>

የምህረት አዋጁን በደስታና በቀና ልቦና ተቀብየዋለሁ!!! (መስፍን ነጋሽ)

የምህረት አዋጁን በደስታና በቀና ልቦና ተቀብየዋለሁ!!!
መስፍን ነጋሽ
አዋጁ የተቀረጸበትን ወቅትና መንፈስ ስለምረዳ፣ አዋጁንም ሆነ በዚያ በኩል ለማሳከት የታቀደውን በጎ ዓላማ ስለምደግፍ መሠረታዊ ልዩነት የለኝም። በዚያ ላይ በግሌም ተጠቃሚ የምሆንበት ስለሆነ አመሰግን ይሆናል እንጂ አልቃወምም።
እንዲያም ሆኖ፣ አዋጁም ሆነ የሪፖርት ማድረጊያ ቅጹ “ተጠዋሚዎች ይሆናሉ” ያላቸውን ሰዎች ሁሉ በተዘረዘሩት ወንጀሎች እንደተሳተፉና ጥፋተኛ እንደሆኑ ደምድሞ/አምኖ እንደሚነሣ እታዘባለሁ። ነገሩን ለፓርላማው ያስረዱት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢም ምሕረቱ “በአዋጁ በተዘረዘሩት ወንጀሎች ተሳትፈው ለነበሩ …” የመጣ መሆኑን ተናግረዋል። የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስታወቂያም “…በተለያዩ የወንጀል ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ለድርጊታቸው የወንጀል ተጠያቂነታቸውን በጠቅላላው በመሰረዝ…” ይላል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አዋጁ የሚመለከታቸው ወንጀሎቹን “በመፈጸም ወይም በመሞከር የተሳተፉ [በመፈጸምና በመሞከር]” በማለት አስረድተዋል። ይህ አረዳድ ግማሽ እውነት ነው፤ ምንም የሕግ ጥሰት ሳይፈጽሙ በፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ በፈጠራ የተከሰሱ ሰዎች ስላሉ። በሕግ እና በፍርድ ቤት ስም የተሠራውን መንግሥታዊ ውንብድናና እብሪተኛነት የሚያለባብስ፣ ለታሪክም የተሳሳተ አሻራ የሚተው አቀራረብ ነው። በአሻንጉሊቶቹ ፍርድ ቤቶች ተላልፎ የነበረውን የጥፋተኛነት ብይን በፍትሐዊ ሒደት እንደተሰጠ ውሳኔ ቆጥሮ መንደርደር ስሕተት ነው። ፍጹም ስሕተት ነው።
በእርግጥ፣ በግልጽ የአገሪቱን ሕግ ኢፍትሐዊነት በመጥቀስ ይሁነኝ ብለው ሕግ በመጣስ የፖለቲካ ትግል ማድረግን የመረጡ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ፍርድ ቤት ባይወስንባቸውም ጭምር ሕጉን መጣስ የትግላቸው አንድ ስልት መሆኑን በአደባባይ የሚገልጹ ናቸው። ለምሳሌ መሣሪያ ማንሳት ከዚህ ይመደባል። በተመሳሳይ፣ ፈቅደውም ይሁን በአስገዳጅ ሁኔታዎች ሕግ የጣሱ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ሰዎች “ሕግ መጣሳችሁ እንዳልተደረገ ተቆጥሮላችኋል፣ አሁን ወደ ሕግ ግቡ” ቢባል ያስኬዳል። ምሕረት ነው።
በተቃራኒው፣ እኔን የመሰሉ ሰዎች ግን የእብሪተኞች መቀለጃ በሆነው፣ የተጻፈበትን ወረቅት ያህል እንኳን ዋጋ እንዳይኖረው በተደረገው ሕግም ቢሆን ሕግ ያልጣስን ነን። ሕሊናቸው በፓርቲና በጎሳ ጥቅም በታወረ ባልሥልጣናት፣ የደኅንነት ሐላፊዎች፣ “ዐቃብያነ” ሕጎችና “ዳኞች” የቀረበብን የፈጠራ ክስም ሆነ የተላለፈብን ብይን፣ የሰካራም መዘላበድን ያህል እንኳን ዋጋና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ አይደለም።
