>
5:13 pm - Monday April 19, 5041

ኢትዮጵያዊነት  በትውልዳችን ይለምልም  !!!  (አሰፋ ሀይሉ)

ኢትዮጵያዊነት  በትውልዳችን ይለምልም  !!! 
አሰፋ ሀይሉ
ኢትዮጵያዊነት በትውልዳችን ውስጥ እንዲለመልም የምንፈልገው – ኢትዮጵያዊነት ስለሚያዋጣን ወይ ስለሚያተርፈን ወይ ደስ ስላለን ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ምስኪን ጠይም ባለማዲያት እናት ብትሆን እንኳ ፡ የጋራ እናታችን ብለን እንቀበላት ፡፡ ጥላዋ የጋራ ጥላችን ይሁነን ፡፡
ባንዲራዋ የጋራ አልባሳችን ትሁነን ፡፡ ቢኖራት፣ ባይኖራት፣ ብታቀማጥለን፣ ብታስርበን፣ ብትበደር፣ ብትለቀት፣ ብትገርፈን – ብትመቸን፣ ባትመቸን – በቃ ኢትዮጵያችን ይችው ምስኪን እናታችን ነች ብለን እንቀበላት ፡፡ የኅብረት መጠለያ ታዛችን ትሁነን ፡፡ ደኸየች ብለን አንጫረስባት ፡፡ እና አናሳዝናት ፡፡
ወላዲት እናቴ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብለን በድህነቷ መጠን አንለካት ፡፡ ባደረገችልን መጠን ባለውለታነት አይሰማን ፡፡ ባላደረገችልን መጠን ባይተዋርነት በልባችን አይደር ፡፡ ብትደኸይም – ይህች ሀገር – ያላትን ለልጆቻችን ሰጥታ አቆይታናለች ፡፡ ያላትን በፍቅር በልተን እንደር ፡፡ የጎደላትን እንሙላላት ፡፡
ምስኪኒቱ ሀገራችን ትናንት ምን ብትደኸይ፣ ምን የምትሰጠን ብታጣ – ሀገራችንን – ልጆቻችን ሁሉ በፍቅር፣ በነፃነት፣ በደስታ፣ ችግራቸውን ሁሉ ረስተው የሚቦርቁባት – የጋራ የደስታ መስካችን እናድርጋት ፡፡ በኅብረታችን ኢትዮጵያችንን ኅብር ያላት የኅብረት ድንኳናችን እናድርጋት ፡፡ ሀገሬ ለእኔ ምን ሰጠችኝ አንበል ፡፡ እኔ ለሀገሬ ምን ልስጣት እንበል ፡፡
ሀገር ማለት ሌላ አይደለችም ፡፡ የምንወልዳቸው ልጆቻችን ናቸው ፡፡ በሀገር ተጠልለን ያለንን አበርክተን፣ ያላትን በፍቅር ተቋድሰን፣ በኅብረት እንኑርባት ፡፡ እና ልጆቻችንም በእሷ በእናታቸው ታዛ ሥር ተጠልለው – መጪውን ዘመናቸውን ከኛ ይበልጥ አሳምረው የሚኖሩባት ታላቅ ጥላችን እናድርጋት ፡፡
እኛ እናልፋለን ፡፡ ልጆቻችን ግን ይኖራሉ ፡፡ እናታችንን ግን እኛን በፈጠረች – አናድማት፣ አናቁስላት፣ አናስለቅሳት፣ አናሳዝናት ፡፡
ምክንያቱም ሀገር የችግር ጊዜ ጥላ ነችና፡ሀገራችንን በጥበብ፣ በፍቅር፣ በባንዲራ፣ በኅብረታችን አድምቀን ሰብዓዊ ሆነን እንለፍባት፡፡ትውልዳችንን ለሠላም ለፍቅር ለኅብረት ወደ ወደፊቱ ብሩህ ህይወት እናሻግራቸው፡፡
ምክንያቱም ሀገር ሌላ አይደለችም ፡፡ ሀገር ይህች ልጅ የያዘቻት ጥላ ነች ፡፡ ይህ ህጻን ቀና ብሎ የሚያያት ባንዲራ ነች ፡፡ ዛሬ ድክ ድክ የሚሉ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን – ነገ ቀና ብለው የሚራመዱባት – የእናት ቤት ነች ሀገር ፡፡
ኑ – መጠጊያ ታዛችንን – እናት ሀገራችንን – የልጆቻችንን የወደፊት መኖሪያ – በፍቅር ተጋግዘን – በትዕግስት ተሳስበን፣ መልካምን አዋጥተን – ኑ – በጋራ እንገንባት ፡፡ እናት ሀገራችንን ደስ እናሰኛት ፡፡ ኑ ፡፡ ኑ ወደ ፍቅር ፡፡ ተ ደ መ ሩ  ፡  ለ ፍ ቅ ር  ፡  በ ፍ ቅ ር ! ! ! ፍ ቅ ር  ፣  ኅ ብ ረ ት  ፣  ሠ ላ ም  –  ሁ ሉ ን  ፡  ያ ሸ ን ፋ ሉ ና ፡፡ 
ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት  ፡  በ ት ው ል ዳ ች ን  ፡  ው ስ ጥ  ፡  ይ ለ ም ል ም  ! ! ! 
አምላክ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ አብዝቶ በፍቅሩ በቸርነቱ በፀጋው ይባርክ ፡፡ እናት ሀገር እምዬ ኢትዮጵያ ከትውልድ እስከ ትውልድ ፀንታ ለዘለዓለም ትኑር ፡፡ እኛን፣ ልጆቻችንን፣ የልጅ ልጅ ልጆቻችንን ሁሉ አስጠልላ ታኑር ፡፡ አምላካችን ከእኛ ከልጆቻችን ሁሉ ጋር አብሮን ይሁን ፡፡ አ ሜ ን  ፡፡
Filed in: Amharic