>

የምስራቁ በር ትኩሳት!!! (መሳይ መኮንን)

የምስራቁ በር ትኩሳት!!!
መሳይ መኮንን
ስሜት ጨምድዶ፡ ልብ ሰቅዞ ለ3 ቀናት የዘለቀው የምስራቁ በር ትኩሳት ለጊዜው በረድ ብሏል። ዘላቂ ሰላም ይወርድ ዘንድ ጸሎት ምኞታችን ነው። አሁንም አስተማማኝ አይደለም። በአስፈሪው የሶስት ቀናት ጨለማ ውስጥ ለዘለቀ፡ የዘመናት ጎጆውን በአንዲት ጀምበር ላጣ፡ የእምነት ቤቱን በእሳት ለጋየበት፡ ወዳጅ ዘመዱን፡ ቤተሰቡን በጨካኞች የሞት በትር ለተነጠቀ ወገናችን አሁንም የሚቀር ነገር አለ። የስነልቦናው ስብራት በቀላሉ የሚጠገን አይደለም። ሀዘኑ ከባድ ነው።
በእርግጥ የአብይ አስተዳደር ለጂጂጋው ዕልቂት ምላሽ ለመስጠት ዘግይቷል ከሚሉ ወገኖች አንዱ ነኝ። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እረዳለሁ። ፖለቲካው ገና መረጋጋት እንደሚቀረው እገነዘባለሁ። የ27 ዓመቱ የህወሀት ቆሻሻን ለማጽዳት የተወሰኑ ጊዜያት እንደሚፈልግ አይጠፋኝም። በለማ ቡድን ቆራጥነት፡ በጠ/ሚር አብይ የፍቅርና የይቅርታ መስመር ከገደል ጫፍ የተመለስን መሆናችንም እርግጥ ነው። የሰከነ አካሄድ፡ የጥሞና ጊዜ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ መሆናችንንም አውቃለሁ። ….ግን የጂጂጋው ይለያል።
ከ10 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። አራት ካህናትና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከ60በላይ ሰዎች ህይወታቸው ጠፍቷል። ከፍተኛ ንብረት ወድሟል። ቤተሰብ ተበታትኗል። ቤት ፈርሷል። ጥሪትና ሀብት ተዘርፏል፡ የቀረው ተቃጥሏል። በምስራቁ በር የመጣብን መዓት ያስፈራል። ጂጂጋ ላይ የነበረው አስደንጋጭ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝሙ ጥርሱን ሞርዶ እየገዘገዘን ለመሆኑ አይነተኛ ማሳያ ነው።
የአብይ አስተዳደር የቱንም ያህል የፖለቲካ ስክነት የሚከተል ቢሆንም ለጂጂጋው ቀውስ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ይሰማኛል። አብዲ ዒሌን በዚህን ወቅት መተናኮል አደጋ ቢኖረውም ቢያንስ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ አስቀድሞ የመከላከል ስራ አልተሰራም የሚል እምነት አለኝ። አብዲ ዒሌ ይህን ዓይነት አደጋ ሊደቅን እንደሚችል የቅድመ ሴራ ትንተና በማድረግ አስፈላጊው የጥንቃቄ እርምጃ ሊወሰድ ይገባ ነበር። የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ይበልጥ እንዳያግለው በሚያደርግ መልኩ አብዲ ዒሌን ሳይናደፉ፡ የህዝቡን ህይወት ከአደጋ መጠበቅ የሚቻልበት ብልሃት አልነበረም የሚለኝ ካለ አልቀበለውም። መዘናጋት ነበር። አብዲ ከእነእብደቱ አውላላ ሜዳ ላይ ተፈቶ የተለቀቀ አደገኛ ሃይል ሆኖ እንዲቀጥል የተፈለገበት ምክንያት አይገባኝም። ቢያንስ በቅርብ ክትትል ውስጥ ሆኖ ስልጣኑን ሳይነኩበት፡ በብልጠት የመግደልና የማሸበር አቅሙን ሟሟሸሽ ይቻል ነበር ባይ ነኝ።
