>
5:13 pm - Friday April 20, 7184

አገር በጨረፍታ! (ደረጀ ደስታ)

አገር በጨረፍታ! ደረጀ ደስታ

(ደርሼ መጣሁ)

አዲስ አበባ አልተለወጠችብህም? 

 

እንደኔ 17 ዓመታትን ቆይቶ ለተመለሰ ሰው ይቺ ጥያቄ “ታዲያስ!” የማለት ያህል የትም እምትሰነዘር ጥያቄ ናት። መልሷ ግን እንደ ጠያቂና መላሹ ሄዶ ሄዶ “ፖለቲካ” ሊሆን ይችላል። ፖለቲካው አገርህን ምን እንዳደረጋት ለማየት ከፈለግክ ግን የኢትዮጵያ ናሙና ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ሂድ! ከተማዪቱ ኢህአዴጎቹ እርሳስና ላጲስ ይዘው እንደጻፉባት ወረቀት መስላኛለች። በእርሳሱ ውብ ነገር ጽፈው በላጲሳቸው ደግሞ የጻፉትን ውበት መልሰው እየደመሰሱ እንደሚሄዱ እድለ ቢስ ቀናተኞች አድርገህ ልታያቸው ትችላለህ። ሰው በገዛው ሥራው መልሶ ይቀና ይሆን ወይስ ከመጀመሪያውም ቢሆን ሥራው ራሱ የቀና ሰው አልነበረም እያልክ መፈላሰፍህም አይቀርም። የነበረውን በማጥፋት ብቻ ሳይሆን የሠሩትንም ሳይቀር መልሶ እስከማጥፋት ድረስ እሚሄድ የእልህ ፖለቲካ ግን ይገርምሃል። ወይም ደግሞ ከሠሩት ሥራ ይልቅ ያጠፉት ካበገነህ መራገም መሳደብህ አይቀርም። ምስጋና ቢስነትህንም ሳትዘነጋ፣ ማንበብና መጻፍ ሳይችል እርሳስ በጁ እንደገባ ሰው የተገኘው ነገር ሁሉ የተሞነጫጨረባት ባዶ ወረቀት አድርገህም ከተማዪቱን እምታይበት አጋጣሚም መከሰቱ አይቀርልህም።

በተረፈ ግን ሥራ ፈትና እንባ ፈት ሆኖ እንደሚያያት ጉንጭ አልፋው ፖለቲከኛ ካልሆንክ፣ ይቺ ከተማ አዲስ አበባም ፊንፊኔም አይደለችም። ደግሞ ይህን ሰምተህ ሌላ ስም እናውጣ አትበል እንጂ ከተምየዋስ በትልቅ ድማሚት ተደብልቃለች። አዱ ገነትን ልማትና ስደት አፈንድቶ አዝረክርኳታል። ስለ አዲስ አበባ መስክር ብትባል ምኑን ከምን አደርገህ ከየት ብለህ ትጀምራለህ? እውነታው ከስሜትህ ስሜትህ ከእውነታህ ተፈናቅሎልሃል። አገርና ሰው አብረው አይደሉም ብልህ ይገባህ ይሆን? ሰው ከአዲስ አበባ ብቻ አይደለም የተፈናቀለው። ኢትዮጵያም ወደ አዲስ አበባ ተፈናቅላለች። ባላገሩም ከያለበት ክልል ነቅሎና ተነቅሎ የገባ ይመስላል። አዲስ አበባ ተስፋፋች ማለት ህን ወደ ገጠር ገበሬው ደግሞ ወደ ከተማ እንደማለት ይመስለኛል፡፡ የከተሜውም ሰፈር ከሰፈር መፈናቀል ከመሃል ጫፍ መስፈንጠርም የተለመደ ነው። በሀሳብ ብቻ ሳይሆን በአካልም ወደ ውስጥ መሰደድ ሞልቷል። አገር ወደ ውስጥም ተፈናቅሏል። የተፈናቀሉት በተስፋና ስጋት ተጥደዋል። ሰው በዝቶ ችግር እንደ ሽሮ ፈልቶ እየተንተከተከ ነው። የለውጥ ተስፋ እንደ ጨው ተነስንሶ ሊመጣ ያለው ቀውጥና ነውጥ ለቅጽበት ተቀልብሶ ለአፍታም ቢሆን እፎይታ ሆኗል። ሰው እንደልቡ እያወራ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ስጋትና ምኞት ተቃቅፈው ተኝተዋል። ቢሆንም ቢሆንም አዲስ አበባም እንደ ኢትዮጵያ እጆቿን ብቻ ሳይሆን ህንጻዎችዋን ወደ ሰማይ ዘርግታለች።

