>

"ወደ ሚኒሶታ ስንሔድ ህዝቡ በ11 ስታዲየሞች ተሰብስቦ ጠበቀን፣ ከዚያ በስንት ድርድር ወደ አንድ መጣ" (ዳንኤል ክብረት) 

“ወደ ሚኒሶታ ስንሔድ ህዝቡ በ11 ስታዲየሞች ተሰብስቦ ጠበቀን፣ ከዚያ በስንት ድርድር ወደ አንድ መጣ” 
ዳንኤል ክብረት 
.
” የኢሳቱ ብሩክ ይባስና አበበ ገላው ወዲያና ወዲህ የቆሙ ኃይሎች ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ሌት ተቀን የደከማችሁትን ድካም መቼም አልዘነጋውም “
.
የሦስት ወሩን አድካሚና አስደሳች ሩጫ አገባደድነው፡፡ አሁን የቀረን ዝርዝር ሪፖርቱን ተረጋግቶ መጻፍ ነው፡፡ ብዙ አስገራሚ፣ አሳዛኝ፣ አስደሳች፣ አስቂኝ ገጠመኞችን በቀጣዮቹ ቀናት አወጋችኋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በአሜሪካ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለማነጋገር ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ የታቀደው ግንቦት ወር ላይ ነው፡፡ የዳላሱ የኢትዮጵያውያን ስፖርት በዓል ግብዣ ሲመጣ ነገሩ ሌላ መልክ ይዞ ነበር፡፡ ጋባዡ ማን ነበር? ክልከላውስ ከየት መጣ? በብዕር ወደፊት እንራመድበታለን፡፡
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የርእሳነ መንግሥታት ታሪክ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎች በዋናነት ከአሜሪካ መንግሥት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሌሎች ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ የዲያስፖራው ጉዳይ በጎንዮሽ የሚያዝ ነው፡፡ የዚህኛው ጉዞ ዋናው ልዩነቱ በዋናነት ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡
ለአዲስ ሐሳብ አዲስ አካሄድ በሚል ጉዞውን የሚያስተባብረው ኮሚቴ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከባለ በጎ ፈቃድ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ የዳሰሳ ጥናት ተዘጋጀ፡፡ ዝርዝር ዕቅድ ወጣ፡፡ መጀመሪያ በዋሽንግተን ዲሲ በመቀጠል በሎስ አንጀለስ በመጨረሻም በሚነሶታ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ፡፡
እንግዳው ነገር ተጀመረ፡፡ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የቅንጅት፣ የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ፣ የግንቦት ሰባትና የሌሎቹም ፓርቲዎች አባላት በአንድ ኮሚቴ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ጥሪ ቀረበ፡፡ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው መጡ፡፡ በፓርቲ ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ዋነኛ የፖለቲካ አቀንቃኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጎረፉ፡፡ ተያይተው የማያውቁ፣ ተደማምጠው የማያውቁ፣ በአንድ ላይ ተቀምጠው የማያውቁ፣ ቢገናኙ የሚደባደቡ ኃይሎች ተሰበሰቡ፡፡ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐረሪ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ አፋር፣ ኮሙኒቲዎች ሰዎችን ላኩ፡፡
