>

“እኛም እንዋደድ ብለን መጥተናል” ዶ/ር አረጋዊ በርሄ

“እኛም እንዋደድ ብለን መጥተናል”

በ አለማየሁ አንበሴ

• በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የመንግስት ሳይሆን የሥርአት ለውጥ ነው


• አሁን የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲጓዝ እናግዛለን


• አንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ምን እንደሚፈልግም አይታወቅም


• ለሁላችንም እኩል የሆነ ስርአት ነው መገንባት ያለብን

    በ1967 ዓ.ም ወደ ደደቢት በረሃ ወርደው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይን (ህወኃት) ከመሠረቱት አንዱ የሆኑትና ባለፉት 30 ዓመታት በውጭ ሃገራት የኖሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በቅርቡ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የፖለቲካ ድርጅታቸውን “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር”ን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከዶ/ር አረጋዊ በርሄ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

    የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብላችሁ ወደ ሃገር ቤት ከገባችሁ በኋላ አቀባበሉን እንዴት አገኛችሁት?
በተደረገልን አቀባበል በጣም ነው ደስ ያለን፡፡ በአካል የማያውቁን ወጣቶች ሳይቀር በጥሩ ሁኔታ ነው የተቀበሉን፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው ከጠበቅነው በላይ ቆንጆ ነው፡፡
ከ44 ዓመታት በኋላ ነው እንግዲህ አዲስ አበባን ያይዋት፤ አዲስ አበባን እንዴት አገኟት?
እውነቱን ለመናገር በቀጥታ ከቦሌ አየር ማረፊያ ወደ ሆቴላችን (ሂልተን ሆቴል) ነው የመጣነው፡፡ ሆቴላችን ከደረስን በኋላ ስራ ስለበዛብን ብዙም መንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡ ግን ከቦሌ እዚህ ድረስ ያለው ሁኔታ ቀድሞ ከማውቀው በጣም ተለውጧል፡፡ ድሮ ከቦሌ መስቀል አደባባይ ድረስ ጫካ ነበር፤ አሁን ግራና ቀኙ ፎቅ በፎቅ ነው የሆነው፡፡ የህዝቡ ብዛትም በዚያው ልክ አድጓል፡፡ አብዛኛው በየመንገዱ የምናየው ወጣት ነው። ብዙ ሥራ ፈላጊ ህዝብ በሃገሪቱ እንዳለ ያመላክታል። በፎቅ ደረጃ አዲስ አበባ አድጓል ማለት ይቻላል። ግን በየመንገዱ ያለውን ወጣት ስትመለከት፣ ገጠሩ ምን ያህል እንደተራቆተ፤ ገጠሩ ሰራተኛን ይዞ ማቆየት እንዳልቻለ ይነግረኛል፡፡ ስለዚህ የተመሠቃቀለ ስሜት ነው ያደረብኝ፡፡ ለወደፊት በጥናትና በአኃዝ የተደገፈ እውቀት ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጣንበት ጉዳይ መስመር እየያዘ ሲመጣ ደግሞ ከተማውንም ሃገሪቱንም ተዘዋውረን ለማየት እድሉ ይኖረናል ማለት ነው፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ከድሮ የህወኃት የትግል አጋሮችዎ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥመዎታል?
አዎ! በርካቶቹን የድሮ ጓደኞቼን አግኝቻቸዋለሁ፡፡ እስካሁን ድረስ በአመራር የቆዩት እነ አባይ ፀሃዬ፣ ስዩም መስፍን፣ ሙሉጌታ አለምሠገድ፣ እነ ጀነራል ፃድቃን፣ ጀነራል ዮሃንስ፣ ጀነራል አበበን አግኝቻቸዋለሁ፡፡
በምን ጉዳይ ላይ ተነጋገራችሁ?
በብዙ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል፡፡ ያለፈው አልፏል ወደፊት እንዴት እንስራ በሚለው ላይ ተነጋግረናል፡፡ ይሄን ትልቅ ሀገር እንዴት ነው ማሳደግ የምንችለው? እንዴት ነው ሠላም የምናመጣው? እንዴት ነው መቀራረብን የምንፈጥረው? በሚለው ላይ ተነጋግረናል። እንዴት ነው ቀድሞ የተነሳንለትንና ሺዎች የተሠዉለትን የአንድነት፣ የእኩልነት፣ አብሮ የማደግ አላማዎች ማሣካት የምንችለው እያልን ተወያይተናል፡፡ በዚህ መንፈስ አብሮ ለመሄድ የተዘጋጁ መሆኑንም ነው ያየሁት፡፡ በዚህ በኩል እረክቻለሁ፡፡

