>

አዲስ አበባ፣ ከየት ወደየት?  (ዶ/ር ሺመልስ ቦንሣ) 

አዲስ አበባ፣ ከየት ወደየት?
 (ዶ/ር ሺመልስ ቦንሣ)
* “የድሮዋ በረራ (የአሁኗ አዲስ አበባ) የአምሃራ፤ ጉራጌ እና ጋፋት ክርስትና ተከታዮች ይኖሩባት የነበረች ከተማ ነች”
በመጀመሪያ
የዛሬ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ አመት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1878 ንጉሰነገስት ምንሊክ ወደ አርሲ ሰራዊታቸውን ይዘው ይዘምታሉ። ባልተቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እንጦጦ የነበረውን የመንግስት መቀመጫ ወደ አሁኗ አዲስ አበባ ያዛውራሉ። ለጤና ተመራጭ የሆነው ፍልውሃ ፊንፊን ይልበት የነበረው ቦታ ለከተማው መቀየር አንዱ ግብዐት ቢሆንም የአድዋ ድል፣ የመንግስቱ መረጋጋት፣ የእንጦጦ ቀዝቃዛነትና ባካባቢው የነበረው የማገዶ እንጨት እጥረት የአገሪቷን ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመቀየር ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነው አገልግለዋል። ንግስቲቷ የአገሪቷን መናገሻ አዲስ አበባ ብለው ሲሰይሟት ሌላ ፡ ማለትም ስድስተኛ፡ ምክንያት እንድንፈልግ እንድንመረምርም ያደርገናል፣ ታሪክ ።
በስም ወይም ስያሜ ውስጥ ምን አለ? አዲስና አበባ አዲስ አበባ የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፣ አዲስ እና አበባ። የቦታውን ልምላሜና ውበት ከሚወክለው አበባ ከሚለው ስያሜ ይልቅ እንደገና መጀመርን፣ መታደስን፣ መነሳትን የሚያሳየው አዲስ የሚለው ቃል የተለቀ ትርጉም የተሸከመ ስም ይመስላል። ባንድ በኩል ስያሜው የውጭ ወራሪ ጠላትን በማሸነፍ ከመጣው መረጋጋትና እርግጠኝነት በተጨማሪ ስለወደፊቱ የነበረውን ብሩህ ተስፋን፣ ወደፊት ማደግን መመንደግን፣ በአለም ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አግኝቶ መከበርን ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ ወደሁዋላ ተመልሶ ማስታወስን፣ የጠፋን መመለስን ፣ የፈረሰ መገንባትን፣ እንደገና መታደስን ያሳያል። እስቲ በሁለተኛው ትርጉም ላይ በማተኮር ወደሁዋላ ተመልሰን የከተማዋን ታሪክ መረጃዎቹ በሚሉት መሰረት እንመርምር።
ከተማና ታሪክ፣ ከበራራ እስከ አዲስ አበባ
የከተሜነት ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊነቱን ለመረዳት በትንሹም ቢሆን የአገሪቷን ታሪክ ማንበብ ከተቻለም የከተሜነት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ የከተሞች ፍርስራሾችን {ለምሳሌም የሃን፣ አዱሊስን ፣ ቆሃይቶን}፣ ወይንም እስካሁን ያልጠፉትን ፣ ህይወት ያለባቸውን እነአክሱምን፣ ሃረርን፣ ጎንደርን መመልከት ይበቃል። በስነህንጻ፣ በስነጽሁፍ፣ በስነመንግስትና በኪነጥበብ አክሱም የደረሰችበትን የስልጣኔ ከፍታ የተረዳው ማኒ የተባለው ፐርሻዊ ጸሓፊ አክሱማዊት ኢትዮጵያን ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በአራተኛው ክፍለዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዷ ናት ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሃረርና ጎንደርም የከተማነት ዝናቸው በብዙ ቦታ የናኘ መሆኑ ሰፊው ታሪካቸው ቆመው የሚታዩትም የስነሕንጻ ቅሪቶችም ማረጋገጫዎች ናቸው።