ይህን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገኝ ለሚቀጥለውም ጊዜ ተመሳሳይ ምክንያት እየሰጠን የህዝብን ህይወት አደጋ ላይ እንዳንጥለው ለማሳሰብ በሚል ነው። የአብይ አስተዳደር ይህን ሁኔታ አልተረዳውም ከሚል ድፍረት አስተያየት እየሰጠሁ ግን አይደለም። ሀገር ለማዳን እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር አመራር ቤተመንግስት እንደገባ አውቃለሁ። ኢትዮጵያ የምትገኝበትን መስቀለኛ የታሪክ መንገድ በብልሃትና በሰከነ አመራር ለመሻገር የተነሳ መንግስት ሀገሪቱን እያስተዳደራት ነው። ይሁንና እንደአንድ ዜጋ ሀሳብና አስተያየት በመስጠት መዘናጋት ካለ እንዲወገድ፡ ትኩረትም እንዲሰጠው ለመወትወት ያህል ነው።
አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች ችግሮች እንዳሉ መረጃዎች ይነግሩናል። የሀገሪቱ ትርምስ ውስጥ መግባት ፖለቲካዊ ትርፍ የሚያስገኝላቸው እንደህወሀት ዓይነት ተሸናፊ ቡድን የጂጂጋው ቀውስ ሰርግና ምላሽ ሆኖለታል። በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥና ትርምስ የሚሻ ወገን ካለ ተሸናፊ የሆነ ሃይል ነው። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሀሳብ የሚመራ፡ በዲሞክራሲ ፉክክር የሚጠናከር እንጂ በአመጽና ግርግር የሚነዳ አይደለም። በስልጣን ላይ ያለው አመራር እንደህወሀት ቀውስንና ግጭትን እንደስትራቴጂ በመጠቀም ስልጣኑን ለማስጠበቅ የሚፈልግ እንዳልሆነ ይታመናል። የሀሳብ ጥራት እንጂ የሁካታና ትርምስ መንገድ ቤተመንግስት እንዳያስገባን ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል። እናም ከእነዚህ ትርምሶችና ግጭቶች ጀርባ የማን እጅ እንደሚኖርበት በድፍረት መናገር ይቻላል።
በጂጂጋው ቀውስ የአብይን አስተዳደር የምወቅስበት ከቅዳሜው ክስተት ጭምር ነው። አብዲ ዒሌ አንቀጽ 39 መዞ ሶማሌ ክልልን ለመገንጠል የጠራውን ስብሰባ ለማስቆም በሚል የገባው የመከላከያ ሰራዊት መውጣት አልነበረበትም። ምንም እንኳን አብዲ ዒሌን ከእብደት ውሳኔ ማስቆም የተቻለ ቢሆንም የህወሀቶችን ጩሀትና የአብዲ ዒሌን ቡራ ከረዩን ተከትሎ ጂጂጋን ለቆ መውጣቱ ተገቢ አልነበረም። ቀድሞውኑ አለመግባት፡ ከገቡም ስራን ጨርሶ፡ አብዲ ዒሌን አስተንፍሶ፡ ከተማዋን አረጋግቶ፡ የህዝቡን ደህንነት አስጠብቆ እንጂ ነካክቶ መውጣት ምን ዓይነት ስትራቴጂ ነው? ያ ሁሉ ዘረፋና አሰቃቂ ግድያን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉት መከላከያ ሰራዊት ጂጂጋን ለቆ ከወጣ በኋላ ነው። አብዲ ዒሌም እየተንጎማለለ ”እንደኮ/ል ደመቀ አፍነው ሊወስዱኝ የመጡትን ህዝቤ አስጣለኝ” ማለት የጀመረውም ከዚያን ወዲህ ነው።