ይህ ክስተት ለኤምባሲውም፣ ለተሰብሳቢውም፣ ለእኛም፣ ለመንግሥትም፣ ለማኅበረሰቡም አዲስ ነው፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆኑ ኤምባሲዎቹ ከጥቂት፣ ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንጂ እንዲህ እንደ ነዳይ ምግብ ውጥንቅጣቸው ከወጣ ዳያስፖራዎች ጋር በሰላም ተገናኝተው አያውቁም፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በሽምግልናና በልመና ነው ያለቁት፡፡ አንዱ አንዱን ማየት አይፈልግም፡፡ ‹እገሌ ከመጣ እኔ እወጣለሁ› ይላል፡፡ ‹ስሜ ሲጠራ ከነ እገሌ ቀጥሎ መጠራት የለብኝም› ብሎ ያኮርፋል፡፡ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ አልፋቤትን ለመጠቀም ተሞከረ፡፡ መጀመሪያ የሚጠሩት ሲደሰቱ መጨረሻ የሚጠሩት ቅር ይላቸዋል፡፡ ችግሩን በኮሚቴው ውስጥ ተነጋግሮ በስምምነት ወይም በድምጽ ብልጫ ከመወሰን ይልቅ ‹ይህንን ካልተቀበላችሁ መግለጫ አወጣለሁ፣ ሰልፍ አደርጋለሁ፣ ቦይ ኮት አደርጋለሁ› የሚለው ብዙ ነው፡፡ እገሌን እዚህ ቦታ እንዳናያው ብሎ በማኅበር፣ በኮሙኒቲ፣ በፓርቲ፣ አስወስኖ፣ የሺዎችን ፊርማ አሰባስቦ የሚመጣ አለ፡፡
ይህ በየምሽጉ ሲታኮስ የኖረ ማኅበረሰብ ተግባብቶ፣ ተስማምቶ፣ ተጣጥሞና ተማምኖ ያንን አስደናቂ ሥራ እንዲሠራ ሌት ተቀን መሰብሰብ፣ ጆሮ እስኪቃጠል በስልክ ማውራት፣ በየሆቴሉና ካፍቴሪያው እየዞሩ ማግባባት፣ በሚያውቋቸው ሰዎች በኩል ማስረዳት፣ አንዳንዱን እንዳላዩ ማለፍ፣ ሌላውን ፊት ለፊት መጋፈጥ፣ ከአንዳንዶች ጋር መከራከር፣ ከአንዳንዶችም ጋር መደራደር አስፈልጎ ነበር፡፡ ለሁሉም የሚሆን፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ቢያንስ ልብ የሚሰጠው ሁነና ሰው ማግኘት እንዴት ከባድ ነበር፡፡ አንድነቱ ዶክተር ዐቢይን በመቀበል የተመሠረት ቋሚ (vertical) እንጂ እርስ በርስ በመግባባትና በመተማመን የተገነባ የጎንዮሽ(horizontal) አልነበረም፡፡
ተቦክቶ፣ ተንተክትኮ፤ በጭድና በውኃ ተጣብቆ አንድ እንደሚሆን ጭቃ፣ ከብዙ ውይይት፣ ክርክር፣ ጭቅጭቅና ትግትግ በኋላ የጎንዮሹ አንድነት እየተገነባ መጣ፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የኮሚቴዎች አባላት ኤምባሲና ቆንስላ መጥተው አያውቁም፡፡ አንዳንዶቹም የሚመጡት ለተቃውሞ ነው፡፡ ለቆንስላ ጉዳዮች የሚመጡትም ወደ ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ እዚያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ መግባት ዋጋ ያስከፍል ነበር፡፡ ያስወግዛል፣ ያሰድባል፤ ያስገልላል፡፡ ‹እንዳያልፍ የለም ያ ሁሉ አለፈ፡፡› መግባባቱ ሲመጣ ኤምባሲው ለሥራ በሚሠማሩ ዜጎች ተሞላ፡፡ በሚወያዩ፣ በሚያቅዱና መፍትሔ በሚያፈላልጉ የኮሚቴ አባላት የሚያሸበርቀውን ኤምባሲ ያየ ለኮንደሚኒየም ምዝገባ የመጡ እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል የሚተጉ ናቸው ብሎ ለማመን ይቸገራል፡፡ የዲሲ ኤምባሲና የሎስ አንጀለስ ቆንስላ የተቃውሞ ሰልፍ ሲናፍቀው ማየት አስገራሚ ነበር፡፡ ያቺ መከረኛ ሰንደቅም ሰላም ውላ ሰላም ማደር ጀመረች፡፡ በባለ ኮከቡ ባንዴራ ያልተስማሙም እናውርድ ብለው አያስቸግሩም፡፡ የራሳቸውን ባንዴራ ይዘው መጥተው ትከሻቸው ላይ ያውለበልባሉ፡፡