ይህንን ስንመለከት የአሁኗ አዲስ አበባ የዚህ ጥንታዊና ጥልቅ የከተማ ስልጣኔ ወራሽ እንጂ
ጀማሪ እንዳይደለች እንረዳለን ማለት ነው። እስቲ ስለአዲስ አበባ ትንሽም ቢሆን ታሪክን ወደሁዋላ እንበል። የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናትም፣ ሆነ የውጭ ሀገር ጸሐፍት የሚያረጋግጡት አሁን ሸዋ ተብሎ የሚጠራውና የአገሪቱ መናገሻ አዲስ አበባ የሚገኝበት አካባቢ ከዛሬ 700 አመት በፊት ማለትም የሰለሞናዊው መንግስት ከተመሰረተበት ከ13ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የአገሪቱ ቁልፍ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚና፣ የባህል ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደነበረ ነው። በጊዜው የነበረው ማዕከላዊው መንግስት ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪ ቢሆንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተሞችን የመሰረተ ሲሆን ትልቁና በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ግን በራራ የተሰኘው ከተማ ነበር። ወረብ በራራ የምትገኝበት ቦታ ሲሆን በመሐከለኛው ዘመን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት እና የነገስታቱ ቤተመንግስት የተሰራበት የነበረ በ16ኛው ክፍለዘመን ደግሞ ብዙ የውጭ ሀገሮችን የጎበኙት ፣ አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴም ከኢየሩሳሌም ጋር ሁሉ ያመሳሰሉት ሀብታም አካባቢ ነበር። ሺሃብ አድ ዲን {በቅጽል ስሙ አረብ ፋቂህ} የተባለው የመናዊ የፍቱህ አል ሃበሻ {የሃበሻመወረር} መጽሃፍ ጸሐፊ የግራኝ አህመድን ጦር በማጀብ ወረብንና በራራን ያየ ሲሆን ወረብን የሀበሾች ገነት ብሎ ጽፎላታል።
የበራራ ከተማ በአሁኗ አዲስ አበባ አካባቢ በተለይም እንጦጦ ላይ የተመሠረተ ሲሆን የኢትዮጵያ መዲናነት ታሪኩ የሚጀምረው በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት {እኤአ1380-1413} ሲሆን የሚያበቃውም በአህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋአዚ {በቅጽል ስሙ ግራኝ አህመድ} ጦር በሚቃጠልበት የአጼ ልብነ ድንግል {እኤአ 1508-1540} ዘመን ነው። እኤአ በ1450 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማው ፍራ ማዉሮ የተባለ ቬኒሲያዊ {ጣልያናዊ} ባዘጋጀው የዘመኑ ፈር ቀዳጅ በሆነው የአለም ካርታ ላይም ለመስፈር በቅቷል። ካርታው መሬት ላይ ባሉ መረጃዎች ተመስርቶ የተሰራ ሲሆን እነሱም አዉሮፓ ከነበሩ ኢትዮጵያዉያንና በተለያየ ወቅት በተለይም በአጼ ይስሀቅ {እኤአ 1414-1430} እና አጼ ዘርዓ ያዕቆብ {እኤአ 1434-1468} ዘመን ኢትዮጵያን ከጎበኙ አዉሮፓዉያን የተገኙ ነበሩ። ሰዓሊ ማዉሮም ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፣
