>

ጆሮ የተነፈገው የጅግጅጋው ጩኸት…. (ውብሸት ሙላት)

ጆሮ የተነፈገው የጅግጅጋው ጩኸት….
ውብሸት ሙላት
 
ማልዶ ወደ አደባባይ የወጣው የአ.አበባ ህዝብ የጂጂጋ ወገኖቹን የድረሱልን ድምጽ ሲያስተጋባ ውሏል!!!
ወደ መከላከያ ዋናው ማዘዣ በማምራት በዋይታና በኡኡታ ” መከላከያ ይግባልን ወገኖቻችን አለቁ፣ እህቶቻችን ተደፈሩ! እረ የመንግስት ያለህ!” እያለ ድምፁን ሲያሰማ የዋለው ሰልፈኛ ወደ ጠ/ሚ ቢሮ በመሄድ ይህንኑ የምሬት ድምፁን ልብ በሚሰብር አሳዛኝ የሰቆቃ ድምጽ ሲያሰማ ውሏል!
*****
ዛሬ፣ የጅግጅጋ ነዋሪዎች የሆኑ፣ነገር ግን በተለያዩ ምክንያት አዲስ አበባ ያሉ ከአስር ያላነሱ ሰዎች ጋር ተገናኝተን ነበር፡፡ ሁሉም ቤተሰባቸው ጅግጅጋ ነው፡፡ ሁሉም ቤተሰቦቻቸው ጋር ስልክ በመደውል የሆነውን እና እየሆነ ያለውን በየሰዓቱ መልእክት ይቀያየራሉ፡፡ የተወሰኑት ልጆችም ስላላቸው ልጆቻቸውን እንዲህ አድርጉ እንድህ አታድርጉ በማለት ይመክራሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ጅግጅጋ ከሚኖሩ ጓደኞቼ በስልክ አነጋግሬያለም፡፡ መልእክትም የላኩል አሉ፡፡ በጥቅሉ ከእነዚህ ሰዎች የሰማሁትን መሠረት በማድረግ፡-
ጅግጅጋ ከተማ ላይ በዚህ ዓመት ብቻ የሐበሾች (ማናቸውም ከሶማሌ ውጭ የሆነ) ቤት ከአራት ጊዜ በላይ ፍተሻ ተደርጓል፡፡ የፍተሻው ዓላማ የጦር መሳሪያ (ጩቤም ሜንጫም ሳይቀር) ያላቸውን ለማስፈታት ነው፡፡ በተለይ በአብዲ ኢሌ አጠራር፣ ”የደርግ ርዝራዦች” ተብለው የሚጠሩት ሙሉ በሙሉ ስለት ያለው ነገር እንኳን በእጃቸው እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ራሳቸውን ከጥቃት የሚከላከሉበት ምንም ዓይነት መሳሪያም የላቸውም፡፡ የሚከላከልላቸው፣የሚጠብቃቸው  የጸጥታ ሃይልም የለም፡፡
ሰሞኑን ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ የመጡ የተደራጁ ወጣቶች ልዩ ሃይሉ እያየም አልፎ አልፎም እራሱ ልዩ ሃይሉም ጭምር ከቤት በማውጣት የሐበሾቹ ቤት ምንም ዓይነት ለምግብ የሚሆን ዱቄት እንኳን ሳይቀር ተደፍቷል፤የምግብ ማብሰያ እቃዎች ተሰባብረዋል፤የተሻለ ዋጋ የሚያወጡ እቃዎች በመኪና እየተጫኑ ተወስደዋል፡፡  አበዝሃኛው ሰው ለምግብ የሚሆን ነገር የለውም፡፡ ሶማሌ ያለሆኑ ነዋሪዎች የሚበዙባቸው ቀበሌዎች ንብረታቸው ከተዘረፈ በኋላ አሁን ላይ በርካታ የሶማሌ ልዩ ሃይል በዙሪያቸው አሉ፡፡
ቤተክርስቲያን ሊቃጠል ሲል አንዳንድ ሙስሊሞች በቆራጥነት ሄደው አቃጣዮቹን በመቃወማቸው ጉዳት የደረሰባቸው አሉ፡፡ አንዳንድ ቆራጥ የጅግጅጋ ነዋሪ የሆነ ሶማሌዎች ሌሎች ወገኖቻቸውን ከቤታቸው በማስጠለል እኛን ሳትገድሉ እነሱ እትነኩም ያሉ መኖራቸውን በስም እየጠቀሱ ሁሉ ነገረውኛል፡፡
ጅግጅጋ ላይ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የተቃጠለው አብዲ ኢሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መጥቶ “አይዟችሁ ሰላም ነው” ብሎ ነገር ግን ሕዝቡ ጩሆበት ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ የሚካኤልም ቤተ ክርስቲያንም በርካታ ሱቆች ተቃጥለዋል፡፡ የሚያቃጥሉት ላይ ልዩ ፖሊሱ ምንም ዓይነት ርምጃ ሲወስድ አልታየም፤በቁጥጥር ስር የማዋል ስራም አልሰራም፡፡
