>

ህወሀቶቹ መቀሌ ተሰብስበው የጥፋት ድግስ እያሰናዱ ነው ነገም ሌላ ግድያ ሌላ ሽብር...  (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ህወሀቶቹ መቀሌ ተሰብስበው የጥፋት ድግስ እያሰናዱ ነው ነገም ሌላ ግድያ ሌላ ሽብር… 
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን
የምርመራው ውጤት እስኪታወቅ ከመላ ምት ያለፈ አስተያየት መስጠት የሚቻል አይደለም። እንደሚባለውም ወደ ግድቡ ሲያመሩ የነበሩ መሀንዲሶች በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ህይወታቸው አልፏል። ስለዚህኛው
መረጃ ከመንግስት የሚዲያ ተቋማት የሰማሁት ነገር የለም። ትላንት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ድንገት ህይወታቸው ያለፈው የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣንም ሁኔታ አሳዛኝ ነበር።
የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊና የክልሉ ሁለተኛ ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው እየተራመዱ ወደ ሆስፒታል ገብተው በሰዓት ልዩነት ህይወታቸው አልፏል። አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለህወሀት የሚጎረብጡ፡ ለለውጥ ሃይሉ
የጀርባ አጥንት የሆኑ፡ ብአዴንን ከህወሀት ቀሚስ ለማላቀቅ ግንባር ቀደም ሆነው የተሰለፉ ቆፍጠን፡ ጠንከር ያሉ ሰው ነበሩ። ለውጡን መርተው ሂደቱን ሳያጋምሱ ሞት ቀደማቸው።
ሌሊት በአጋጣሚ ስነቃ ደግሞ የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ሞት ሰማሁ።ምን እየሆነ ነው? የተለያዩ መረጃዎች ይፈሳሉ። ከጆሮአቸው ደም ይፈስ እንደነበር አይተናል የሚሉ ሰዎች የጻፉትን አነበብኩ። ሽጉጥ ከጎናቸው
ተቀምጧል የሚሉም አሉ። ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ከመስክ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውም ይነገራል። የሞት ቀጠሮ መስቀል አደባባይ ላይ ጠበቃቸው።
በእርግጥም ኢንጅነሩን በጠዋቱ የገጠማቸው ዱብ እዳ ምን ይሆን?
ሰሞኑን የአባይ ግድብን በተመለከተ የጦፈ ወሬ መድረኩን ተቆጣጥሮት ሰንብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ስለግድቡ የተናገሩት ተጠቅሶ ውይይቱ ደምቆ ነበር። ኢንጅነር
ስመኘውም ሰሞኑን ስማቸው ማህበራዊ መድረኮች ላይ ሲመላለስ ቆይቷል። ግጥምጥሞሹ ያጠራጥራል። አንድ ግለሰብ በፌስ ቡኩ በተደጋጋሚ ስለኢንጅነር ስመኘው ደህንነት እየጠቀሰ ሲያሰራጭ የነበረው መልዕክት
ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። የግለሰቡ የፌስ ቡክ መልዕክት እውነተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት ቢከብድም ሁኔታውን ከተራ ሞት በዘለለ መመልከት እንደሚገባ የሚጠቁም ነው።
በፎቶግራፍ በመኪና ውስጥ የሚታየው የኢንጅነር ስመኘው አስክሬን አንዳች ነገር እንዳለ የሚያመለክት ነው። በጆሮ ግንዳቸው ፈሶ ከፊታቸው ላይ የሚታየው ደም ግድያ ተፈጽሞባቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነው።
በመስቀል አደባባይ ስፖርት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች የተኩስ ድምጽ እንደነበር ተናግረዋል።
የአባይ ግድብ ግዙፍ ሙስና የተሸከመ እንደሆነ ይታወቃል። ሜቴክና ኢፈርት እጃቸው የተነከረበት የግድቡ ፕሮጀክት በውስብስብ የሙስና ገመዶች የተተበተበ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ። ከግድቡ ጋር በተያያዘ
