ የማንነትና እኩልነት ጥያቄ የሚያነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገርና ሕዝብ ላይ ክህደት እንደፈጸሙ ተደርገው ይወገዛሉ፥ ይገፋሉ፥ ይቀጣሉ። በዚህ ምክንያት ለእስራት፥ ስደት፥ እንግልትና ሞት ይዳረጋሉ። በዚህ መልኩ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በማሸበር በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዲሰርፅ ይደረጋል። ይሁን እንጂ በሂደት ሽብር (terror) የጨቋኝና አምባገነናዊ ስርዓቱ የተግባር መርህ (principle of action) መሆኑ ያበቃል።

3. ከሰማዕታት ወደ መስዕዋት
በፍርሃትና ሽብር የተመሰረተው የፖለቲካ ስርዓት ስልጣኑን ወደፊት ለማስቀጠል የራሱ የሆነ አይዲዮሎጂ (ideology) ይፈጥራል። በዚህ አይዲዮሎጂ መሰረት እያንዳንዱ ግለሰብ የስርዓቱ አካል ብቻ ሳይሆን ስርዓቱን ከአደጋ የመከላከል ግዴታ ይጣልበታል። በመሆኑም ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ራሱን መስዕዋት ያደርጋል። በዚህ መልኩ ትላንት ጨቋኞችን ለማስወገድ የታገሉ ሰዎች የአዲሱን ስርዓት ለማስቀጠል ሲባል የመስዕዋት በግ ሆነው የሚቀርቡበትን ሂደት “Hannah Arendt” እንደሚከተለው ትገልፀዋለች፡-

“Human beings, caught or thrown into the process of History for the sake of accelerating its movement, can become only the executioners or the victims of its inherent law. According to this law, they may today be those who eliminate the “dying classes and decadent peoples” and tomorrow be those who, for the same reasons, must themselves be sacrificed. What totalitarian rule therefore needs, instead of a principle of action, is a means to prepare individuals equally well for the role of executioner and the role of victim. This two sided preparation, the substitute for a principle of action, is ideology.” Hannah Arendt (____): On the Nature of Totalitarian: An Essays in Understanding”

ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ይዞት የመጣው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚል የፖለቲካ አይዲዮሎጂ አለው። ይህ አይዲዮሎጂ የፓርቲና የመንግስት ከመሆን አልፎ የህዝብ መስመር እንዲሆን ተደርጓል። ለዚህ ደግሞ “የህወሓት መስመር የህዝብ መስመር ነው፣ የህዝብ መስመር የህወሓት መስመር ነው” የሚለውን መርህ መጥቀስ ይቻላል። ይህ አይዲዮሎጂ፤ “በህወሓት አባላት መካከል ልዩነት አይኖርም፣ ከህወሓት ሌላ የትግራይን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር የፖለቲካ ቡድን የለም፣ በትግራይ ሕዝብ (ተጋሩዎች) መካከል ልዩነት አይኖርም፣ እና በህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ መካከል ልዩነት የለም” በሚሉ የአንድ-ዓይነትነት እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ ነው።

የሰማዕታት ሃውልት፥ መቀሌ

በዚህ መሰረት ህወሓት የሚከተለው የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ማህብረሰብን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑም በላይ ግለሰባዊነትን ሙሉ በሙሉ የሚጨፈልቅ፣ በሕዝብ ስም የግለሰቦችን መብትና ነፃነት የሚገድብ ነው። በዚህ ረገድ የህወሓት አይዲዮሎጂ በጀርመንና ሩሲያ ከነበሩት አምባገነንና ወታደራዊ ፋሽስት መንግስታት ይልቅ በጃፓን ከነበረው ወታደራዊ ፋሽስት ጋር ይበልጥ ይመሳሰላል። በተለይ እ.አ.አ. ከ1915 እስከ 1945 ዓ.ም የጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት ሲመራበት የነበረው “የንጉሱ አይዲዮሎጂ” “the tennosei ideorogii” (emperor ideology) በመባል ይታወቃል። “Edward Said” (1993) “Representations of the Intellectual፡ Holding Nations and Traditions at Bay” በሚለው ፅሁፉ የዚህን አይዲዮሎጂ አመጣጥ እና የመጨረሻ ውጤት እንደሚከተለው ይገልፃል፥-

“The Meiji Restoration of 1868 that brought back the emperor was followed by the abolition of feudalism, and the deliberate course of building a new composite ideology began. This led disastrously to fascist militarism and national perdition that culminated in the defeat of imperial Japan in 1945. …the tennosei ideorogii (emperor ideology) was the creation of intellectuals during the Meiji period, and while it was originally nurtured by a sense of national defensiveness, even inferiority, in 1915 it had become a full-fledged nationalism capable simultaneously of extreme militarism, veneration of the emperor, and a sort of nativism that subordinated the individual to the state. It also denigrated other races to such an extent as to permit the willful slaughter of Chinese in the 1930s. After the war, most Japanese intellectuals were convinced that the essence of their new mission was not just the dismantling of tennosei (or corporate) ideology, but the construction of a liberal individualist subjectivity”