ዛሬ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተጠልሎ የሚገኘው ሕዝብ በግምት ከአራት እስከ አምስት ሺህ እንደሚሆን እዚያው ያሉ የሚገኙ ሰዎች ነግረውኛውል፡፡ አውደ ምህረቱም የቤተ ክርስቲያኑ ስር በሚገኘው ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎችም ሞልተዋል፡፡ በቦታው ላይ ህጻናት፣ ነፍሰጡር እናቶች ሁሉ አሉ፡፡ ምግብ የለቻውም፡፡ ለመኝታ የሚሆን የሚለበስም ነገር የላቸውም፡፡ ቤቶቻቸውም ስለተዘረፉ ከቤታቸው ሊያመጡት የሚችሉት ምንም ነገር የለም፡፡ አፋጣኝ እርዳታና እርምጃ ካልተወሰደ ከባድ የሰብኣዊ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ስድስት ሰዓት ገደማም ሚካኤል ቤተክርስቲያን በር ላይ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትው ወዲያውኑ የሞቱ ሲሆን ትንሽ ቆይቶም አንድ ቆስሎ የነበረ ሌላ ሰውም ሞቷል፡፡
አብዲ ኢሌ በትናንትናው ዕለት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ሕዝቡን ማነጋገር ሲጀምር እና ብስኩት (ኮቸሮ) ለሕዝቡ መስጠት ሲጀምር የተመረዘ ሊሆን ይችላል በማለት አልተቀበሉም፡፡ በድጋሜ በልዩ ሃይሉ በኩል  ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች ዳቦ ያመጣ (አብዲ ኢሌ የላከ ቢሆንም)  ሁኔታ ቢኖርም ሕዝቡ የተመረዘ ሊሆን ይችላል በማለትም እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ነው የምንፈልገው በማለት አለተቀበለም፡፡
ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊትም ይሁን የፌደራል ፖሊስ የለም፡፡ ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ የገባው የከተማው ነዋሪዎች መያዣ (collateral) እንዳደረጋቸው፣ የፌደራል መንግሥት አብዲ ኢሌን የሚነካ ከሆነ ልዩ ሃይሉ እነሱ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነው የሚያስቡትም የሚሰማቸውም፤ የሚወራውም ይሔንኑ ነው፡፡
ኢንተርኔት በአካባቢው ስለማይሰራ እንጂ ልዩ ሃይሉ የወሰዳቸውን አሰቃቂ እርምጃዎች በሞባይላቸው ቀርጸው አስቀርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ መላክ ስላልቻሉ ለሕዝቡ ማጋራት አልተቻለም፡፡
አሁን ላይ የጅግጅጋም ሆነ የአብዲ ኢሊ ደጋፊ የሚበዛባቸው ከተማዎች ላይ የሚኖሩ በተለይ አማራ፣ ኦሮሞና ጉራጌዎች ምንም ዓይነት ጥበቃ የማያገኙ፣ ዕጣፈንታቸው በአብዲ ኤሊ ላይ የሚወሰን፣ የፌደራል መንግሥት ምንም ዓይነት ጥበቃ እንደማያደርግላቸው ረዳት አልባ ዜጎች ሆነዋል፡፡
Filed in: Amharic