እነጀነራል ክንፈ ዳኘው ከበርካታ ቢሊዮን ብሮችን ጋር ስማቸው ይነሳል። ኢፈርት ከብረት፡ ከሲሚንቶና ትራንስፖርት አቅርቦት አንስቶ የግድቡን አብዛኛውን ስራ በመውሰድ በግልጽ ዘረፋ የተሰማራ ለመሆኑ መረጃዎች በየጊዜው ይወጣሉ። እንግዲህ በዚህ ሁሉ ወንጀሎች ውስጥ የኢንጂነር ስመኘው ስም መነሳቱ አይቀርም። የዘረፋው አካል ላይሆኑ ይችላሉ። እርግጠኛ ባልሆንም። ነገር ግን መረጃው ሊኖራቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። መረጃው ያለው ሰው ደግሞ ለህወሀት አደገኛ ማስረጃ መሆኑ አይቀርም።
የመብራት ሃይል ዋና ስራ አስኪያጇ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ተነግሯል። የስራ አስኪያጇ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ንግግር በኋላ እንደሚለቁ መሰማቱ ምን ያመለክታል? የምርመራው ውጤት ወሳኝ ቢሆንም የተለያዩ ዶቶችን በማገናኘት የኢንጅነር ስመኝም አሳዛኝ ትራጂዴ የተመለከተ ግምት መስጠት ይቻላል።
አንዳንድ የህወሀት ደጋፊዎች ግብጽ እጇ እንዳለበት መግለጽ ጀምረዋል። ውሃ የሚያነሳ ድምዳሜ ሆኖ አላገኘሁትም። ግብጽ ይህን ማድረግ ፍላጎቷ ቢሆን ቀደም ብሎ ጀምሮ ላለማድረግ የከለከላት ነገር ምን ነበር? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ካለ መስማት ጥሩ ነው። ኢንጅነሩን በመግደል ግብጽ የአባይን ግድብ ልታቆመው ትችላለች ብሎ ማሰብ መብት ነው። ግን ጅላጅል ሀሳብ ነው።
የኢንጅነር ስመኘው ሞት(ግድያ) የሰሞኑን ፖለቲካ ያሞቀዋል ተብሎ ይጠበቃል። የተቀነባበረ ግድያ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ፖለቲካውን የበለጠ አስጨናቂና አስፈሪ ያደርገዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ብርቱ ፈተና
መሆኑ የማይቀር ይሆናል። ምርመራው ደረጃውን በጠበቀ ገለልተኛ ተቋም ካልተካሄደ በቀር እውነቱ ላይ ለመድረስ በቀላሉ የሚቻል እንዳልሆነም መታወቅ አለበት። FBI የገባበት የሰኔ 16 የቦምብ ጥቃት እስከአሁን ውጤቱ ያልታወቀበት ምክንያቱ ምን ይሆን? እንግዲህ የኢንጂነሩን ሞት (ግድያ) ፖለቲካዊ ምክንያት ካለው በአጭር ጊዜ ውጤቱ ይታወቃል የሚለውም እጅግ አጠራጣሪ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሽንግተን ዲሲ ገብተዋል። በዚህን ወቅት ከሀገር ባይወጡ የሚሉ አስተያየቶች በርክተዋል። ይህ ክስተት የአሜሪካውን ጉዞ አቋርጠው ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ባያደርጋቸውም የነገሮች መደራረብና
በሀገር ቤት ያለው ስጋት የውጪውን ጉዞአቸውን እንዲቀንሱ ማድረጉ የማይቀር ነው። ህወሀቶች መቀሌ ተሰብሰበው ስለሀገር ሰላም መምጣት እየመከሩ እንዳልሆነ ይታወቃል። የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚችሉትን ጥፋት ሁሉ ለመፈጸም ቃል ኪዳን ገብተው እየተማማሉ እንደሆነ አይጠፋንም። መርዝ እየቀመሙ ነው። የጥፋት ድግስ እያሰናዱ ነው። ጠ/ሚር አብይን መደገፍ ኢትዮጵያን ማዳን ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።
የኢንጅነር ስመኘው ሞት(ግድያ) ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው በአጠቃላይም ላለፉት ስምንት ዓመታት ከግድቡ ጋር ከነበራቸው ትጋት አንጻር ለሚያደንቃቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አስደንጋጭ መርዶ ነው። ለሁሉም
መጽናናትን እመኛለሁ።
Filed in: Amharic