በአዲሳባ እግርና ስሜት ለማፍታት ዎክ ሲያደርጉ ወደ ላይ ቀና ብሎ ማየት መተንፈስ ነው። ሰማዩም ደስ ያሰኛል። ወደ እግዚያብሔር የተዘረጉ ህንጻዎች አሉ። ወደታች ማየት ያው ታች ያወርዳልና ግን ደስ አያሰኝም። ህንጻ በየቦታው ነው። በጅምር ያሉት ብዙ ናቸው። መሬት መሬት አለማየት ነው። ፊለትፊት ማየቱም ቢሆን ቀላል አይደለም። መንገዱ በሰው ስለተሞላ 2 ሜትር ርቆ ማየት አይቻልም። በቃ ለእግዜር እንደሚናገር ሰው ዝም ብሎ ወደ ላይ ማንጋጠጥ ነው። እዚህም እዚያም ወደ ሰማይ እሚነጉደው ሰማይ ጠቀሱ ህንጻ ያስደንቃል። ግራውንድ ፕላስ ምንትስ የተባሉትን ባለ ሁለትና ሶስት ህንጻዎችን ሳትጨምር ያሉት ረጃጅም ህንጻዎች እየበረከቱ ነው። ቁጥራቸውም እንደተነገረኝ አስታውሳለሁ። መችና እንዴት እንደተቆጠሩም ተነግሮኝ ነበር። ረሳሁት። አይቼው አላውቅ ይመስል የሰው ብዛትና ጉስቁልናው አስደንግጦ አስረሳኝ።

ምንም ጥያቄ የለውም፣ “እንዲህ ነው እንጂ!” እሚያሰኝ መንገድ ተሠርቷል። ማቋረጫው ፣ማሳለጫው፣ ከላይ ከታች መሿለኪያው ደስ ይላል። ይሁን እንጂ እግረኛውና መኪናው በዝቶ በዚያ ላይ ሥርዓት ጠፍቶ አብዛኛው መንገድ ፈጥኖ አይወስድም ። ትራፊክ ተጨናንቆ መኪኖች ዳዴ ይላሉ፡፡ ብዙ ቦታም እየተሻሹ እሚሄዱ ይመስላሉ። አንዳንድ ቦታማ ከመቀራረባቸው የተነሳ እዚህኛው መኪና ውስጥ ተቀምጦ ወዲያኛው መኪና ውስጥ ያለውን ማርሽ መቀየር ያስችላል። ትራፊኩ አያነቃንቅም። ቄራ፣ መገናኛ ፣ገርጂ ወይም ቦሌ መድኃኒያለም አካባቢ ያለው መጨናንቅ ያስጨንቃል። ደግሞ ክረምትም ስለሆነ ጨቅይቷል። የተቦዳደሰው መንገድ ውሃ ቋጥሯል። አንዳንድ ቦታ መንገዱ ተፈትፍቷል። ጭቃው ለዓይንም ለእግርም ደስ አይልም። ጭቃውን እንደፈንጂ እንዳይረግጡት በጥንቃቄ ተሻገሮ ከተንጣጠለለው ቪላ ወይም ከተንጠራራው ፎቅ መግባት የተለመደ ነው። አንዳንዱ ቤትና ህንጻ ውስጥ ሲገቡ ለአፍታ ያህል ወደ ውጭ አገር የተሰደዱ ይመስል ፋታ ይሰጣል። በተለይ ከፎቅ መስኮት ሆነው ከላይ ወደታች እሚያዩ ከሆነ ከታች ሆነው ወደ ላይ የተመለከቱትን ውበት ይረሱታል። እዚያ አካባቢ ደስ እሚል ወዲያ ደግሞ ቅራንቅቦ ኮተት ….

ሥርዓት አልበኝነት የህዝባችን ተፈጥሯዊ ሀብቱ እየሆነ ይመስላል። መንገድን ሳያስተውሉ ወደ ተገኘበት አቅጣጫ ማቋረጥ ይቻላል። በዋን ዌይ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ይነዳል። ቀለበት መንገድ ላይ እጅን ከኪስ ከቶ መሄድ ይቻላል። ከመንገድ መሽናትና መጸዳዳት ድሮም የተለመደ ነው። የዛሬ ሶስት ዓመት ከመኪና ውስጥ ያሉ ልጆቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት ቀን ደንግጠው እንደነበር ባለቤቴ ነግራኛለች። አሁን እንዴት ናቸው ብዬ ጠየቅኳት። አሁንማ ለምደው እሚሸናውን ሰው ብዛት እየቆጠሩ እንደሚጫወቱበት ነገረችኝ። ለነገሩ አብሮን የኖረ ቅርሳችን ስለነበረ አልደነቀኝም። ፊትና ብልትን ሳይቀር ወደ ሰው አዞሮ መሽናት መስፋፋቱ ግን አስደንግጦኛል። ጌታ ሆይ አገሬን ጠብቅልኝ።