እንናገር ከተባለ፣ በሕግ እና በፍርድ ቤት መሣሪያነት ወንጀል የተፈጸመብን ንጹሐን ነን። ተጎጂዎች ነን። ምሕረት የምንጠይቅም የሚሰጠንም ወንጀለኞች አልነበርንም፤ አይደለንም። ፈጽሞ! ይኼ እምነቴ የምሕረት አዋጁን በበጎ ሕሊና ላመጡትም ይሁን፣ ዐይናቸው በቋሚነት ለሚቀላባቸው ሕመምተኞች ሁሉ እኩል ግልጽ መሆን አለበት።
በበኩሌ፣ አሁንም ቢሆን ቢያንስ እንድንሞላ በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ከመግቢያው ጀምሮ ይህንን ችግር የሚፈታ አገላለጽ እንዲተካ እመኛለሁ። ለምሳሌ፣ “ሕግ በመጣሳቸው ወይም ጥሰዋል ተብለው” “ወንጀል ፈጽመው ወይም ፈጽመዋል ተብለው” የመሳሰሉ ለትርጉም ክፍት የሆኑና ሁሉንም ሊያካትቱ የሚችሉ አገላለጾች ጥቅም ላይ ቢውሉ ይሻላል።
አንደኛው የቅጹ ጥያቄ፣ “ወንጀሉ የተፈጸመው በስንት ዓመት ምሕረት ነው?” ይላል። ወንጀል አልፈጸምኩም የምለው ሰውዬ ይኼንን ጥያቄ የምመልሰው ምን ብዬ ነው? ወንጀሉ ተፈጽሟል ያሉትን ሕሊና ቢሶች (ከሳሾችና ዳኞች) ሄዶ መጠየቅ ነው እንጂ፣ እኔ መልስ የለኝም። ከዚህ ይልቅ፣ ክስ የቀረብብዎ ወይም የተበየነብዎ መቼ ነው፣ በክሱ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው መቼ ነው፣ የተከሰሱበትን ፋይል ቁጥር የሚያውቁት ከሆነ ይጥቀሱ ወዘት ብሎ መጠየቅ አይሻልም ነበር?
“ምህረት የተደረገልዎ በየትኛው የወንጀል ድርጊት ነው” (ቃል በቃል አይደለም) የሚል ጥያቄም አለ። መንፈሱን እረዳለሁ። አስፈላጊ ጥያቄም ነው፤ አጠያየቁ ግን ችግር አለበት። አሁንም፣ ከዚህ ይልቅ “አሁን ምሕረት የተደረገልዎ የትኛውን ሕግ በመጣስዎ ወይም ጥሰዋል ተብለው በመጠርጠርዎ፣ በመከሰስዎ ወይም በመቀጣትዎ ነው” ወይም “በጥሰት የተጠረጠሩበት ወይም የተከሰሱበት ሕግ የትኛው ነው?” ብሎ መጠየቅ ይሻል ነበር። ዝርዝሩ ብዙ ነው፤ ለባለሞያዎቹ መተውም አግባብ ነው።
ከጅምሩ የምሕረት አዋጁን መንፈስ በበጎነቱ ስለተቀበሉኩት፣ እነዚህ በአዋጁም ሆነ በአሁኑ ቅጽ የተንጸባረቁት ስሕተቶች በሙሉ ሆን ብለው የገቡ አይደሉም ብባል ለማመመን አልቸገርም። ጥድፊያውም ይገባኛል። ሆኖም፣ ቢያንስ አመልካቾች በፊርማችን በምናስረከበው ቅጽ ላይ ስሕተቱ መታረም ይኖርበታል፤ ይቻላልም። ይህን ማድረግ ማንንም አይጎዳም። ለእኔ ብጤዎቹ ደግሞ ያለብዙ የሕሊና ትግል ሪፖርት እንድናደርግ ያግዘናል። በግፍ እስከ አሁን የተቀጣነው አንሶ፣ ምሕረት ለማግኘትም ያልሠራነውን ወንጀል እንደሠራን አድርገን እንድናመለክት መጠየቅ፣ የአዋጁን መንፈስ መቃረን ሆኖ ይሰማኛል።
በነገራችን ላይ፤ በፓርላማው ውይይት ጊዜ፣ በምሕረት አዋጁ ተጠቃሚ ለመሆን ሪፖርት ለማድረግ የተሰጠው ጊዜ ከሁለት ወር ወደ ስደስት ወር መራዘሙን የተቃወመ ሰውዬ አይቻለሁ። ጉድ እኮ ነው። አምስት ዓመት ያለሥራ እየተከፈለው እንዲኖር በሚፈቅድ ፓርላማ ተቀምጦ፣ የግፍ ሰለባ የሆኑ ሰዎች 4 ወር ተጨማሪ የማሰቢያ ጊዜ አይሰጣቸው ብሎ ይሟገታል። ጊዜው በመራዘሙ በግሉ የሚጎዳው ነገር ኖሮት ነው ወይስ እንዳይማር የሚፈልገው ሰው አለ? የዐይን ሐኪም ያስፈልጋል።
(እዚያ ያያያዝኩት የአዋጁ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ሰዎች እንዲሞሉት የተዘጋጀውን ቅጽ ነው።)
 
Filed in: Amharic