ክርስቶስ በምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜ የነበሩ ሰዎች በብሉይ አመለካከት ሐዲስን እየተቀበሉ ነበር፡፡ የተማሩት፣ የኖሩበት፣ የለመዱትና የሚያውቁት ብሉይን ነው፡፡ ጠባያቸው፣ ባሕላቸውና አሠራራቸው ብሉይ ነው፡፡ ነገር ግን በሐዲስ ኪዳን መንገድ ውስጥ ናቸው፡፡ በአሜሪካ የነበረውም እንዲህ ነው፡፡ከዚህ በፊት መሪን መቃወም እንጂ ከመሪ ጋር መሥራትና መሪን መደገፍ አልተለመደም፡፡ መሪን ለመቃወም ድርጅቶች ተመሥርተዋል፣ ቡድኖች ተዋቅረዋል፤ መፈክሮች ተዘጋጅተዋል፣ ሚዲያዎች ተፈጥረዋል፤ ዜማዎች ተዚመዋል፤ ፖስተሮች ተቀምረዋል፡፡፡ ቢያንስ የ40 ዓመት ልምድ አለ፡፡ የአንድ ትውልድ ልምድ፡፡ መሪን ለመቀበልና መሪን ለመደገፍ ግን የተዘጋጀ ነገር የለም፡፡ ምንድን ነው የሚባለው? እንዴት ነው የሚደረገው? ብዙዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ዘመነ ነው የሚያስታውሱት፡፡ ዕንቁላልና ቲማቲም ከውርወራ ተርፈው ሳንዱች ተሠራባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣናትም በአሜሪካ ከተሞች ላይ እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ከትተው ያለ መሸማቀቅ መራመድ ጀመሩ፡፡
እስከዛሬ ድረስ ስንቃወም ‹ሼም ኦን ዩ› እንላለን፡፡ አሁን ለድጋፍ ‹ምን ኦን ዩ› ነው የምንለው? ብሎ እንዳሳቀኝ ልጅ፡፡
አስተሳሰባችንና አሠራራችን፣አደረጃጀታችንም የድሮ ነው፡፡ ፍላጎታችን ግን የዛሬ፡፡ አዲሱን ሐሳብ በድሮው መንገድ ነበር የምንሠራው፡፡ ተስፋው እንጂ ባሕሉ ገና አልመጣም፡፡ አንድ የሆነ ቡድን ቅሬታ አለኝ ብሎ ሊያናግረን ቀጠረን፡፡ ሚኒስቴር ዲኤታዋና አምባሳደሩ ከፕሮቶኮሉ መሥመር ወርደው ሰዎቹ የፈለጉት ቦታ ላይ ተገኙ፡፡ ቅሬታ ያሉትን አቀረቡ፡፡ እንዴው መቼም ቅሬታ እጥረት ስለተፈጠረ እንጂ ነገሩስ እዚያው በኮሚቴ የሚያልቅ ነበረ፡፡ በመጨረሻ ተስማማን፡፡ ከውይይቱ ስንወጣ እነዚያው ሰዎች ከኛ ጋር እየተወያዩ ባሉበት በዚያ ሰዓት በጎን የተቃውሞ መግለጫ አውጥተው ጠበቁን፡፡ አልገረምን፡፤ አንዳንድ ጥይት ይባርቃል፡፡ ነጥብ ማስቆጠር የኖርንባት ስልት ናት፡፡ ሤራ ተሠርቷል፣ ሼር ተሸርቧል፤ በምሥጢር እንዲህ ተደርጓል፣ እነ እገሌ ‹ሃይጃክ› አድርገዋል፣ ሰነድ ወጣ ሰነድ ገባ፣ የሚሉት ነገሮች አዲሱን የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ለማስቀመጥ ሲታሰብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ያው አባታችን ጴጥሮስ ከፍቅር መምህሩ ከክርስቶስ ጋር እየዋለ በመጨረሻ ሰይፍ መዝዞ አልነበር? የኖሩበት ነገር በአንዴ አይተውም፡፡
በፖለቲካ ድርጅቶች መድረክና በምሁራን መድረኮች የታዩ አስደሳችና አስገራሚ፣ አሳዛኝና ልብ አውላቂ ነገሮችን ወደፊት እመጣባቸዋለሁ፡፡ በፊደላውያንና በምሁራን መካከል ያለውን ሰፊ ርቀት ለማየት እነዚህ መድረኮች ምቹ ነበሩ፡፡ ዕውቀታቸው የተደላደለ፤ ብስለታቸው የነጠረ፤ ሐሳባቸው የጠራ፤ ጥበባቸው የላቀ ምሁራንን አይተናል፡፡ ኢትዮጵያ እነርሱን በማግኘቷ የሚቆጫት፡፡ በዚያ ማዶ ደግሞ እነ ሆድ ይፍጀውንም ታዝበናል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ አባላትና በፖለቲከኞች መካከል ያለውን እንደ አልዓዛርና ነዌ ማዶ ለማዶ የተቀመጠ ልዩነት ለመገንዘብ ከዚህ የተሻለ ዕድል አልገጠመኝም፡፡ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከቅዱስ አትናቴዎስ ተሾሞ ሲመጣ የኦሪት ትምህርት እያስተማሩ ያገኛቸውን የኢትዮጵያን ሊቃውንት እንዴት የሐዲስ ሊቃውንት እንዳደረጋቸው ከታሪካችን መማር ያስፈልገናል፡፡ በኢትዮጵያ የዕውቀትና የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ብሉይን ከሐዲስ የማጣጣም ችግር አለ፡፡ ከታሪክ ተቆርጦ ትናንት ላይ የመቅረት ዕጣ፡፡