በሃገሪቱ በየአቅጣጫው እየተደረገ ያለውን የፖለቲካ ትግል  እንዴት ይገመግሙታል?

የህወኃት/ኢህአዴግ አምባገነን አፋኝ አገዛዝ በህዝብ ላይ ብዙ ችግር አድርሷል፡፡ ህዝብ ደግሞ ግፍ ተሸክሞ መቀጠል አይችልም፡፡ መብቱን ለማስከበር ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ደግሞ የተጀመረው ዛሬ አይደለም ቆይቷል፡፡ ህዝቡ የለውጥ አመራር በማጣቱ ነው እንጂ ገና ከጅምሩ ነበር የህወኃት/ ኢህአዴግን አምባገነንነት እየታገለ  የነበረው። በተለይ ድምፃችን ይሰማ የሚለው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ ለመጣው ለውጥ አንድ ትልቅ ግንድ ነው የደረመሠው፡፡ የፍርሃትን ግምብ ደርምሷል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ድምፃችን ይሠማ ብሎ መነሣቱ ትልቅ የለውጥ ጀማሮ ነበር። ድምፃችን ይሠማ የሚለው መፈክር በራሱ ትልቅ አፈና እንዳለ የሚያመላክት ጠንካራ መፈክር ወይም የተቃውሞ ማንቀሳቀሻ ነበር፡፡ በወቅቱ በአቶ መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረውን መንግስት ያስጨነቀና በዚህም ሰዎች በብዛት ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ደግሞ ይሄን እንቅስቃሴ ደግፎታል። ከዚያ በኋላ ፍርሃት እየጠፋ መጥቶ ዛሬ ቄሮ፣ ፋኖ የመሣሠሉ እንቅስቃሴ ሃይል ሆኖ ስርአቱን አናግቷል። ይህ ሲሆን ደግሞ ህወኃት/ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ለውጥ ፈላጊዎች የልብ ልብ እንዲሠማቸው አድርጎ፣ በጥንካሬ በድርጅታቸው ውስጥ ታግለው ለውጥ እንዲመጣ አስችለዋል፡፡ የውጭው የወጣቶች ትግልና የኢህአዴግ ውስጥ የለውጦች ሃይሎች እየተናበቡ መጥተው፣ ዛሬ እነ ዶ/ር ዐቢይና አቶ ለማ፣ እነ አቶ ገዱ ፈንቅለው ሊወጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ነገሩ የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ወደ ኋላ የማይመለስ ጎርፍ ሆኗል፡፡ ይሄን የለውጥ ጎርፍ እኛም እንዋኝ ብለን መጥተናል፡፡
ህወኃት ለእርስዎ ምን አይነት ድርጅት ነው?
የብሄር ትግል ሲደረግ ሁለት ስልት ነው ያለው። በአንድ በኩል አፈናን፣ ጭቆናን፣ የመብት መረገጥ እንዳይኖር ለትግል የሚጋብዝ ስልት አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለኔ ብቻ የሚል ለግል ቡድንተኝነት ፍላጎት የተገዛ እንቅስቃሴን የሚጋብዝ ነው፡፡ እኔ…እኔ ሲበዛ ሌላውን በእኩል ለማየት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁለት ስልቶች አጣጥሞ ለመሄድ ከባድ ነው። ምክንያቱም በሁለቱም ስልቶች በኩል የሚጎትቱ ሃይሎች ይኖራሉ፡፡ ወደ መገንጠል ወይም ወደ አንድነት የሚያዘነብሉ ሁለት ሃይሎችን የሚፈጥር አካሄድ ነው፡፡ የመብት መጠበቅ ሲረጋገጥ አንድነትን ሁሉም ይፈልጋል፡፡ የመገንጠል ነገር የሚነሳው ገፊ ምክንያት ሲኖር ነው፡፡ በትግሉ ሂደት መገንጠልን የሚያንፀባርቁ ሃይሎች በብዛት ነበር የተንቀሳቀሱት፡፡ አንድነት ያስፈልጋል የምንለው ደግሞ በየዋህነት መንቀሳቀስ ነበር የጀመርነው፡፡ በኋላ የመገንጠል አላማን ሲያራምዱ የነበሩ ሃይሎች የበላይነት አግኝተው፣ አንድነት የሚለውን ሃይል ፈንግለው ካራቁት በኋላ ደርግን አሸንፈዋል፡፡ እኛ ብዙ አልተጠነቀቅንም ነበር። በዚህ ምክንያት በቀላሉ ልንገለል ችለናል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እያየለ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡—-
