>

በጅጅጋ ሕገ መንግሥት ተብዬው  እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም! (አቻምየለህ ታምሩ)

በጅጅጋ ሕገ መንግሥት ተብዬው  እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!
አቻምየለህ ታምሩ
«የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል» በሚባለው ክልል ውስጥ  በተለይም በጅግጅጋ ከተማ  ከሶማሌ ውጭ በሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ  እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝ  ግድያ፣ ግፍ፣ ጭካኔ፣ ዝርፊያ፣ የንብረት ማውደምና የቤተ ክርስቲያን  ማቃጠል  ብዙ ሰው እንደሚያስበው «ሕገ መንግሥት» የሚባለው ነገር እየተጣሰ አይደለም፤ እንዴውም እየተተገበረ እንጂ።
ሕገ መንግሥት ተብዮው የተጻፈው  «ለዘመናት ነበረ» የተባለውን «የተዛባ ግንኙነት» ወይንም «የጨቋኝና የተጨቋኝ ግንኙነት» ለማጥፋት ነው። በሕገ መንግሥቱ መሰረት  የክልሉ ባለቤት ሶማሌ ብቻ ነው። ከሶማሌ ውጭ ያለው መጤና ሰፋሪ ነው ተብሏል። ነዋሪው አማራ ከሆነ ደግሞ ጨቋኝ እንደሆነ ተደርጎ ተረክ ተፈጥሯል።  ቤተ ክርስቲያኗ የጭቆና መሳሪያ ተደርጋ ትምህርት መሰጠት ከጀመረ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሆኖታል። ይህ በሆነበት ሁኔታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ጭቆናን ማጥፋት የሚቻለው ጨቋኝን በማጥፋትና ምልክቶቹን በማውደም ብቻ ነው።
ስለዚህ በወያኔ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ  «ለዘመናት ነበረ» የተባለውን «የተዛባ ግንኙነት» ወይንም «የጨቋኝና የተጨቋኝ ግንኙነት»  በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ማጥፋት የሚቻለው አሁን «የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል» በሚባለው እየሆነ እንዳለው ጨቋኙን በማጥፋት እንደ ቤተ ክርስቲያን አይነት የጭቆና መሳሪያ ናቸው የተባሉትን  ደግሞ በማውደም ብቻ  ነው። በሌላ አነጋገር በጅግጅጋ  የምንሰማው ሁሉ ሕገ መንግሥት ተብዮው እየተተገበረ እንጅ እየተጣሰ አይደለም። ሕገ መንግሥቱ «የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል» በሚባለው ክልል ውስጥ ከሶማሌ ውጭ የሚያውቀው ዜጋ የለውም። ዜግነትህን የገፈፈህን ሕገ መንግሥት ተብዮ የወያኔ  ደንብ ተጣሰ ካልህ ሕገ መንግሥቱን አለማወቅህን ብቻ ነው የሚያሳየው።
ዐቢይ አሕመድ  ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆን አገዛዙ  የተዋቀረበት  ርዕዮተ ዓለም  እስካልተቀየረ ድረስ ምን ቅን ሰው ቢሆን  ከወያኔ ዘመን የተለየ ነገር እንዲያመጣ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድለትም ብለን ተናግረን ነበር። ገፋ አድርገንም እውነተኛ ስልጣን ቢኖረው  እንኳ የትግሬን የበላይነት በኦሮሞ የበላይነት ከመተካት በስተቀር  ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደዜጋ የሚበጅ ነገር  እንዲያመጣ ርዕዮተ ዓለሙ አይፈቅድለትም ብለን ተናግረን ነበር።
አሁንም እንደግመዋለን! የኢትዮጵያ ችግር ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው  አገዛዙ የተዋቀረበት  ርዕዮተ ዓለም ነው። ከዐቢይ አፍ ማር ቢዘንብ እንኳ ተፈጻሚ የሚደረገው  ይህ ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው  ርዕዮተ ዓለም ነው። ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው  የወያኔ ሕገ አራዊት እስካለ ድረስ የሕግ የበላይነት፣ ንብረት የማፍራት፣ ዜጋ የመሆን፣ የሕይወት ጥበቃ፣ ወዘተ የሚባሉ መብቶች የሉህም።
ባጭሩ የጭካኔ አስተሳሰብ የወለደው  የፋሽስት ወያኔ ሕገ አራዊት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ እስካልተወገደ ድረስ ክልልህ አይደለም በተባለው አማራና ኦሮሞ  ላይ ዛሬ  በጅግጅጋ እየደረሰ ያለው የወያኔ ሕገ መንግሥት የወለደው ግፍና ጭካኔ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በየተራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ መፈጸሙ የማይቀር ነው።
Filed in: Amharic