በዚህ ሂደት ያየናቸው ለሀገራቸው ያለ ምንም ዋጋ ለማገልገል በእሳትና በውኃ መካከል የሚያልፉ ጀግኖችም አሉ፡፡ የትውልድ ድልድይ አባላት እስከ ቀራንዮ ያደረጉት ተጋድሎ ዕጹብ ዕጹብ ያሰኛል፡፡ ብዙዎቹ የዲሲ ግብረ ኃይል አባላት ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁመው የታገሉት ትግል አስደናቂ ነበር፡፡ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ባለቀ ሰዓት የተቀበለችውን ኃላፊነት ለመወጣት የለፋችው ልፋት የማይረሳ ነው፡፡ የቪኦኤ፣ የኢሳት፣ የዓባይ ሚዲያ፣ የአዲስ ድምጽ፣ የኦ.ኤም.ኤን፣ የቲጂ ቲቪ፣ ጋዜጠኞች ከግራ ከቀኝ የሚመጣውን ሁሉ እየታገሉ ለዝግጅቱ መሳካት የከፈሉት ዋጋ በታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ በጄኔቫ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ የነበረው ዝግጅት እንዲሳካ ባሕር ማዶ እየተሻገሩ ለማወያየት፣ ለማቀራረብ፣ አንዳንዶችንም ለመምከርና ለመገሠጽ የሄዱበት ርቀት እንኳን ዐወቅናችሁ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ከሆቴል እስከ ኮንቬንሽ ሴንተር የነበረው ቅንጅት ከ ‹ዩ ስትሪት ፓርኪንግ› ባለቤት ከሄኖክ ተስፋዬ ውጭ አይታሰብም ነበር፡፡ ከመቶ በላይ መኪኖችን በማቅረብ ያለ ዕረፍት የሠሩት የዲሲዎቹ ባለ መኪኖች፣ ሕዝቡን በትጋት ያመላለሱት የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ባለ ታክሲዎች አገልግሎት እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነው፡፡ ለመስተንግዶውና ለቅንጅቱ የደከሙት የዋሽንግተንና አካባቢዋ ወጣቶች ተስፋን የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡
የአቶ ነአምን ዘለቀ ባለቤት ሕይወት ለሀገሯ የሠራችውን ታላቅ ሥራ ይህ ትውልድ ሲያስታውሰው እንዲኖር ወደፊት በዝርዝር እጽፈዋለሁ፡፡ የኢሳቱ ብሩክ ይባስና አበበ ገላው ወዲያና ወዲህ የቆሙ ኃይሎች ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ሌት ተቀን የደከማችሁትን ድካም መቼም አልዘነጋውም፡፡ በዲሲው የኮንቬንሽ ሴንተር ጉባኤ የነበረው የፍቅር ትዕይንት ከእናንተ ውጭ ሊታሰብ አይችልም ነበር፡፡ አምልጦን የነበረውን ያንን ክስተት ወደ ተገቢው ቦታ የመለሳችሁት እናንተ ናችሁ፡፡
ያንን እንደ ሐምሌ ማዕበል እየተጎማሸረ የሚመጣ ዲያስፖራ በትዕግሥትና በጥበብ፣ ሳይታክቱ በማገልገል፣ ስድቡንና ርግማኑን፣ ቁጣውንና ተቃውሞውን ችለው፣ ከላይና ከታች እንደ ገና ዳቦ እየተለበለቡ ታሪክ የሠሩት የዲሲ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ናችው፡፡ በዚህ የታሪክ መለወጫ ምዕራፍ ላይ ብዙዎቹ ነገሮች ያለ እነርሱ ሊሳኩ አይችሉም ነበር፡፡ ተጨቆንን፣ ተገለልን፣ ኮታችን አነሰ፣ ለኛ ኮሙኒቲ በቂ ቦታ አልተሰጠም፣ ከሥልጣን ድልድሉ ተገቢውን ሥፍራ አላገኘንም፣ የሚለውን ፍላጎት ሁሉ ማቀራረብ እንዴት ፈታኝ ነበር?