ከላይ የተገለፀው የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ከአፈጣጠሩ እስከ ውጤቱ ድረስ ከህወሓት አይዲዮሎጂ ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። ይህ የግለሰብን መብትና ነፃነት በመጨፍለቅ፣ ህዝብና ፓርቲን አንድ አድርጎ መጓዝ መጨረሻው አስከፊ ጦርነትና ዕልቂት ነው። በመሆኑም በጃፓን የነበረው ወታደራዊ ፋሽስት በስተመጨረሻ በሀገሪቱ ሕዝብ ላይ ያስከተለው ዕልቂት ህወሓት እየሄደበት ያለው መንገድ ነው። የጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት እ.አ.አ. በ1944 የፈፀመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ አሜሪካኖች የሁለተኛው ዓለም ጦርነትን በይፋ እንዲቀላቀሉ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ አመት በሄሮሽማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የኒኩለር ቦንብ እንዲጣል ምክንያት ሆኗል።

ፋሽስታዊ ስርዓቱ በግብዝነት በፈፀመው ጠብ-ጫሪ ድርጊት ሀገሪቱን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ከማስገባቱ ባለፈ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ዕልቂት አስከትሏል። ገና ከጅምሩ የጃፓን ጦር መሸነፉ እርግጥ ነበር። ሽንፈቱ የአሜሪካን ጦር የተሻለ ብቃትና ብዛት ሰለነበረው አይደለም። ከዚያ ይልቅ በዋናነት ጃፓኖች የሞራል ልዕልና (የበላይነት) ስላልነበራቸው ነው። ጦርነትን ማሸነፍ የሚቻለው በኃይል ብዛት አይደለም። ከኃይል ሚዛን ይልቅ የሞራል ሚዛን ለድል ያበቃል። የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በመግፈፍ ወረራ የፈፀመ ኃይል ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆን መሸነፉ አይቀሬ ነው። ምንም ያህል የጦር ኃይል ቢኖረው ሰራዊቱ ግን የትግል ሞራል ሊኖረው አይችልም። በአንፃሩ ወረራ ወይም ጭቆና የተፈፀመበት ወገን የጦር መሳሪያ ባይኖረው እንኳን ጠንካራ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ እና የሞራል የበላይነት ይኖረዋል። ይሄ ደግሞ ጦርነቱን በድል እንዲያጠናቅቅ ያስችለዋል። ለዚህ ደግሞ ራሱ ህወሓትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በእርግጥ ህወሓት በ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ከፍተኛ ቁጥር የነበረውን የደርግ ሰራዊት በማሸነፍ የፖለቲካ ስልጣን ይዟል። በዚህ መልኩ የያዘውን ስልጣን ከእኩልነት ይልቅ የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አውሎታል። በዚህ ምክንያት የህወሓት የበላይነት በሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ተገርስሷል። ሆኖም ግን፣ ከላይ ከተገለፀው መሰረታዊ ባህሪ አንፃር ህወሓት እውነታውን ተቀብሎ መቀጠል ይሳነዋል። ከዚያ ይልቅ በማህብረሰቡ ላይ ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋል። ይህ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር ግን የሂትለር ናዚ በፖላንድ ላይ፣ በተለይ ደግሞ የጃፓኑ ፋሽስት በአሜሪካን ላይ የፈፀመው ዓይነት ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ወረራ ይፈፅማል።

የህወሓትን አካሄድ ቀድሞ አውቆ መግታት ካልተቻለ በስተቀር አክራሪ አመለካከት ያላቸው የድርጅቱ መሪዎች የደረሰባቸውን ሽንፈት ላለመቀበል በሚያደርጉት ጥረት ከሽብርተኝነት አልፎ በአጎራባች ክልሎች፣ ከፌደራሉ መንግስት ወይም የጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት መግባታቸው አይቀርም። ቀደም ሲል በመተገለፀው መሰረት በትግሉ ሰማዕታት ስም የዘረጉት “የአንድ-ዓይነትነት” ፖለቲካ ዓላማው የትግራይን ሕዝብ ለመስዕዋትነት ማዘጋጀት ነው። የራሱን የስልጣን የበላይነት ለማስቀጠል ሲል የትግራይን ሕዝብ ከጦርነት ውስጥ ለመማገድ የሚያስችል ነው። በዚህ መልኩ በሚቀሰቅሰው ጦርነት ህወሓት መሸነፉ አይቀርም። ነገር ግን፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚያስከትለው እልቂት እጅግ የከፋ ከመሆኑ በተጨማሪ በሀገራችን ፖለቲካ ላይ ለዘመናት የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያልፋል።

Filed in: Amharic