“…{በካርታው ላይ የተመለከቱትን ስለአፍሪካ} 
ደቡባዊ ክፍሎች ማዉራቴ ለአንዳንዶች አዲስ ነገር ሊሆን ስለሚችል በጥንቶችም {በባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ስለማይታወቁ ከሰይቶ ጀምሮ ወደላይ ያለውን ጠቅላላ ስዕል ያገኘሁት ከቦታው ተወላጆች ነው ብዬ እመልሳለሁ። እነርሱም ቄሶች ሲሆኑ {በካርታው ላይ ያሉትን} ክፍለ ግዛቶች ፣ ከተሞች፣ ወንዞችና ተራሮችን ከነስማቸው በእጃቸው ለእኔ የሳሉልኝ እነርሱ ናቸው። ካርታው አሁን ድረስ ያሉ፣ እንዲሁም ስማቸው የማይታወቅ ቦታዎችን የጠቀሰ ሲሆን አቀማመጣቸውንም በመረጃ አስደግፎ ለማሳየት ሞክሯል። ለምሳሌም ከዘረዘራቸው ውስጥ የየረር፣ የዝቋላ፣ የመናገሻና የወጨጫ ተራሮች፣ የዱከምና አዋሽ ወንዞች፣ በወጨጫ ተራራ አካባቢ የሚገኙ የቤተመንግስት ፍርስራሾች፣ ይገኙባቸዋል።”
ከማዉሮ ካርታ በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያዉያንና የውጭ ሰዎች ስለበራራና አካባቢው ብዙ መረጃዎችን ትተውልን አልፈዋል። አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል አሌሳንድሮ ዞርዚ የተባለ የቬኒስ ጣልያናዊ {15ተኛዉና 16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ የመናዊው ሺሃብ አድ ዲን {16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ እና አዉሮፓ የነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት ፡ አባ ዞርጊ፣ አባ ሩፋኤል፣ አባ ቶማስና አባ እንጦንዮስ {15ተኛዉና 16ተኛዉ ክፍለዘመን} ይገኙበታል። እኤአ በ1529 ሽምብራ ኩሬ {በደብረዘይት ወይም ቢሾፍቱና ሞጆ መሃል ያለ ቦታ} በተደረገ ጦርነት ንጉስ ልብነ ድንግል መሸነፉና ወደሰሜን ማፈግፈጉ ወረብንና የአገሪቱ መዲናን በራራን ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን እኤአ በ1530 ቦታዎቹ በግራኝ አህመድ ጦር ለመያዝ ከተማዋም ለመቃጠል በቅተዋል። እንደሺሃብ አድ ዲን ትረካ ከሆነ የግራኝ ሰራዊት በአስር ቀናት ውስጥ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ {የአሁኗ ግንጪ} ተነስቶ በራራ በመድረስ አጭር ቆይታ አድርጓል፣ ከበራራም ሆኖ ግራኝ የተወሰኑ ወታደሮቹን የስድስት ቀን የእግር መንገድ ወደሚፈጀው ደብረ ሊባኖስ ልኮ እንዳቃጠለ ይዘረዝራል። የተቃጠለው የኢትዮጵያ መዲና የነበረው በራራ ከተማ የሚገኝበትን የወረብ ግዛት እንዲያስተዳድር ሙጃሂድ የተባለውን ታማኙን መሾሙንም ይጽፋል።
ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ስለበራራ የሚዘግብ ምንም የጽሁፍ መረጃ አልተገኘም። በ19ተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን የጥንቱን በራራ ታሪክ የሚያስታዉሱ ግኝቶች መታየት ይጀምራሉ። እኤአ በ1881 በንጉስ ምኒልክ የሚመራው የሸዋ ፣ እኤአ ከ1889 በሁዋላም የኢትዮጵያ መንግስት መዲናውን እንጦጦ ላይ ያደርጋል። እንደዘመኑ ትርክት ከሆነ {ድርሳነ ራጉኤል ላይ እንደተጻፈው} የንጉስ ምንሊክ እንጦጦ ላይ መከተም ከስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ታሪካዊ ትርጉም ነበረዉ፣ እሱም ታሪክ የዘከረዉን የጥንቱን የአጼ ዳዊት ከተማን እንደገና መገንባት፣ ወደአገሪቱ መዲናነትም መመለስ ነበር። ንግርቱም ታሪካዊ መሰረት እንደነበረው የሚያመላክቱ መረጃዎች በእንጦጦ {የጥንቱ በራራ ክፍል} የተገኙ ሲሆን ይህንንም በጊዜው ሀገሪቷን የጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች {ዲፕሎማቶች፣ ተጓዦችና ወታደራዊ ባለሙያዎች} ዘግበዉታል። ቻርለስ ማይክል፣ ሲልቬይን ቪኘራስ፣ ሻለቃ ፓወል ኮተን፣ አልበርት ግሌይቸን፣ እና ቸዛሬ ኔራዚኒ፣ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሁሉም በቦታው የነበረዉን ጥንታዊ የመከላከያ ቅጽሩን ተመልክተው ስለጥንካሬዉና ግዙፍነቱ አድናቆታቸውን በጽሁፍ አፍረዋል። እንጦጦ ላይ የፔንታገን ቅርጽ {አምስት ጫፎች ያሉት} ያለው በዙርያውም 12 መመልከቻ ማማዎች የያዘ እንደመከላከ የሚያገለግል ቤተመንግስትና ግንብ የተገኘ ሲሆን ርዝመቱም 520 ሜትር ከፍታውም እስከ 5 ሜትር እንደሚደርስ ታውቋል። የስነህንጻና አርኪዎሎጂ ባለሙያዎች {ለምሳሌም ዴቪድ ፊሊፕሰን፣ ማይክል ዎከርና ማርክ ቪጋኖ እንደተነተኑት ግንቡ እኤአ ከ1550 በፊት የነበረዉን የፖርቱጋልና ስፔን የመከላከያ ግንብ አሰራር ዘዴ የተከተል ሲመስል ቢያንስ የ400 አመት ወይም በላይ ዕድሜ ያለዉና በ16ተኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ምናልባትም በአጼ ልብነ ድንግል የተገነባ እንደሚሆን ነው።
የአዲስ አበባ ምንነት
እንግዲህ በጥንቷ በራራና በአሁኗ አዲስ አበባ መሐከል ታሪካዊ ግኑኝነት እንዳለ ካየን አሁን ደግሞ የሁለቱን ከተሞች በተለይም የአዲስ አበባን መልክ ወይንም ዋና መገለጫ ባህርይ ምን እንደሚመስል እንመልከት። የኢትዮጵያ ከተሞችና መዲናዎች {ለምሳሌም አክሱም፣ ጎንደር} ልክ እንደአገሪቷ ህብረብሄራዊ ገጽታ የነበራቸው ሲሆን በውስጣቸው የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የተለያየ እምነትና ባህል ተከታይ የሆኑና፣ በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም የዉጭ ሀገር ተወላጆች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ነበሩ። ጥንታዊቷ አክሱም በሶስት ቋንቋ {ግዕዝ፣ግሪክ፣ ሳባ} የምትጽፍ፣ ከሶስት ቋንቋ በላይ የምትናገር፣ ከኢትዮጵያዉያን በተጨማሪ ግብጻዉያን፣ የመረዌ {ሱዳን} ሰዎች፣ የመናዉያን፣ የምስራቅ ሜድትራንያን {ፊንቄያዉያን፣ ግሪኮች፣ የጥንት ሶሪያዉያን} ተወላጆች እንዲሁም ህንዶችና ቻይናዉያን የኖሩባት ወይም ደግሞ የሰሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች። ጎንደርም ብትሆን የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ እምነት ተከታዮች አብረው ኖረው {ተለያይተው የሰፈሩ ቢሆንም} ፣ በስራና በህይወት ተስተጋብረው መልኳንና ታሪኳን ውብና ዥንጉርጉር አድርገው የቀረጿት ከተማ እንደነበረች ታሪኳ ይመሰክራል። ሀረርም ከአራቱ የእስልምና ቅዱሳን ቦታዎች አንዷ ስትሆን በብዝሀነቷ እና በእምነት ማዕከልነቷ የምትታወቅ፣ በመቻቻል ታሪኳ የተመሰገነች በዚህም እንደ ታዋቂዉ የፈረንሳይ ገጣሚ አርተር ራምቦ እና እንግሊዛዊዉ ሪቻርድ በርተን ያሉ የውጭ ሰዎችን ለመማረክ የቻለች ምስራቃዊ እንቁ ነበረች፣ ነች።
የበራራም ታሪክ ቢሆን በብዝሃነት ያሸበረቀ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። በከተማዉም ሆነ በዙሪያው ባሉ እንደ ወረብ ባሉ ግዛቶች ይኖር የነበረው ማህበረሰብ በብዛት ከአምሃራ፣ ከጉራጌ እና ከጋፋት {ሶስቱም ተቀራራቢ ቋንቋዎችን ይናገራሉ } የተዉጣጣ እና የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችና እምነት ተከታዮች ይገኙ እንደነበረ ይታሰባል። ለዚህም ምክንያቱ ከተማው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከምስራቅ ኢትዮጵያ በዛም በኩል አድርጎ ከአረቡና የህንዱ ስልጣኔ ጋር በንግድ እና በባህል የተገናኘ ስለነበረ ነው። በበራራ የታሪክና የስነህንጻ አሻራ ላይ የተገነቡት ሁለቱ ወራሽ ከተሞችም {እንጦጦና አዲስ አበባ} የነዋሪዎቻቸው ያሰፋፈር ታሪክ ከዚህ በተለየ መንገድ የተቃኘ አልነበረም፣ ይልቁንም የበፊቱን ታሪክ መሰረት አድርጎ ፣ ብዝሃነትን አቅፎና ደግፎ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሆኖና ተላብሶ የተፈጠረ ቅኝት፣ ያደገ ማንነት ነው ያላቸው፣ በፊትም አሁንም።
አዲስ አበባ ስትመሰረት የነበራትን ጥልፍልፍና ድርብርብ ታሪክ በ19ኛውና በ20ኛ ክፍለዘመን መባቻ ላይ በሃገርኛና በጎብኝዎች የተጻፉ ስራዎች ዘግበውታል። ነገስታቱ በተለይም አጼ ሀይለ ስላሴ ከተማዋ ዘመናዊ ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ሆና እንድትፈጠር ወይንም እንድታድግ ያቀዱና የሰሩ ስለነበር አዲስ አበባ ከተማም፣ የሀገርም ምልክት ሆና በእሷ ውስጥ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያ ውስጥም እሷን እንዲታይ፣ እኛም እንድናይ ሆና ነበር የተቀረጸችው። በእርግጥ በአገሪቱ መሪዎች እና በከተማ ቀራጮች አእምሮ ውስጥ የታለመችው አዲስ አበባ እንደታሰበችው ሁሉ መሬት ላይ ባትሰራም {ለምሳሌ የመሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረት፣ የስራ አጥነት፣ የሀብት ልዩነት ቢስፋፋባትም } ከተማዋ የኢትዮጵያውያን ሆና ኢትዮጵያን ከነዥንጉርጉር ውበቷና ከነውስብስብ ችግሯ መስላና፣ ተመስላ እስካሁን አለች፣ ትኖራለች። አዲስ አበባ፣ አዱገነት ሸገራችን ከብዙ የአፍሪካዉያን ከተሞች በተለየ ድሃና ሀብታም ተሰባጥረው የሚኖሩባት፣ ነዋሪዎቿን ከነብዝሃነታቸው ሳትለይ አቅፋ የኖረች፣ ያኖረች፣ የምታኖር የኢትዮጵያ የልብ ትርታ፣ ነርቭ ማዕከል የሆነች ኦ አዲስ አበባ “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ“ የምንልላት ከተማችን፣ ችግሯም ችግራችን፣ ፍቅራችን እንደገናም ተስፋችን፣ የሆነች ማረፊያችን ሆናለች።
