>
5:13 pm - Sunday April 19, 9091

የቂሊንጦ፤ የቃሊቲ፤ የሸዋ ሮቢት እና የድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከሃላፊነታቸው ተነሱ!

የቂሊንጦ  ፤ የቃሊቲ፤ የሸዋ ሮቢት እና የድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከሃላፊነታቸው ተነሱ!!!
አዲስ አድማስ
ታራሚዎች ከፍተኛ የሠብዓዊ መብት ጥሠቶች እንደሚፈፀምባቸው ለቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በምሬት መግለፃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የቃሊቲ ፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋ ሮቢትና ድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ታውቋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዲሱ ጴጥሮስ እንደተናገሩት  የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ዳይሬክተር ገብረኢየሱስ ገብረ እግዚአብሄር ፣ የቂሊንጦ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት  አስተዳደር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ሃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት የማነ አስፋው እንዲሁም የድሬዳዋ ማረሚያ ቤት ዳይሬክተር መኮንን ደለሣ ከስልጣን ተነስተው በአዳዲስ አመራሮች ተተክተዋል፡፡
በማረሚያ ቤቶቹ የሚገኙ ታራሚዎች ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶች እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለደብደባ ፣ ለእንግልትና ለአካል መጉደል መዳረጋቸውንም በተከታታይ ለቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ሲገልፁ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የምህረት አዋጅ ዝርዝር አፈፃፀም ይፋ መደረጉን ተከትሎ “ለምን እኛን አያካትትም” የሚል ጥያቄ ያላቸው ታራሚዎች፤ በተለያዩ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ የሰነበቱ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መረጋጋት መፈጠሩን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡
ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መካከል ቂሊንጦ፣ ቃሊቲና እና ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከታራሚዎች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩ መፈታቱን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ ማረሚያ ቤቶቹ ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሠው ከሐሙስ ጀምሮ ቤተሠብም ታራሚዎችን መጠየቅ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ተመሳሳይ ተቃውሞ በክልል አስተዳደሮች ስር በሚገኙ በመቐለ ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በደብረማርቆስና በወልዲያ ማረሚያ ቤቶችም ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን በማረሚያ ቤቶቹ ላይም የእሣት ቃጠሎ ተከስቷል ፡፡ የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙም ተጠቁሟል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚንስትር ዴኤታ አቶ ካሣሁን ጎፌ ሰሞኑን በሠጡት መግለጫ፤ ታራሚዎች በዚህ መልኩ የሚያቀርቡት ከእስር የመፈታት ጥያቄ በህግ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡
Filed in: Amharic