ነቢዩ ሲራክ.
* የትንሳኤው ጅምር ማሳያው ስኬት
* የትንሳኤው አደናቃፊዎች አጓጉል ህልም
* ዶር አብይ በሀገረ አሜሪካ በፍቅር መንገድ
* ሳውዲ ላይ እኔ ፣ አሜሪካ እነ ታማኝ ስንከለከል
* እንዳንጋጭ እንዳንለያይ የእኔ ምክር
የትንሳኤው ጅምር ማሳያው ስኬት …
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በመንታ መንገድ ቆማለች ! በሶስት ወራት እድሜ ኢትዮጵያውያን ያላየነው ይሆናል ተብሎ የተገመተ አይደለም ። ሁሉንም እንደ መልኩ በፍቅር የሚመከከቱ መሪ ዶር አብይን በአጭር ጊዜ አስደናቂ እርምጃ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር እርቅ በመፍጠር ፣ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ በማድረግ ፣ ትውልድ የጨረሰው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በሰላምና በፍቅር እንዲዘጋ ፣ በሙስሊማንና በክርስትያን የሐይማኖት መሪዎች መካከል የነበረው ጣልቃ ገብነት አቁሞ እርቅ እንዲዎርድ ማድረጋቸው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጅማሮ ምልክቶች ናቸው ባይ ነኝ !
የትንሳኤው አደናቃፊዎች አጓጉል ህልም …
ከዚህ የአጭር ወራት አስገራሚ ስኬት ኢትዮጵያ ነጋላት ፣ ኢትዮጵያውያን መሪ አገኘን ስንል የስውር ሴራ ቀጠሮ በየአቅጣጫው እየገመደ ይገኛል። በቀናው የሰላም ፣ የፍቅርና የይቅርታ መርህ በእንደመር የተገኘው ህብረትና ለውጥ እንዳይሳካ ብዙ ፈታኝ ስራ እየተሰራ መመልከት ይዘናል ። ከብዙው በጥቂቱ ልጠቀስ ። በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም የድጋፍ ሰልፍ መሪያችን ለመግደልና ህዝብን ለማጫረስ ቦንብ መጣል ፣ በየክልሎች በሚሰራ ርኩስ ሴራ ሰውን በዘር ፣ በሐይማኖትና በጎሳው ማናቆር ፣ ማጋጨት ፣ ከአረብ ሀገራትና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተደረገውን መልካም ለሀገር የሚበጅ የሁለትዮሽ ግንኙበት ማንቋሸሽ ፣ ትናንት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓም የህዳሴውን ግድብ ጀግና ኢንጂነር ስመኘው በቀለን መግደል ከሚጠቀሱት ኢትዮጵያን የማጥፋትና የማጨራረስ ተንኮል ሴራ ሆኖ እያየን ነው 🙁
ይህ ደስታችን ሳናጣጥም የሚከወን ስውር ሴራ የሀገራችን የኢትዮጵያ ትንሳኤ በመንታ መንገድ ቆማ እንድናያት አድርጎናል! ጥፋት የሚያሴሩልን ወደ መልካም የምንጓዝበተረን መንገድ ለማደናቀፍ ክፉዎች ያደረጉት ሴራ ከሐጢያቱ ሁሉ የከፋ ሐጢያት ነው ባይ ነኝ ! ህብረታችንና ለውጣችን ማየት የማይፈልጉት ወገኖች ሴራ ሀገር የማወክ የማፈራረስ ህልም ዋጋው ከባድ ቢሆንም ኢትዮጵያውያ አትጠፋም !
በአሜሪካ ኢንባሲው የዶር አብይ ክስተት ያስደመመኝ !