በሚካዔል ቤተክርስቲያን የተጠለለው ህዝብ ለሶስት ቀናት ምግብና ውሃ አላገኘም ነበር። ከአከባቢው በረሃማነት ጋር የረሃቡ ነገር ተፈናቃዩን ህዝብ ከሞት ጋር አፋጦት ነበር። ምግብ ለማግኘት ከቤተክርስቲያኗ በወጡ ወጣቶች ላይ የአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው አራቱን ገድለዋል። እንግዲህ የአብይ አስተዳደር በዚህም ሊወቀስ ይገባል። ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከቤተክርስቲያን የተሸሸጉትን በረሃብ እንዳያልቁ በድርድርም ይሁን በሌላ መንገድ እርምጃ መውሰድ ይገባ ነበር። አብዲ ዒሌ ነገሮች እየከፉ ከመጡ እነዚህን በቤተክርስቲያን የተጠለሉትን ዜጎች እንደመያዣ ከአብይ መንግስት ጋር ለመደራደር አቅዶ እንደነበርም ተስምቷል።
በእርግጥ አሁን አልፏል። የጂጂጋው ቀውስ ለአብይ አስተዳደር ጥሩ ትምህርት ሰጥቷል ማለት ይቻላል። ፖለቲካውን ለማረጋጋት በሚል ሀገርን የሚያጠፋ ወንጀል ሲሰራ እርምጃ አለመውሰድ የበለጠ ቀውስን እንደሚፈጥር ከጂጂጋው ክስተት መረዳት ይቻላል። አብዲን ዒሌን በዚህን ውጥረት ውስጥ መነካካት አደገኛ ነበር የሚሉ ወገኖች ከዚህም በላይ ቀውስ ይፈጠር ነበር ሲሉም አቋማቸውን ያጠናክራሉ። ህወሀቶች የመረበሽ አቅማቸው እስኪሟሽሽ ድረስ አሁንም በጋጠወጦቻና ሽብር አንጋሾች ላይ እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ለአብይ አመራር ምክር ይሰጣሉም።
በእርግጥ ይህ አካሄድ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው። በዘገዩ ቁጥር ከሚታሰቡት በላይ አደጋ የሚያመጡ ጉዳዮች እንዳሉም መዘንጋት አይገባም።  በሌሎች አከባቢዎችም ተመሳሳይ ክስተቶች መኖራቸው የሚጠበቅ በመሆኑ የአብይ አስተዳደር ሁኔታዎችን በመመርመር እርምጃ በመውሰድ የሚከተለውን አደጋ በመፈተሽ በቶሎ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። ህዝብ አሁን ላይ የሚያጉረመርመው ”የታለ መንግስት?” የሚለውን ቅሬታ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ውጥረት ጋር እያስተያዩ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው።
የአብዲ ዒሌ መጨረሻ አልታወቀም። ራጆ የተሰኘ በክልሉ ጉዳይ ላይ ዜና የሚያሰራጭ የፌስ ቡክ ገጽ አብዲ ዒሌ ፑንትላንድ ገብቷል ሲል ዘግቧል። መንግስት በዚህ አንጻር ግልጽ የሆነ ነገር አልነገረንም። ከፕሬዝዳንትነት እንጂ ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበርነት እንዳልተነሳ ተገልጿል። ድርድሩ በምን እንደተጠናቀቀ አናውቅም። አሁን በአብዲ ዒሌ ቦታ የተተካው ሰው ቀኝ እጁ ነው ይባላል። የሶማሌ ክልል መንግስት ካቢኔ የቤተዘመድ ጉባዔ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ክልሉን እንዲመራ የተደረገው አህመድ አቢድ ሞሀምድም የአብዲ ዒሌን ሌጋሲ ያስቀጥላል የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። ህወሀት ከክልሉ ፖለቲካ ላይ እጁን እንዲሰበስብ ካልተደረገ ቀውሱ መመለሱ አይቀርም። የሆነው ይሁን። ዋናው ለጊዜውም ቢሆን ወገኖቻችንን መታደግ ነው።
በተረፈ የህወሀቶች ጩሀት ይገባናል። ከቤተመንግስት የተባረረው ቡድን ከመቀሌም እስኪወገድ ጩሀቱ ሊቀጥል እንደሚችል እንጠብቃለን።
Filed in: Amharic