>

የመቀሌዉ ህዝባዊ ሠልፍ ሠምና ወርቅ (ያሬድ ደምሴ)

የመቀሌዉ ህዝባዊ ሠልፍ ሠምና ወርቅ

ያሬድ ደምሴ

መሳሙን ወደሽ ጢሙን ጠልተሸ!

የሃምሌ ሃያ አንዱ የመቀሌ ህዝባዊ ሠልፍ ሠምና ወርቅ ያለዉ ቅኔ ነገር ነዉ፡፡የሠልፉ ሰም የኢትዮ-ኤርትራን እርቀ ሰላም መደገፍ ሲሆን የሠልፉ ወርቅ ደግሞ ዶ/ር አብይን ማመስገንና እዉቅና መስጠት ነዉ፡፡ብዙ ሰዉ ሰሙ ላይ አትኩሮ ወርቁ ተጋርዶበት እንጂ የኢትዮ ኤርትራን ሰላም ያወደሰ ማህበረሰብ ሰላሙ እዉን አንዲሆን ያደረገዉን መሪ እያወደሰ መሆኑ ጠፍቶት አይደለም፡፡መቼስ ዉጤት ሲወደስ ወጤቱን ያመጣዉ አካልም እየተወደሰ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡

የመቀሌዉን ሰልፍ ከሌላዉ ክልል ሰልፍ የሚለየዉ በርካታ ነገሮች እንዳሉ ግልጽ ነዉ፡፡የመጀመሪያዉ ልዩነት በሌላዉ ክልል የተካሄደዉን ሰልፍ ያደራጀዉና የመራዉ ህዝቡ መሆኑ ነዉ፡፡የክልል አመራሮችን ሰልፉ ላይ እንዲታደሙ የጋበዘዉም ራሱ ህዝቡ ነበር፡፡ በመቀሌዉ ሰልፍ ላይ ግን ክልሉን የሚመራዉ ግንባር ነዉ ህዝቡን ለሰልፍ የጠራዉና የመራዉ፡፡ ለዚህም ነዉ የመቀሌዉ ህዝባዊ ሰልፍ የዶ/ር አብይን ጅምር ጥረትና ስኬት በገሃድ ለመደገፍና እዉቅና ለመስጠት በሚል ዓላማ ሊደረግ ያልቻለዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ ህወሃት ለዶ/ር አብይ መልካም ጅምርና ጥረት በአደባባይ እዉቅና ለመስጠት ለዘመናት የሰረጀዉ እብሪተኛ ባሃሪዋ አይፈቅድላትም፡፡የዶ/ር አብይ በህዝብ ዘንድ መወደድ እንቅልፍ ነስቷታል፡፡ በዚህም የተነሳ የዶ/ር አብይ ስም በመቀሌዉ ሰልፍ ላይ ጎልቶ እንዲሰማና በሌሎች ሰልፍ ላይ የተትረፈረፈዉ የዶ/ር አብይ ምስልም በአደባባይ እንዲታይ አልተደረገም፡፡የሆነዉ ሁሉ ይሁን እንጅ የኢትዮ ኤርትራን ሰላም ድፍረት በተሞላበት ያላሰለሰ ጥረት በፍጥነት እዉን እንዲሆን ያደረጉት ዶ/ር አብይ የመሆናቸዉን እዉነታ ከቶዉን ሊቀይረዉ አይችልም፡፡

አልሸሹም ዘወር አሉ!!

የዚህ ሠልፍ ዓላማ የኢትዮ-ኤርትራን እርቀ ሰላም መደገፍ ነዉ ቢባልም በዚያም አለ በዚህ የእርቀ ሰላሙ ፊትአዉራሪ የሆኑት ዶር አብይ በመቀሌ ሰልፍ ላይ የኢትዮ ኤርትራ ሰላም ሲደገፍና ሲወደስ እርሳቸዉም አብረዉ ሲደገፉና ሲወደሱ ዉለዋል፡፡የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ እስከተነሳ ድረስ ለማተቡ ያደረ ማህበረሰብ ማወደስ ያለበት እሳቱን ለኩሶ መቶ ሺዎችን የማገደዉን ሳይሆን ለ20 ዓመታት ሲያቃጥለንና ሲለበልበን የነበረዉን ሰደድ እሳት በፍቅር ዉሃ ያጠፋዉን ጀግና ነዉ፡፡ ይህ ጀግና ደግሞ ከአብይ ዉጭ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡ያለበለዚያ ግን ፍርዱ በርባንን ፈቶ እየሱስን እንደመስቀል ያለ ይሆናል፡፡

የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ!!

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ብሄር ዶር ደብረጽዮን በሃምሌ ሃያ አንዱ የመቀሌ ህዝባዊ ሠልፍ ላይ የተናገሯት አንዷ ነገር አንጀቴን አራሰችዉ፡፡

“አንዱ የበላይ አንዱ የበታች፣ አንዱ ለማኝ ሌላኛዉ ተለማኝ የሚሆንበት ጊዜ አብቅቷል”

ብራቮ ዶ/ር!!ብራቮ!! ያለዛሬም ዶክተርነትዎን አላስመሰከሩ!!!

ኢትዮጵያዉያን ላለፉት 27 ዓመታት ሲጠይቁ የነበረዉ እኮ ይሄንኑ ነዉ!!የህወሃትና የጄሌዎቹ የበላይነትና ተለማኝነት ያብቃ ሲል ነዉ ስንቱ ለእስራትና ለግርፋት ለስደትና ለሞት የተዳረገዉ!! መቼስ የህወሃቱ ዶ/ር ይህቺን እዉነት በዚች 3 ወር ዉሰጥ አይዘነጓትም ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገሩ የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ ቢሆንም፣ በዶ/ር አቢይ ዘመን ይሄ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች፣ አንዱ ለማኝ ሌላኛዉ ተለማኝ የሚሆንበት የህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ጊዜ ማብቃቱን በድፍረት በመመስከርዎ ሳንወድ በግዳችን ልናደንቅዎና ልናመሰግንዎ እንገደዳለን!!ይልመድብዎ ዶ/ር፡፡

ያደቆነ ሠይጣን….!!

ሌላኛዉ የደብረጽዮን ዛቻ አይሉት ንግግር ያሳወቀን ቁም ነገር ህወሃት ገና ከማለዳዉ አንግቦት የመጣዉ ኢትዮጵያን የመበታተን አላማ ዛሬ ወደ መሬት ለማዉረድ ዳር ዳር ማለቱን ነዉ፡፡ ወይ ተከባብረን መኖር አልያም መበታተን ሲል ያስቀመጣቸዉ ሁለት አማራጮች ያደቆነዉ ሰይጣን ማቄስ መጀመሩን አመላካች ነዉ፡፡ደብረጽዮን የአንድ ክልል ርዕሰ ብሄር ሆኖ በድፍረት መቶ ሚሊዮን ህዝብን ወክለዉ ስለመበታተን ሲያወራ ትንሽ እንኳ ደንቀፍ አላደረገዉም፡፡ዶ/ር ደብረጽዮን አይደለም ሌላዉን ህዝብ ቀርቶ እመራዋለሁ የሚለዉን የትግራይን ህዝብ እንኳ ወክሎ ስለመበተን የማዉራት መብት የለዉም፡፡ዶ/ር ደብረጽዮን ምናልባት እንደ አንድ ግለሰብ ስለትግራይ መገንጠል ሊቀባጥር ይችል ይሆናል፡፡በዚህ ወቅት አንድ ትንሽ ክልልን እየመሩ ስለአንድ ትልቅ ሃገር መበታተን ማዉራት ግን በቁም መቃዠትና ህዝብና መንግስትን መዳፈር ነዉ፡፡ህወሃት አንድ ቀን ሊበታተን ይችላል፡፡ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ታፍራና ተከብራ እንደምትኖር ከወዲሁ ስንነግርዎ በምኞትዎ ያለመሳካት ከልባችን እያዘን ነዉ፡፡

የአባዬን ወደምዬ!!

ዶ/ር ደብረጽዮን ስለመከባበር ያነሱት ሃሳብ የምር አስቆኛል፡፡ ዶ/ሩ መከባበር ሲሉ ምን ማለታቸዉ ይሆን? ለመሆኑ ማን ማንን ነወ ያላከበረዉና ሲንቅ የኖረዉ? መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃትን ላለፉት 27 ዓመታት አክብሮ እንደኖረ ያደባባይ ሚስጢር ነዉ፡፡ እርግጥ ነዉ አክብሮታችን ከዉዴታና ከፍቅር የመነጬ እንዳልሆነ እነደብረጽዮንም ቢሆኑ አያጡትም!!ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ምን ሲያደርግ እንደነበር ለርስዎ መንገር ለቀባሪዉ ማርዳት ስለሆነ በዝምታ አልፈነዋል፡፡

Filed in: Amharic