በመሪሩ ሀዘን መካከል የፍቅር ሰላምና ይቅርታ መንገድ ተከታዩ ዶር አብይ በአሜሪካ ኢንባሲ ንግግራቸው ” አፍሪካ መሪ አጥታ ለማኝ ሆናለች …” ብለዋል ። ንጉሱ ዶር አብይ ” ፍቅር ያሽንፋል ፣ ፍቅር ያሸንፋል! ” ያሉት ዶር አብይ አህመድ ” የፈረሰ ቤታችን እንስራው! ” በሚል መሳጭ ንግግር አድርገዋል ።
ድንቁ የፍቅር መሪ ንግግራቸውን እንደጨረሱ እንግዶችን በመቀመጫቸው እንዳነሱ በመጠየቅ ” እየዞርኩ ሰላም እላለሁ ” አሉና አስደመሙን ። ቃል አክባሪው ዶር አብይ በቃላቸው መሰረት በየጠረጴዛው እየዞሩ ለተጋባዦች ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
ሳውዲ ላይ እኔ ፣ አሜሪካ እነ ታማኝ ስንከለከል …
ዶር አብይ ንግግራቸውን እንደጨረሱ ይህኔ ትዝ ያለኝን አንድ የቅርብ ወራት ትዘታ ልግለጠው ። ዶር አብይ ሳውዲ መጥተው በነበረ ወቅት እኔ እንዳላገኛቸው ተደርጎ ነበር። ዳሩ ግን ስለሚሆነው ሁሉ መረጃ ያላቸው ብልሁ ዶር አብይ አምባሳደር ውብሸት ደምሴን ጠርተው ነቢዩ ሲራክን አገናኝ በማለት በአንባሳደሩ ስልክ አስደውለው አገኝተውኛል ። በስልክ በነበረን ቆይታ ፍጹም ትህትና በተሞላበት መንገድ ስለብላቴናው መሐመድ መረጃ እንዳላቸው በመግለጽ እኔም ሆንኩ የብላቴናው አጋሮች ስላደረግነው የፍትህ ጥያቄ ማሰማት ድጋፍ ምስጋና አቅርበውልን ነበር !
በምድረ አሜሪካም ኢንባሲው እነ ታማኝ ታግደው ነበር ። የዲሞክራሲ ታጋዮች መገለል ያንገበገባቸው አንድ ወንድም ከተጋባዥ ታዳሚዎች መካከል ዶር አብይ ንግግራቸውን እንደጨረሱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ታማኝ ለምን አይገኝም?” በሚል የታማኝን ክልከላ በመቃዎም የዜጋ ጥያቄያቸውን አሰምተዋል ። ዶር አብይ አህመድ መለሱ “ታማኝ፣ ሲሳይ አጌና፣ አበበ በለው ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ … ሁሉም ይኖራሉ” ሲሉ መለሱ ! ለመረጃ ሰው ለዶር አብይ አህመድ እውነት አትጠፋበትም ፣ ፈልጎ አግኝቷታል ! በነገራችን ላይ ሳውደ ጅዳም በተደረገው ድጋፍ የሆነው ይህው ነው …
ኢትዮጵያና ህዝቧም በእኩዮች ሴራ እንዳንጋጭ !
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ትንሳኤ በመንታ መንገድ ላይ ናቸውና ለኢትዮጵያና ህዝቧ የተሻለውን የለውጥ ጅማሮ ለማስቀጠልና በእኩዮች ሴራ እንዳንጋጭና እንዳንለያይ የበኩሌን ልበል ። ከምንም በላይ የክፉዎችን ሴራ ለማክሸፍ ተረጋግቶ የሂደቱን አደናቃፊዎች የመከላከል ፣ ሀገር ህዝብ የመከላከል ኃላፊነት አለብንና የተጀመረው የለውጥ ጅምር በሴረኞች እንዳይደናቀፍ አላስፈላጊ ሰላማዊ ሰልፍን እናስወግድ ። ዘርን ተኮር ጸብ አጫሪ መረጃ አናሰራጭ ። የመንግስትም ሆነ የግለሰብን ንብረት አናውድም ፣ አናቃጥል ። ከመቸውም በላይ ዛሬ ክፉ ቀንን ከሚመኙልን መረብ ላለመውደቅ በጉዳት ስሜት የተቆጣውን ወገናችን ተረጋግረን ህዝባችን እናረጋጋ ! በቃ አማራጩ መንገድ ይህ ነው !
ኢትዮጵያ ወደ ትንሳኤው በምታደርገው ግስጋሴ ላይ በክፉዎች ተጠልፈው ህይዎታቸውን ላጡት ለኢንጂነር ስመኘው በቀለና እና የቀሩት ወገኖችን ነፍስ ይማር 🙁 ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ: ( አሁንም በሴራው የተፈናቀሉ ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና የተለያየ መስዋዕትነትን ለከፈሉ ወገኖች ክብር እሰጣለሁ !
ፈጣሪ ሀገራችንና ህዝቧን ይጠብቅ !
ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓም