>

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንኮራለን!!! (ኢብራሐም ሙሉሸዋ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንኮራለን!!!
ኢብራሐም ሙሉሸዋ
* ቆይ አሁን «አንተ ሙስሊም ሆነህ ስለ ኦርቶዶክስ ምን ገደደህ?» ብባል ምን እላለሁ? …. መልስ አለኝ!!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያነት ማሳያ ትልቅ የአገር ሀብት ናት። ቤተ ክርስትያኒቱ ከመንግስት ጋር ከነበራት ግንኙነት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮች መኖራቸው አሌ ባይባልም በሌላው ጎን ግን ቤተ ክርስትያኒቱ ለአገራችን ፓለቲካ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያደረገችው አስተዋፅኦ በምንም እና በማንም ሊተካ የማይችል ነው። ዛሬ የምንጠቀመው የአማርኛ ፊደል እና የዘመን አቆጣጠራችን ከቤተ ክርስትያን ያገኘናቸው ናቸው። እኔ ባለሁበት ቱርክ አገር ስለ ኢትዮጵያ ሳወራ ኮራ ብዬ ደረቴን ከምነፋባቸው ነገሮች አንዱ የራሳችን የዘመን አቆጣጠር እና ፊደል ያለን መሆኑ ነው።
ይህን በኢትዮጵያዊነት የምኮራበትን ስጦታ ያስረከበችኝ ይህችው ቤተ ክርስትያን በመሆኗ የእሷ መበላሸት የእኔም የሙስሊሙ ዜጋ አገር መበላሸት ነው። ለዚህ ነው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ «ኦርቶዶክስ የእናንተ (የኦርቶዶክሶች) ብቻ አይደለም። የሁላችንም ሀብት ነው። ታሪካችን አለበት። ትውፊት አለበት። ቋንቋ አለበት። ማንነታችን አለበት። ሲበላሽ ሌላውም ሃይማኖት ይገደዋል» ያሉት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ከኢትዮጵያም ያለፈ አፍሪካዊ ሚና ያላት ቤተ እምነት ናት። ከሳሀራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል ክርስትና ከምዕራቡ ዓለም የመጣ አለመሆኑን እና የአፍሪካ አካል መሆኑን ለማሳየት የሚጥር አንድ አፍሪካነቱንም ክርስትናውንም እኩል የሚወድ ሰው ብቸኛው ምሳሌ ይህችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ናት። ለፈረንጆች «አንተ ያመጣኸው ሳይሆን የእኔው የራሴ ክርስትና አለኝ» ብሎ ለፓርቱጋል ተስፋፊዎች አልንበረከክም ያለ ንጉስ እዚሁ እኛው ጋር ነው የነበረው።
«አንተ ሙስሊሙ ስለ ኦርቶዶክስ ምን አገባህ?» ላለኝ ደግሞ መልሴ «ከእኔ ሀይማኖት ጋር በቀጥታና በአዎንታዊ መንገድ የተገናኘች ብቸኛ የሀይማኖት ተቋም ይህችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ናት» የሚል ነው። በቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች የተወደሱትን እጅግ ፍትሐዊ ንጉስ ነጃሺን እና ቀሳውስቱን ያበረከተችው ቤተ ክርስትያኒቱ ናት።
ይህ ብቻም አይደለም! አውሮፓውያን በመስቀል ጦርነት ዘመን «ሙስሊሙን ተባብረን እናውድም» ጥሪ ሲያቀርቡላት ተቃውማ ከዓለም አቀፉ ዘመቻ የተቆጠበችው፣ ለዚህ ውለታዋም ከገናናው ሙስሊም ሱልጣን ሰላሁዲን አል አዩቢ እየሩሳሌም ውስጥ ገዳም የተሰጣት ታላቅ ቤተ ክርስትያን ይህችው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ናት።
ይህች ቤተ ክርስትያን ከደርግ ዘመን ጀምሮ በመጣው ለውጥ አማካኝነት የመንግስት እና የቤተ ክርስትያን ግንኙነት በመሰረታዊ ሁኔታ በመለወጡ የመጣባት ጣጣ እና የፓለቲከኞች ጣልቃ ገብነት በልጆቿ መካከል ክፍፍልና ጸብ ፈጥሮባት አንድነቷን አጥታ ቆይታለች። ዛሬ ግን በኢትዮጵያችን እየነፈሰ ያለው መልካም አየር ለቤተ ክርስትያኒቷም እየደረሰ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያነቴ ከልብ የመነጨ ደስታ ተሰምቶኛል! በዚህ አጋጣሚ ለመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች «እንኳን ደስ አላችሁ» እላለሁ!
Filed in: Amharic