ይህም ይለወጥ ይሆናል። ዛሬ ዛሬማ እንኳን ፖለቲካው ሁሉ ነገር ቶሎ ቶሎ ይለዋወጣል። አየሩ ቀዝቅዞ ሞቆ ይበርዳል። ወዲያው ጥሎ እሚያባራ ዝናብ በየቀኑ ይታያል። ከከተማው ወጣ ካሉ ነፋሻው አየር ደስ ያሰኛል። አዲስ አበባ ግን ታጨሳለች። አሮጌ መኪኖቿም ያጨሳሉ፣ ያላለቁ ህንጻዎቿ ፍርስራሶቻቸውን ያቦናሉ። በየጥጋጥጉ የተወታተፉ ቆሻሾች በዝናብ ርሰው ጸሐይ ሲመታቸው ይተናሉ። የተነነው ይማጋል፡፡ የከባድ መኪናው ጭስ ግን አይን ይለበልባል፡፡ መቸም የሾፌር ባለጌ እንጂ የመኪና አሮጌ የለውም፡፡ ጃጅተውም ቢሆን መኪናም ከመንገድ ባለሥልጣንም ከወንበር አይወርዱም፡፡ከድሮይቷ ቮክስ ዋገን አነስቶ እነ ኤኔትሬ፣ ዚታዎና ትሬንታ ኳትሮ ሳይቀሩ አሁንም እንደነ አቦይ እና አባይ ብርቅዬ የአዲስ አበባ መኪኖች ለመሆን ሲሟሟቱ ይታያሉ፡፡
የድሮ አዲስ አበባን ለማየት ወደ ፒያሳና አራት ኪሎ ብሎም ሽቅብ ወደ ስድስት ኪሎ ማቅናት ነው። ለታሪክ ቅርስ እንዲቀመጥ የተባለው አሮጌው ከተማ ይበልጥ አርጅቶና ጃጅቶ እንዲሞት የተፈረደበት ሳይሆን አልቀረም። ያለ ዕድሜው ከርክሶና ጨርጭሶ እንዲያረጅ እየተገፋ ይመስላል። ያሳዝናል። (እንደ ፖለቲካችን ሁሉ) አዲሱ እንዲያምር የድሮው ማስጠላት አልነበረበትም፡፡ በተረፈ ሁሉም ቦታ ትርምስ ሆኖ የድሮ መርካቶን ይመስላል። የመኪናውን ቁጥር የተመለከተ፣ የሰውን ቁጥር አስልቶ ሊገምተው ይችላል። አቤት ህዝቡ!
ወጣት ይበዛል። እድሜያቸው ተመሳስሎ ቁመታቸውም የተከረከመ ይመስል አንድ ዓይነት ናቸው። የሸመገለው የጎለመሰው ብዙ አይታይም። አዲስ አበባ በወጣት ተጥለቅልቃለች። ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት ብለውኛል። የአገሪቱ አማካይ እድሜ 19 መሆኑን የሰማሁ መሰለኝ። አሮጌቷን አገር ወጣት እሚያደርጋት ከሆነ እሰየው ነው። ኮሽ ባለ ቁጥር ገንፍለው ወደ አደባባይ እሚሮጡ እነዚህ ወጣቶች ታግቶ እንደተለቀቀ ጥጃ ቧርቀው ሲያይዋቸው ደስተኞች ይመስላሉ። የኢንጂነር ስመኝው ቀብር ቀን ግን ሲቆጡ አይቻቸው ደንገጥ ብያለሁ። ለቁጣቸው ማብረጃ አንድ ሁለት ወያኔዎችን አሁኑኑ አሳልፋችሁ ጣል አድርጉልን ማለታቸው አላማረኝም፡፡ በዚያ ላይ ሥራ አጥተው ተስፋ ጠጥተው እስከመቼ እንደሚቆዩ አንድዬ ያውቃል፡፡ ከሩቅ በዝናና በቲቪ እማውቃቸውን ፖሊስ፣ ፌደራልና ወታደሮችንም ተጠግቼ አየዋቸው። ምንም እንኳ አዳዲሶች ቢሆኑም እነሱም ወጣት ብቻም ሳይሆኑ ልጆችም ናቸው። ይህ ሁሉ ሲታይ ራሱ ወጣት የሆነው የጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ አመራርም ብዙ ፈተና ይጠብቀዋል። ከእነ እስክንድር እና አንዷለም ጋርም ተገናኝተን አውግተናል። በለወጡ አኩርፈው መኖሪያቸውን ሳይቀር ለቀውና በነው ስለሄዱ ባለሥልጣናትም – ተመልከት ያ ቤት የማን መሰለህ… እያሉ ጭር ያለውን ሰፈር እያስጎበኙ ያጫወቱኝም ሰዎች ነበሩ። ሰው ሲያሳዝኑ የኖሩ ሰዎች ራሳቸው መልሰው ማዘናቸው ባይቀርም፣ ጊዜ አንስቶ ጊዜ እሚጥለውን ነገር ግን ሲያስቡት ይገርማል። አገሬ ግን ከጊዜ በላይ ሆና ሳያት ደስ ብሎኛል። እሚያልፈው ያልፋታል እንጂ እሷ ግን አታልፍም! ስጋትም ቢሆን እኮ ደንቧ ነው፡፡ ዛሬ እየተጋደለች ነገ እምትተቃቀፍ አገር ድንቅ አይደለች! አገር አለኝ በል! (ይቀጥላል)

Filed in: Amharic