>

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አብዮትህን ጠብቅ! (ታዬ ደንደአ)

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አብዮትህን ጠብቅ!

ታዬ ደንደአ

የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ ባደረገዉ ትግል እጅግ አሰደማሚ አብዮት አካሄዷል። ይህ አብዮት ወሳኝ ለወጦችን እያመጣ ስለመሆኑ አለም በሙሉ ይመሰክራል። በሺ የሚቆጠሩ እስረኞች ተፈቷል። ብዚ የጥላቻ እና የጥርጣሬ ግንቦች ፈራርሷል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መሀከል ሠላም ወርዷል። ምስራቅ አፍሪካ ተስፋ ሰንቋል።የኢትዮጵያ ዴያስፖራ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስትን ደግፏል። ለቁጥር የሚያታክቱ ብዙ ነገሮች በአጭር ጊዜ ተከዉኗል።ነገር ግን የሚቀሩ ነገሮች ብዙ ናቸዉ። ፀረ-ለዉጥ ቡድኑ ደግሞ ለዉጡን ለመቀልበስ በተለመደዉ ስልቱ መንደፋደፍ ላይ ይገኛል። 

ተጨባጭ መረጃ እንደሚያሳየዉ 100 ሺ የሚሆን የሶሻል ሚዲያ ሠራዊት ስልጠና ወስዶ ተሠማርቷል። ከሀገር ካዝና የተዘረፈ ገንዘብ ለፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ተመድቧል።። ይሄ ሰራዊት ከ80% በላይ በአማራ እና በኦሮሞ ስም የዉሸት FB ከፍቷል። ዋና አላማዉ ጥርጣሬን መስበክ ነዉ። በልዩነት እንደኖረ በልዩነት ከወደቀበት ሊነሳ ይፈልጋል።

እዝህ ላይ በኦሮሞ እና በአማራ ላይ አተኩሯል። በሁለት መልኩ እንቅስቃሴ ላይ ነዉ። አንደኛዉ የሁለቱን ህዝብ ዉስጣዊ አንድነት ማፍረስ ነዉ። ለዝህ አላማ ሀይማኖትን እና አከባቢያዊነትን ለመጠቀም አስቧል። ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ ወይም ሸዋ እያለ አማራን እርስ-በርሱ መለያዬት ይፈልጋል። በዝያዉ ልክ ሸዋ፣ ወለጋ፣ አርሲ፣ ሀረርጌ፣ ቦረና፣ ጉጂ ወዘተ እያለ ኦሮሞን በኦሮሞ ላይ ለመቀስቀስ አቅዷል። ሁለተኛዉ ደግሞ የአማራን እና የኦሮሞን አንድነት ማላላት ነዉ። ለዝህ አላማ ደግሞ ባንዲራን፣ የስልጣን ክፍፍልን እና የአዲስ አበባን ጉዳይ ለመጠቀም ወስኗል። ባንዲራ የኦነግ እና የምንልክ በማለት ለሁለት ከፍሏል። ኦሮሚያ ላይ የሚያዘዉን ባንዲራ እያሳየ “ኦሮሞ ሊገነጠል ነዉ!” በማለት አማራን ለጥርጣሬ ይጋብዛል። አማራ ላይ የሚያዘዉን ባንዲራ በማጉላት ደግሞ “ሚኒልክ እየመጣ ነዉ!” በማለት ኦሮሞን ለማወናበድ ይከጅላል። 

ወገኖቼ ጥያቄያችን ከባንዲራ ቀለም በላይ ነዉ። ነፃነት እና ብልፅግና እንፈልጋለን። ተለያይተንም ተባብረንም አየይተናል። በተለያዬን ጊዜ በትናንሽ እንቅፋቶች ተጠልፈን ለከፋ ዉርዳት ተደርጌናል። በተባበርን ጊዜ ደግሞ ትልቅ ተራራን በመናድ አለምን አስደንቀናል። የቱ እንደሚሻል መናገር አይጠበቅብኝም። ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ነች። ከለማች ሁላችንም እንደሰታለን። ከጠፋች ሁላችንም እናጣታለን።

የስልጣን ጉዳይ አንዱ የክፍፍል አጀንዳ ነዉ። ግን አሁን ስልጣን የለም። የፈረሰችን ሀገር መልሰን በመገንባት ላይ ነን። ደግሞ አንድ ሰዉ ስልጣን ሲይዝ ለሁሉም እኩል ማገልገል አለበት። ክቡር አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በጠቅላይ አቃበ-ህግነታቸዉ የሚሰሩት መልካም ነገር የጠቀመዉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነዉ። ከእስር የተፈታዉ ከፍያለዉ ተፈራ ብቻ ሳይሆን አቶ አንዳርጋቸዉም ጭምር ነዉ። በምህረት አዋጁ ተጠቅሞ ወደሀገሩ የሚመጣዉም አንድ ብሔር ብቻ አይደለም። ክቡር ዶር አምባቸዉ በእንዱስትሪ ሚንስትርነታቸዉ የሚሰሩት በጎ ነገር ተጠቃሚዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመሆኑም ባሻገር ከመቶ ወይም ሁለት መቶ ዓመታት በኀላ የሚመጡ የልጅ ልጆቻችን ይሆናሉ። መጠናችን በዝያ ልክ አስፍቶ ማሰብ ነዉ። ከድንክዬ አስተሳሰብ መዉጣት ያስፈልገናል። ማን ምን ስልጣን ያዜ ሳይሆን በስልጣኑ ማን ምን ሠራ ብንል ያምርብናል። ዶር አብይ እየሰሩ ያሉት ጥሩ ስራዎች በዶር ብርሃኑም ቢሰሩ መልካም ይሆናሉ።

የአዲስ አበባ ጉዳይ ለፀረ-ለዉጡ ቡድን አመቺ ቢለዋ ነዉ። በሁለቱም በኩል ይቆርጣል። ያዉ የአንድ ከተማ ካንቲባ ሁለት ሊሆን አይችልም። ኦሮሞ ከተሾመ አጀንዳ ተቀርፆ አሁን ባለዉ መልኩ ቅስቀሳ ይሰራል። አማራ ከተሾመ ደግሞ “የአንተን ከተማ አማራ ወይም ነፍጠኛ ወሰደዉ!” ተብሎ በቄሮ ላይ ፕሮፓጋንዳ ይሰራል። ህዝባችን ከዝህ ወጥመድ መዉጣት አለበት። ከዘር ቆጠራ ወጥተን ሁላችንንም የሚታኮራ ሀገር እና ከተማ ለመገንባት ተባብረን ብንሠራ ይሻለናል። አሜሪካ ለታማኝ በየነ እና ለጀዋር መሀመድ የተመቸዉ ኢትዮጵያዊ ስለሚያስተዳድረዉ ሳይሆን ለሁሉም በሚመች ሁኔታ ስለሚተዳደር ነዉ!

አንድ ነገር ግልፅ ይሁን። በድንክዬ አስተሳሰብ ተመርተን እርስ በእርሳችን በመጠላለፍ ከልወደቅን በስተቀር የትኛዉ ምድራዊ ሀይል ከመንገዳችን ሊመልሰን አይችልም። ለዉድቀታችንም፣ ለልማታችንም ኃላፊነቱ የኛ ነዉ። ዘመን የማይሽረዉ ሁሉ አቀፍ አስተሳሰብ ያስፈልገናል።

ሰላም ለሁላችን!

Filed in: Amharic