>

ሞሳድ እና ካሳ ከበደ (ሮነን በርግማን - ትርጉም፡ ካሳ አንበሳው)  

ሞሳድ እና ካሳ ከበደ
ሮነን በርግማን (Ronen Bergman)
ትርጉም፡ ካሳ አንበሳው  
ክፍል 1
ይህ የአንድ [የኢትዮጵያ] ከፍተኛ ባለስልጣን ታሪክ ነው፤ አባቱ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ነበሩ፤ በ50ዎቹ እየሩሳሌም ውስጥ ተማሪ ነበር፤ ከአንድ ወጣት እስራኤላዊት ጋር የፍቅር ግንኙነት በመጀመሩ ምክንያት ወደ ሀገሩ ተጠርቷል፤
ቤተ እስራኤሎች ወደ እስራኤል የተመለሱበትን ሂደት ከእስራኤል መንግስት ተወካይ ጋር በመሆን አስተባብሯል፤ ከሞሳድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፤ የመንግስቱ ኃይለማሪያም ስርዓት ሲገረሰስ በእስራኤል አውሮፕላን ተጭኖ ሀገር ለቋል፤ ይህ የካሳ ከበደ ታሪክ ነው፤ አስደናቂ  (fascinating) እና አወዛጋቢ (controversial) ሰው ታሪክ ነው፤
——————
በ1952 አባቱ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ለትምህርት ወደ እስራኤል ላኩት፤ የ18 አመት ወጣት ነበር፤ እስራኤል እንደደረሰ “አኪቫ አልፓን” ወደሚባል ተቋም ገብቶ ሂብሩ ቋንቋ አጠና፤ ቋንቋ አጥንቶ እንደጨረሰ ወደ ሂብሩ ዩኒቨርስቲ አቀና፤ በዪኒቨርስቲው “ካዛ” ተብሎ የሚጠራ የወጣቶች ቡድን ነበር፤ ካሳ በዛ ቡድን ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ ወጣቶች ውስጥ አንዱ ነው፤ የዛ ቡድን አባል የነበሩት ሴቶች ካሳን ዛሬም ያስታውሱታል፤
ካሳ ያንን ወቅት ሲያስታውስ ፈገግ ይላል፤ “ልክ ነው፣ እየሩሳሌም በጣም ውብ ሴቶች ነበሯት፤ ጥሩ ጊዜ ነበር፤ በወቅቱ ሴት አውል (naughty) የምባል አይነት ነበርኩ” ይላል፤
ካሳ ቋሚ የሆነ የፍቅር ግንኙነት አልነበረውም፤ የተረጋጋው ኒታ ኢፍሮኒን (Neta Efroni) ሲያገኝ ነው፤ የሁለቱ የፍቅር ግንኙነት የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር፤ የጥቁር አፍሪካዊ እና የነጭ እስራኤላዊት ይፋዊ የፍቅር ግንኙነት በወቅቱ እንግዳ ነበር፤ ድፍን እየሩሳሌምን ያነጋገረ ነበር ማለት ይቻላል፤ ጥንዶቹ የሀሜት ርዕሰ ነበሩ፤
ኒታ ወስዳ ከቤተሰቦቿ ጋር አስተዋወቀችው፤ የኒታን አህት ኒዛን (Nizza) አገኛት፤ ኒዛን ደግሞ ከእጮኛዋ ከኤሊያሁ ቤን ኤሊሳር (Eliyahu Ben Elissar) ጋር አስተዋወቀችው፤ ኤሊሳር የሞሳድ ዋና ሰው ነው፤