ውቧ ከተማ ሎስ አንጀለስ፣ የጨዋዎች ሀገር፡፡ ትምህርት ለሀገር ምን ያህል እንደሚጠቅም በተግባር አሳያችሁን፡፡ ምዕራቡ አሜሪካ ለትምህርት የሚመረጠውን ያህል ለኑሮ ይቆነጥጣል፡፡ ውድ ነው፡፡ አብዛኞቹ የኮሚቴዎቻችን አባላት ዕውቀት ቀመስና ጥበብ ጠገብ በመሆናቸው ሎስ አንጀለስ ላይ ሺ ዓመት መሥራት አይከብድም፡፡ ሥራቸውን ሁሉ በሰነድ አዘጋጅተው፣ በዕቅድ ተመርተው፤ ለመግባባት ፈጥነው፤ እንዴት ያስደንቁ ነበር፡፡ ከቆንስላ ጄነራሉ ጀምሮ በየሥራው የተሰለፉት የቆንስላው ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች በመካከል ገጥሟቸው የነበረውን ፈተና አልፈው እንዲያ ለዘላለም ከዓይነ ኅሊና የማይጠፋውን መርሐ ግብር ሠርተዋል፡፡ እንደነ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማርያምና ኤልያስ ወንድሙ(ፀሐይ አሳታሚ) ያሉ ሊቃውንት ለሎስ አንጀለስ ሞገሶቿ ነበሩ፡፡ ጥያቄን ሎስ አንጀለሶች ይጠይቁት፡፡ ቁም ነገር፣ ወደ ገደለው፣ በሰዓቱ፣ ያለ ረብሻ፡፡ በጥበቧ ከተማ ጥበብን አይተንባታል፡፡
ሚነሶታ መጀመሪያ ስንደርስ በአሥራ አንድ ስታዲዮም የነበረው ሕዝብ ነው ብዙ ተደክሞበት ወደ አንድ ስታዲዮም የመጣው፡፡ ብዙ ያልታከሙ ቁስሎች ያሉባት ከተማ ናት ሚነሶታ፡፡ በኦሮሞ ኮሙኒቲ ስም ችግር ፈጥረው ሕዝብን ሊያቃቅሩ የነበሩትን ሰዎች ኮሚኒቲው ራሱ ታግሏቸዋል፡፡ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ሽቱው ውስጥ የገቡት ዝንቦች ለማበላሸት ቢሞክሩም ሁሉን አቀፍ የሆነውን ዝግጅት ለማዘጋጀት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደረጉ፣ የሀገሪቱ አንድነት ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው፣ ጽንፈኝነት የሚያበሳጫቸው፣ ማዶ ለማዶ መሆን የሰለቻቸው አያሌ ወገኖቻችን ነበሩ በሚነሶታ፡፡ በአንድ በኩል የቆንስላ ጽ/ቤት በቦታው አለመኖር የተቀናጀ አመራር እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተፋጠጡ ኃይሎች መኖር ሥራውን ፈትኖታል፡፡ የሌሎች ኮሙኒቲዎች ጠንካራ አለመሆንም ሥራውን ወደ ተወሰኑ ሰዎች ትከሻ ጭኖታል፡፡ ከተንኮልና ከወረደ ሥራ ጋር በአንድ በኩል፤ ከጽፈኝነትና እኔ ብቻ ከሚለው ስሜት ጋር በሌላ በኩል ስንገዳደር ነው ሁለቱ ቀን ያለቀው፡፡
ዶክተር ዐቢይና ኦቦ ለማ መገርሳ በቆራጥነት ያስተላለፏቸው መልእክቶች ወሳኞች ነበሩ፡፡ ይህንን ዓይነት መልእክት በተለይ አዲሱ ትውልድ መስማት ነበረበት፡፡ የዚያ መድረክ አንዱ ጥቅም ይህንን መልእክት እንዳይሰማ ተጋር የነበረው ትውልድ በግላጭ መልእቱን ለማግኘት መቻሉ ነው፡፡ በሦስቱም የሚነሶታ ፕሮግራሞች ጽፈኝነት የሚያደርሰንን የመጨረሻ ገደል ለማሳየትና አንድነታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መሪዎቹ በአጽዖት አስረድተዋል፡፡ በጎንዮሽ ውይይቶችም ይሄንኑ አስረግጠውታል፡፡
ይህ ግን የረዥሙ መጀመሪያ ነው፡፡ በተለይም ማክሰኞ በተደረገው የኦሮሞ ኮሙኒቲ ስብሰባ ላይ ዶክተር ዐቢይም ሆኑ አቶ ለማ አሰፍስፎ የነበረውን፣ ዐቅም ቢያጣም ችግር ለመፍጠር የሞከረውን አክራሪ ኃይል ተሻግረው ትውልዱን በሀገሩ አንድነት ላይ ወሳኝ ሚና እንዲጫወትና ዕድሉን አሳልፎ እንዳይሰጥ ድልድዩን ሠርተውለታል፡፡
ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው ዋጋ ሰይጣን ነጻ አልወጣም፡፡ የብሉዩም ሆነ የሐዲሲ ሰይጣን ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰይጣን ይዟቸው የነበሩ ሰዎች ግን ነጻ ወጥተዋል፡፡ በዚህ ጉዞ ጽፈኞች፣ አክራሪዎች፣ እኔ ከሞትኩ ባዮችና ከሕዝብ መከራ አትራፊዎች ነጻ አልወጡም፡፡ እነርሱ በነበሩበት ናቸው፡፡ እነርሱ ይዘውት የነበረው ሕዝብ ግን ነጻ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ እንጀራ መግዛት ትልቅ ፖለቲካ በነበረበት አሜሪካ፣ መንግሥት በሚጠራው ስብሰባ መገኘት በደል በነበረበት አሜሪካ፣ አገር ቤት ቶሎ ቶሎ መመላለስ በሚያስጠቁርበት አሜሪካ፣ ያ ሁሉ አልፎ ሕዝብና መንግሥት በአንድ አዳራሽ ውስጥ በሰላም ሲገናኙ ማየት ‹በሕልሜ ነው በእውኔ ወይስ በቴሌቭዥን› ያሰኛል፡፡
ዕንቅልፍ አልነበረም፡፡ በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ አልተኛንም፡፡ አንዳንዱን ሆቴል ሳንተኛበት ከፍለንበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ቁርስና ምሳ አልፎናል፡፡ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያና የአሜሪካ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሌት ተቀን ተደክሟል፡፡ በሰኔ 16ቱ ክስተት የተነሣ አሜሪካኖቹ ጥበቃውንን ከፍ አድርገውታል፡፡ በዚህም የተነሣ ረጃጅም ሰልፎች ተፈጥረዋል፡፡ አንዳንድ ሰልፎችም ተቆርጠዋል፡፡ እገሌ እንዲህ ሊያደርግ ነው ተጠንቀቁ፣ እነ እገሌ እንዲህ አስበዋልና ንቁ የሚባሉ ወሬዎች አሁንም አሁንም ይመጣሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የእሳት ማንቂያ (Fire alarm) ጥበቃ ላይ የነበረው የተሳካ ሥራ ስብሰባዎቻችንን ከዕንቅፋት የታደገ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በሚደረጉ ስብሰባዎች የሚቃወሙ ሰዎች የእሳት ማንቂያ ያለበትን የመስተዋት ሳጥን ሰብረው ደወሉን(አላርሙን) በማስጮህ ሕዝቡ አደጋ መጣ ብሎ እንዲበተን ያደርጉ ነበር፡፡ ይህን ለመከላከል እያንዳንዱ የደወሉ ሳጥን በተመደቡ ሰዎች ትከሻ እንዲሸፈን ተደርጎ ነበር፡፡
ከ14 በላይ ሕዝባዊ መድረኮች ተከናውነዋል፡፡ ከልዩ ልዩ ታላላቅ ግለሰቦችና አካላት ጋር ከ23 በላይ የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ‹ወዳጅህ ጠላት እንዲሆን አንድም ዕድል አትስጠው፣ ጠላትህ ግን ወዳጅህ እንዲሆን አንድ ሺ ዕድል ስጠው› የሚለውን በተግባር አይተናል፡፡ ከተጠቀምንበት አሁን አዲስ ነገር ተፈጥሯል፡፡ ተስፋ የሰነቀው የማዶው ወገን የአዎንታዊ ለውጥ አካል እንዲሆን በርትተን ከሠራን ኢትዮጵያን እናሻግራታለን፡፡ መልሰን ከተኛን ግን ከዚህ በኋላ ቀስቃሽ ማግኘታችንንም እንጃ፡፡
Filed in: Amharic