>
5:13 pm - Monday April 19, 8371

ስም እና ግብር (ከይኄይስ እውነቱ)

ስም እና ግብር

ከይኄይስ እውነቱ

ይህንን ስም (‹‹ኢሕአዴግ›› የሚባለውን ማለቴ ነው) ለመጥራት ባልፈልግም ዛሬ ለምጽፍበት ርእሰ ጉዳይ የግድ ነውና በዚህ አስተያየቴ ውስጥ አነሰዋለሁ፡፡ ይህ ስም ወያኔ ትግሬ በራሱ መልክና አምሳል ጠፍጥፎ የሠራቸው÷ ሲጠራቸው አቤት ሲልካቸው ወዴት እያሉ ወያኔ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በጠላትነት በመፈረጅ ለፈጸማቸው ግፍና በደሎች መሣሪያ በመሆን በባርነት/በሎሌነት ሲያገለግሉ ለነበሩ ሦስት ድርጅቶች ‹‹ሀገር አቀፍ›› ቅብ በመቀባት ለፈጠረው ግንባር የሰጠው ስያሜ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ‹‹ግንባሩ›› እያልኩ እቀጥላለኹ፡፡ ወያኔ/ሕወሓት ላለፉት 27 የጨለማ ዘመናት ብቸኛ የአናሳ ጎሣ ገዢ ‹ፓርቲ› ነው እንዳይባል የተከለለበት ጭምብል ነው ግንባሩ ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ስም ጋር አቆራኝቶ የሚያየው ግፍ፣ በደል፣ ጭቆና፣ ሰቈቃ፣ ባጭሩ የአገርና የኢትዮጵያውያንን ውርደት በመሆኑ ይህንን ስም ለመጥራትም ለመስማትም ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም ግንባሩ በተነሳ ቊጥር ሕዝባችን የሚያስታውሰው ወያኔ ትግሬ በአካልና በስነ ልቡና ያደረሰበት በቃላሉ የማይሽር ሕማም ነውና፡፡

በሌላ በኩል ግንባሩን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ግብሩን ያሻሽልልን ሳይሆን በዚህ ግንባር ስም የተሰባሰቡት የጎሣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ ለተፈጸሙት ተወዳዳሪ የሌላቸው ግፎችና በደሎች በጋራና በተናጥል ተጠያቂ በመሆናቸው (እውነትንና ብሔራዊ ዕርቅ በማስፈን ሂደት የሚታለፉ የጥፋት ዓይነቶችን ሳይጨምር) በሕግ የበላይነት በሚቋቋም የፍትሕ ሥርዓት ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ነው፡፡

አቶ ለማንና ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ ንጽሕናቸሁን የምትተማመኑ የግንባሩ አባለት ካላችሁ ጎሣ መሠረቱ ያልሆነ አዲስ ፓርቲ መሥርታችሁ የተጀመረውን ለውጥ መሠረታዊ በማድረግ ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ አመለካከት ሥጋ የለበሱ አጋንንት ስብስብ የሆነውን ሕወሓት በጭራሽ አይመለከትም፡፡ ወያኔ ትግሬን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹የሩቢከንን ወንዝ ከተሻገረ›› ቆይቷል፡፡ በአገር ክህደት፣ በዘር ፍጀት/በጅምላ ግድያ፣ በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የመጨረሻ የሚባለውን፣ መንግሥታዊ አሸባሪነት እና ሌሎች በይቅርታ የማይታለፉ ወንጀሎችን ንቅስ አድርገው ለመፈጸማቸው ከጥርጣሬ በላይ የሆኑ ማስረጃዎች በመኖራቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ርትዕ ማግኘት ይገባዋል፡፡ ባንፃሩም የፓርቲ ንግድ ድርጅቶቹ ከመነሻው የሕግ መሠረት ስለሌላቸው (በስማቸው የተወሰደውን ብድር ከነሕጋዊ ወለዱ መክፈልን ጨምሮ) ንብረቶቹ በሙሉ ተወርሰው ለሀብቱ ባለቤት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም መዋል ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ርምጃ በሌሎች የግንባሩ ፓርቲዎች ስም የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶችንም ይመለከታል፡፡

ካነሳሁት ርእስ ጋር በቀጥታ ባይያያዝም ጠ/ሚ ዐቢይ በስደት በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ኢትዮጵያ ንጽሕናን ከቅንነት÷የሞራል ልዕልናን ከዕውቀት አጣምረው የያዙ ዜጎች የሌላት ይመስል በወያኔ አጥፊ አስተሳሰብ የተቃኙና (በቀላሉ ሊለወጡ የማይችሉ) የማሰብ ሥራ ከላይ ወደታች ሲወርድላቸው በቆዩ በግንባሩ ሰዎች (የፈለጉትንም ዓይነት የት/ት ዝግጅት ይኑራቸው) ለመጠቀምና እነሱንም ይዞ ለመቀጠል ያሳዩት አመለካከት ብዙዎችን በእጅጉ ቅር ያሰኛና ምሳሌ ከሆኑት የለውጡ መሪ የማይጠበቅ መልስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ አዲስ ‹ደም› ቀላቅሎ ለመሥራት ፍላጎት የማጣት፣ እምነት ያለመኖር ወይም የተለየ ሥጋት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ይህ ዓይነቱ አመለካከት ‹መደመር› ከሚለው አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም መሆኑን ነው፡፡ እንደነ አረጋዊና አብዲ ኢሌ ‹የመደመርን› ሃሳብ ያኮስሰዋል፡፡

በመጨረሻም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን የትርርታውን ስሜት (excitement) እና ሆያ ሆዬው ኃላፊ በመሆኑ ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚበጀውን (በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ጭምር እየተደረገ ያለውን) በማስተዋል፣ በመደማመጥ፣ በስክነት፣ በዕውቀትና በጥበብ እንድንመለከተው በትህትና እጠይቃችኋለኹ፡፡ የትኛውንም በጎ አሳብ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ከሁሉም አስቀድሞ አገር መረጋጋት ይኖርበታል፡፡ ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየን በአራቱም ማዕዝናት ውጥረት ውስጥ መሆናችንን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዶ/ር ዐቢይ የሰጠው መልስ አብዛኛው ቅር የተሰኘበት ነው፡፡ በታሪካችን ያልተሄደበትን መንገድ መምረጡ ቢገባንም፣ የገጠመን ታሪካዊ ባላጋራ ግን በታሪካችን ከተከሠቱት የተለየና አገርን ለመበተን የተማማለ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ጎሣ/ነገድ ይቀየማል ማለት ልንፋታው የምንፈልገውን የጎሣ አስተሳሰብ ማሰቀጠል አይሆንም? የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ ደግሞ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ ለአገር ህልውና እና ለዜጎች ደኅንነት ሲባል ሕግ የማስከበሩን ኃይል ባግባቡ መጠቀሙ ጠ/ሚንስትሩ ከመረጠው መንገድ ያወጣዋል ብዬ አላስብም፡፡

Filed in: Amharic