>

ስለ አቶ ለማ ከስልጣናቸው መነሳት የተነዛው ወሬ እና አንድምታው!!! (ኢብሳ አዱኛ እንደጻፈዉ)

ስለ አቶ ለማ ከስልጣናቸው መነሳት የተነዛው ወሬ እና አንድምታው!!!
(ኢብሳ አዱኛ እንደጻፈዉ)
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከዩንቨርስቲ ምሁራን ጋር በመከሩበት መድረክ ላይ የክልል ፕሬዝዳንቶች በቅርቡ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ መናገራቸውን ተከትሎ በ #ስዩም_ተሾመ አራጋቢነት አቶ ለማ መገርሳንም እንደሚያካትት መዘገቡ በፌቡ መነጋገሪያ እየሆነ ይገኛል። የሀሳቡን ተፈፃሚነት ወደ ጎን ትተን አንድምታው ላይ ብናተኩር የበለጠ ትርጉም ሰጪ ሆኖ አናገኘዋለን።
ሀሳቡ የአብይም ሆነ (በግሌ የሱ ሀሳብ ነው ብዬ ለመቀበል ይከብደኛል) የየትኛውም አካል ቢሆን ታርጌት የተደረገው አቶ ለማ መገርሳ ሳይሆኑ ዶር አብይ፣ ከዚያም ባሻገር የኦሮሞ ህዝብ፣ ባስ ካለም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። ምክንያቱም የአብይ ጥንካሬ በለማ ውስጥ ጎልቶ የወጣ ሲሆን የለማ ጥንካሬ በአብይ ላይ የተገመደ ፈርጥ ነው። ሁለቱም ሲቧደኑ እና ከሌሎች ጋር በህብር ሲደመሩ የኢትዮጵያ ተስፋ ሆኑ/ናቸው።ይህ ማለት አንዳቸው ያለ አንዳቸው ምንም እንዳልሆኑ (በዶሩ አገላለፅ አብይ ያለ ለማ ‘ግንጥል ጌጥ’) ከመሆን የዘለለ ሚና አይኖረውም እንደ ማለት ነው። እንግዲህ ለመምታት የታቀደው አቶ ለማን ሳይሆን አልትሜት ጎሉ የኢትዮጵያን ተስፋ ማጨለም ነው። እልቂት ለመፍጠር እና በመሃል አትራፊ ሆኖ ለመውጣት የሚያስቡ ነጋዴዎች አሉ። መገመት ቀላል ነው ፤ ግን አይጠቅምም። ነጋዴዎቹ ግን ከአንድ በላይ እንደሚሆኑ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። መንጋውን በመበተን ነጠላውን አሳደው ለመብላት ያሰፈሰፉ ጅቦች!!
እስኪ ማሳያ እንይ። ሀሳቡ በፈለቀ ማግስት የእርጉዝ ሴት መገደል ትልቅ አጀንዳ ሆነ (እንደ እውነቱ ከሆነ ጉዳዩ ከአጀንዳነትም ያለፈ ቅስም ሰባሪ ግፍ ነው)። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጣቶች ወደ ለማ ሲቀሰሩ ዋሉ። ፌቡከሮች ለማን ከስልጣን ሲያወርዱ እና ስያነግሱ ዋሉ። ይህ ለምን ሆነ ብሎ የሚጠይቅ ልባም ከተገኘ የጠላት አጀንዳ ከበስተጀርባው መኖሩን ጥርት አድርጎ ማየት ይቻለዋል። የፌቡ አሰላለፎችን ከወትሮው ለየት ብሎ መዋልን አስተውሎ ለተመለከተ ትልቅ ድግስ እንዳለ መገመት ይችላል። የሰሞኑ የጎባ እና አላባራ ያለው የምዕራቡ ትንቅንቅ ኢትዮጵያን ለማውደም ቀድሞ ኦሮሚያን ማፈራረስ የግድ እንደሆነ ደግሞ ግልፅ የሆነ ተልዕኮውን የሚያሳይ ነው። የኦሮሚያ ዓይን እና ልብ ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። የኢትዮጵያ ተስፋም እንዲሁ ዶር አብይ ናቸው። ሁሉንም በተራ ለመምታት ያለመ አካል በደንብ እየተወነ ነው። ማን ያውቃል፤ የነገ ሟች ባለ ሳምንት የዛሬውን መርዝ ጠንስሶትም ሊሆን ይችላል።
እዚህ ጋር አንድ ነገር ማለት ይቻላል። ነገሮች በተቃራኒው በመሄድ ጉዞአቸውን ሳያጋምሱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በአፋጣኝ ማስቆም ይችላሉ። የሚያዋጣቸው እርሱ ነውና። ኳሱ አሁን በቀዳሚነት ወደ ሶስት ግለሰቦች ተወርውሯል። ዳውድ-ለማ-አብይ። በፍቅር ተጋምደው ታሪክ ይሰሩ ይሆን ወይስ የታሪክ አተላ ሆነው አስቀያሚውን የአላፊ ጊዜ ውድቀት ደግመው ዳግም ተወቃሽ ይሆኑ ይሆን?! ልብ እንዲሰጣቸው ምኞታችን ብቻ ሳይሆን ፅኑ ፀሎታችንም ነው!!
Filed in: Amharic