ሠፊው ህብረተሰብ ማለትም ገበሬው፣ ሠራተኛው በዋናነት የሚፈልጉት እኩልነታቸው፣ መብታቸው እንዲከበር፣ ሠላምና ሥራ እንዲያገኙ ነው፤ ስልጣን አይፈልጉም፡፡ ስልጣን የሚፈልገው የስልጣንን ጣዕም የሚያውቅ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ፍላጎቱ ከተሟላለት ወደ ሠላሙ፣ ወደ አንድነቱና መደጋገፉ ነው የሚያደላው፡፡ ግን እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉለት፣ እናሟላልሃለን የሚሉ ልሂቃን ይፈጠሩና በየአካባቢው ህዝቡን ቀስቅሰው ወደ ግጭት ሊወስዱት ይችላሉ። አሁንም በሃገሪቱ የሚታዩት ግጭቶች የልሂቃኑ ግጭቶች ናቸው፡፡ በትንሽም በትልቅም ደረጃ ያሉትን ግጭቶች ብንወስድ፣ በልሂቃኑ ፍላጎት የተፈጠሩ እንጂ በህዝቡ አይደሉም፡፡ ህዝብ ሠላምና ሠርቶ መኖር እንጂ የግጭት ዝንባሌ የለውም፡፡  በልሂቃኑ ምክንያት አሁን በየአካባቢው ግጭቶች ተነስተዋል፡፡ ግጭት ለማስነሳት ደግሞ ለልሂቃኑ አመቺ ነገሮች አሉ፡፡ መሬት፣ የውሃ ችግር፣ የግጦሽ መሬት፣ ድንበር፣ የበጀት አመዳደብ ወዘተ– እነዚህ ሁሉ የልሂቃኑ ማነሳሻ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች የበዙት፡፡ የለውጥ አራማጆቹ እነ ዶ/ር ዐቢይ እና አቶ ለማ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ብዙ እየታገሉ ነው፡፡ ለዲሞክራሲ ፈላጊ ሃይሎችም በሩን ከፍተውላቸዋል፡፡ ለምሳሌ እኛ መግባት ችለናል፡፡ ታስረው የነበሩ በርካታ ዜጎች ተፈትተዋል፡፡ ጠመንጃ አንግበው ሲታገሉ የነበሩም በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች ግጭቶችን በሠከነና በተረጋጋ ሁኔታ አይቶ ለመፍታት ያስችላል የሚል እምነት አለኝ።
ድርጅታችሁ “የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር” ማዕከሉ የትግራይ ህዝብ ነው፣ “ህወኃት”ም፣ “አረና”ም፣ “ትህዴን”ም በተመሳሳይ የትግራይ ህዝብ ነው ማዕከላቸው፡፡ ሁላችሁም የብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ነው የምታራምዱት፡፡ ከዚህ አንፃር እናንተ ከሌሎቹ የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶች በምን ትለያላችሁ?
እኛ ስንጀምር ማለትም ከህወኃት ልክ እንደወጣን ህብረ-ብሄራዊ ሆነን ነበር የጀመርነው፡፡ ያኔ በዚህ አደረጃጀት መንቀሣቀስ አልተቻለንም፡፡ ሁሉም በብሄሩ የሚፈረጅበት፣ ብሄሩን የሚፈልግበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ መፈራረጅ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ውስጥ ሳይቀር ገብቶ ነበር፡፡ የትግሬ ገብርኤል፣ የአማራ ገብርኤል፣ የኦሮሞ ገብርኤል እየተባለ ብሄርተኝነቱ ታች ወርዶ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሃገር አቀፍ ፓርቲ መስርተን መንቀሳቀስ አልቻልንም ነበር፡፡ በኋላ ሁኔታውን አጥንተን የተጠቀምንበት ስልት እታች ወርደን ብሄርን አቅፈን፣ ከዚያም ከሌሎች ጋር ተጣምረን ወደ ሃገር አቀፍ ፓርቲነት እንመለሣለን በሚል ነው “ትዴት”ን የመሠረትነው፡፡ ትብብር ያልነውም ለትብብር በራችንን እንደከፈትን ለማሳየት ነው፡፡ አሁንም በዚህ የትብብር መንፈስ ከሌሎች ጋር የመተባበር አላማ ይዘን ነው ወደዚህ የመጣነው፡፡ ስትራቴጂካዊ አላማችን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መፍጠር ስለሆነ፣ ይህ እውን እንዲሆን ከሌሎች ጋር እንሠራለን፡፡ አሁንም እየተወያየን ነው፡፡ 
በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የመንግስት ሣይሆን የሥርአት ለውጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያጣችው ሥርአት እንጂ መንግስት አይደለም፡፡ በየጊዜው መንግስት አላት፡፡ ግን ለዜጎቿ ጠቃሚ ሥርአት አልተገነባም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ሥርአቱ መገንባት አለበት፡፡ ሥርአት ካልተዘረጋ ደግሞ ሁነኛ መንግስት አይኖርም፡፡
ቀጣዩ  እቅዳችሁ ምንድን ነው?
አሁን የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት ባለው መንገድ አንዲጓዝ ማገዝ ነው ዕቅዳችን፡፡ በኛ እይታ የጋራ ሥርአት ነው መመስረት ያለበት፡፡ ከአንድ መጥፎ ሥርአት ወደ አንድ ጥሩ ሥርአት የሚደረግ ሽግግር ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ሽግግር ሥልጣን ላይ ካሉት የለውጥ አራማጆች ጋር ተግባብቶ ወደ መዳረሻው መሄድ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ላይ ነው መሰራት ያለበት፡፡ አብረን ለሁላችንም እኩል የሆነ ስርአት ነው መገንባት ያለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ቁጭ ብሎ መነጋገር ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡
የሃገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ አሠላለፍ እንዴት ያዩታል?
በጣም የተንዛዛ የፓርቲ ፖለቲካ ነው ያለን። አንዳንዱ ምን እንደሚፈልግም አይታወቅም፡፡ ፕሮግራማቸውን ስንመለከት ግን አብዛኛው ተቀራራቢ ነው፡፡ የሁሉንም እንጭመቀው ቢባል ሦስት ሃገር አቀፍ ፓርቲ ቢመሠረት ነው፡፡ አንድ ግራ ዘመም፣ አንድ ቀኝ ዘመምና መሃል ላይ ያለ ቢወጣው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የለም፡፡ በዚህ መንገድ ነው ፓርቲዎች መሰባሰብ  ያለባቸው፡፡ እኛም ከእነዚህ ሦስት ስብስብ አንዱ ጋ ብንገባ ነው እንጂ የተለየ ነገር የለንም፡፡ 
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን የሦስት ወራት የለውጥ እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?
ጥሩ እንቅስቃሴ ነው እያደረጉ ያሉት፡፡ እሣቸውም ቡድናቸውም ጥሩ የለውጥ አካሄድ ላይ ናቸው። ግልጽነት የሌለው የመፈራራት አካሄድ እየተቀረፈ ነው ያለው፡፡ የመደማመጥ አብሮ የመጓዝ ነገር እየተፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ገጥሞን አያውቅም፡፡ በሃሳብ መፎካከር ይቻላል ነው ግባቸው። ይሄ አዲስ ራዕይና አመለካከት ነው፡፡ በዚህ መርህ እየተመሩ ስለሆነ፣ እኔ በሙሉ ልቤ ነው የምደግፋቸው።
ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው እርቅና ሰላምስ ምን አንደምታ አለው?
በኔ አመለካከት አዎንታዊ ነው፡፡ ሁለቱ መንግስታት ጦርነት ውስጥ ነበሩ፡፡ በጦርነቱ የተጎዱት መሪዎቹ አይደሉም፤ ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ነበር የተሠቃየው። ዶ/ር ዐቢይ የሠላም እርምጃውን መውሰዳቸው እረፍት የሚሰጠው ለሁለቱም ሃገራት ህዝቦች ነው። ከዚያ በመለስ እንደ ሀገርም ሁለቱ ሃገራት ንግድና አገልግሎትን ስለሚለዋወጡ፣ ለኢኮኖሚያቸው መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በኤርትራ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እድል ይፈጥራል፡፡ አንድነት ፈጥረንም በፌደሬሽን፣ በኮንፌደሬሽን ወይም በውህደት አንድ አገር ልንሆን እንችላለን፡፡ 
ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው፣ አንድ አይደለም የሚሉ ክርክሮች ይነሣሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን  ነው?
ድርጅትና ህዝብ አንድ ነው ማለት የድርጅትን ምንነት አለማወቅ ነው፡፡ ድርጅት መሳሪያ ነው፡፡ ወደ አንድ ግብ መድረሻ ግብ ነው፡፡ ድርጅት የህዝቡን ፍላጎት ካሟላ ሊወደው፣ ሊያቅፈው ከለላ ሊሆነው ይችላል፤ የማያሟላለት ከሆነ ሌላ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ድርጅትና ህዝብ ልዩነት አላቸው፡፡ ከዚህ ስንነሣ ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደለም፡፡ በእርግጥ ድርጅቱ ህዝቡን አታግሏል፣ ህዝቡም ደግፎት ታግሏል፡፡ ግን ድርጅቱ የተነሣላቸውን አላማዎች ሳያሟላ ሲቀርና ራሱ ጭቆና ሲፈጥር ከህዝብ ይለያል፡፡ ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ እዚህ ነጥብ ለይ ተለያይተዋል፡፡ አሁን የትግራይ ህዝብ እና ህወኃት አንድ ነው የሚል አካል የፖለቲካ ደንባራ ነው የሚሆነው፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ኢትዮጵያ አሁን ሦስት ችግሮች ነው ያሉባት፡፡ አንደኛው ትልቁ ችግር ገዥው መደብ ነው፡፡ ድሮም አሁንም ድረስ ያላት አምባገነን ገዥዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው የሃገሪቱ ችግር የባዕዳን (የውጭ) ሃይሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይሎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ከአምባገነን መንግስታት ጋር እያበሩ ብዙ በደል አድርሰውብናል፡፡ እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን ለብዝበዛ ይፈልጓታል፡፡ ይሄን ማወቅ አለብን፡፡ ሦስተኛው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ህዝቡ ማለቴ ነው፡፡ እኛው ራሳችን ተደማምጠን ተነጋግረን ምን አይነት ሥርአት ያስፈልገናል በሚለው ላይ መግባባት አልቻልንም። መደማመጥ ያስፈልገናል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ካደረግን፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ቅርብ ነው። ሁሉም  ተደማምጦ፣ ተወያይቶ ሃገሪቱን ወደፊት ማራመድ አለባቸው፡፡

Filed in: Amharic