ኒታ እና ካሳ ጋብቻ ለመፈጸም አቀዱ፤ ይህ ወሬ በፍጥነት አዲስ አበባ የንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግስት ደረሰ፤ አባቱ ደጃዝማች ከበደ ጆሮም ደረሰ፤ ይህ አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ቀውስ (international diplomatic scandal) ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤ ተወሰደ፤ ሁለቱ ጋብቻ እንዲፈጽሙ መፍቀድ ማለት ኢትዮጵያ እና እስራኤል ያላቸውን ጥብቅ ሚስጥራዊ ግንኙነትን በይፋ የመለፈፍ ያህል ተደርጎ ተወሰደ፤ ደጃዝማች ከበደ እና ንጉሰ ነገስቱ በጉዳዩ ላይ መከሩ፤ ንጉሱ እህታቸውን በልዩ አውሮፕላን አሳፍረው ወደ እየሩሳሌም ላኳት፤ እሷም ካሳን ፍልጋ ጆሮውን አንጠልጥላ ወደ ኢትዮጵያ ይዛው ተመለሰች።
ካሳ በዚህ ትርክት አይስማማም፤ ተጋኗል ይላል፤ “በእርግጥ አባቴ ከኒታ ጋር የነበረውን ግንኙነት አልደገፉትም፤ መጀመሪያ ከኢትዮጵያዊ ሴት ጋር ሞክረው፤ እሱ ካልተሳካ (ካልሰመረ) ከውጭ ብትፈልግ ይሻላል ነው ያሉት፤ በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ ብለው መልዕክት ላኩብኝ፤ እኔ ግን እስራኤል መቆየት ፈልጌ ነበር፤ እየሩሳሌምን እወዳታለው፤ ኒታን አፈቅራታለው፤”
“የንጉሰ ነገስቱን እህት በተመለከት የሚወራው ግነት አለበት፤ እኔ እስራኤል እያለው የሴትየዋ ባል ሞተ፤ በዚህ ምክንያት ጭንቅላቷ ተነካ፤ ወፈፍ አድርጓት ነበር፤ ንጉሱ ወደ እስራኤል የላኳት የስነ ልቦና ባለሙያ (Psychiatrist) እንድታይ ነው፤ እኔ ያገኝዋት በአጋጣሚ ነው፤ ስንገናኝ ኒታን እንዳላገባ እና ወደ ኢትዮጵያ እንድመለሰ ሀሳብ አቅርባለች፤ ያ ነው የሆነው፤ ጆሮውን አንጠልጥላ ወሰደችው የሚባለው ውሸት ነው፤ እናንተ እስራኤሎች ነገሮችን የፊልም መልክ ማስያዝ ትወዳላችሁ።
የሞሳድ ቅምጥል ካሳ ከበደ ሄድኩኝ ሳይል አዲስ አበባ ታየ፤ መጣው ሳይል ተመለሰ፤ ትላንት ኢሳት ላይ ቀርቦ ከ2 ሰዓት በላይ መጠይቅ አደረገ፤ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ካሳ እዚህ ታየ እንጂ ለምን ታየ ተብሎ አይጠየቅም፤ ብትጠይቅም መልስ አታገኝም፤
የሆነው ሆኖ ካሳ ከበደን በደንብ የማወቅ ጉጉት ነበረኝ፤ በብዙ ልፋትና ቁፈራ በኋላ ገናናው የእስራኤል የምርመራ ጋዜጠኛ (investigative journalist) ሮነን በርግማን (Ronen Bergman) ስለ ካሳ ከበደ እና ሞሳድ “Hebrew-language daily” ጋዜጣ ላይ ያወጣውን 20 ገጽ የምርመራ ውጤት እጄ ገባ፤ የፊልም ስክሪፕት የሚመሰል ጉድ ነው፤ የፈጣሪ ያለህ! ካሳ ከበደ አዲስ አበባ ላይ ሲታይ ትግራይ ኦንላይን ኡኡኡኡኡኡ ያለው ካሳ የደርግ ባለስልጣን ሰለነበር ከመሰለህ ተሳስተሀል፤ ለማንኛውም አንኳር አንኳሩን ተርጉሜ አቀርባለው፤ ሰውየው አዎንታሚ ገጽ ብቻ ያለው ሁኖ አላገኝሁትም፤
…….
(ይቀጥላል)
ፎቶ መግለጫ፤
**በግራ በኩል፡፟ካሳ ከበደ ከባለቤቱ ኒታ ኢፍሮኒ ጋር፤
**በቀኝ በኩል፤ የካሳ ባለቤት (ኒታ) እህት ኒዛ እና ባለቤቷ ኤሊሳር፤ ኤሊሳር ቀደምት የሞሳድ አባል ነው፤ ካሳ ከበደን ለሞሳድ የመለመለው ኤሊሳር እንደሆነ ይታመናል
Filed in: Amharic