የአዲስ አበባ ማንነት
ይህችን ስብጥር የሆነች ከተማ፣ ንብርብር ታሪክ የተሸከመች ምድር፣ ከመሪዎቿ በላይ የብዙሃን ነዋሪዎቿ ድምር ውጤት፣ የእጅ ስራ ነጸብራቅ ሆና የኖረች ግማደ-ኢትዮጵያ የማን ናት? በብዝሃነት ጥልፍልፍ ተጸንሳ ለተወለደች፣ አድጋም ለጎለመሰች አዲስ አበባ ምንነቷና የማንነቷ ምስጢር በአንድነት ተጋምዶ፣ በልዩነት ውበት አሸብርቆ ደምቆ የተፈጠረ የሃገርነት ቋጠሮ ነው። አዲስ አበባ ልክ እንደኢትዮጵያ የነዋሪዎቿ ስብስብ ውጤት ብቻ ሳትሆን፣ ከድምርነትም በላይ እጅግ የጠበቀ፣ የጠለቀ ጥልፍ ስብጥር ናት። ለመሆኑ እዲስ አበባን ለመፍጠር ያልተጋ ኢትዮጵያዊ እጅ የት አለ ኦሮሞው ከአማራው፣ ጉራጌ ከትግሬው፣ ዶርዜ ከሀረሪው፣ ሶማሌ ከወላይታው፣ ምስራቁ ከደቡብ፣ ሰሜኑ ከምዕራብ፣ ወንዱ ሴቱ፣ ልጅ አዋቂዉ፣ አማኙ የማያምነው፣ ነጋዴው ከምሁሩ፣ ሀገሬዉ ከሌላው ተዋዶ፣ ተዋልዶ፣ ተናግዶ፣ ተቀናጅቶ የፈጠራት፣ ከተማ ከሚባል ነገር በላይ የሆነች ምስጢር አይደለችምን? ከቦታነት በላይ የዘለቀች ሁሉም እምነቷን ካመኑ፣ ሕይወቷን ኖረው ትርጉሟን ካወቁ አባል የምታደርግ፣ እጆቿን ዘርግታ የምትቀበል፣ የራሷ የምታደርግ ትልቅ ሃሳብ {Addis Ababa as an Idea} አልሆነችም? አዲስ አበባ አግላይ ከሆነ የኔነት፣ የኔ ናት ከሚል ህሳቤ ወጥታ፣ ርቃ አልፋ ሄዳ፣ የኛነት፣ የእኛ ናት ወደሚል ሰብሳቢ ሃሳብነት ያደገች ከተማ ሆናለች።
ይህ ማለት ግን ሁሉም እኩል ነበር? እኩል ታይቶስ ነበር? ብዙው አዲስ አበቤ አልተገለለም? እስቲ በምሳሌ እናስረዳ። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን በ1960ዎቹ አመታት በቁጥር 1768 የሆኑ ግለሰቦች 58% የሚሆነውን የከተማውን ቦታ ተቆጣጥረው ነበር። 24000 የሚሆኑት የከተማው ነዋሪዎች 7.4% {በግለሰብ 150 ካሬ ሜትር ማለት ነው} የከተማውን ቦታ ሲይዙ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የከተማው ህዝብ መሬትም ሆነ መኖርያም አልነበረውም። በንጉሳዊው ዘመን፣ ከስርዓቱም መውደቅ በሁዋላ ባሉት መንግስታት በተለይ አሁን ጥቂቶችን በጠቀመ ልማትና ዘመናዊነት ስም ከተሜው ከኖረበት ቀዬው እየተነሳ ይፈናቀላል፣ ከኑሮውም ከማህበራዊ ህይወቱም ይቆራረጣል። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ዙሪያ የሚኖሩት አርሶአደሮችም {ኦሮሞም አማራም ትግሬም ሲዳማም እና ሌሎች ኢትዮያውያን} በአነስተኛ ካሳ መሬታቸውን ይቀማሉ፣ ሰርቶ የመኖር መብታቸውን ይነጠቃሉ። እንግዲህ የአዲስ አበባንና የሌሎች ከተሞቻችንን ታሪክ ስንተርክ እነኝህንና ሌሎች ታሪካዊ በደሎችን፣ ዘመናዊ ነጠቃዎችን የተሸከመ ከተሜነትና ዘመናዊነት ይዘን መሆኑን ሳንዘነጋ ነው።
አዲስ አበባና የዘመኑ ትርክት በአሁኑ ሰዓት፣ እንደ በፊቱ ሁሉ፣ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ቅራኔዎች የሚፈጠሩባት፣ እንዲሁም የሚንጸባረቁባት ቦታ ሆናለች። ውጥረቶቹ በመሠረታዊነት መደባዊ ሆነው በብሄር ማንነት መነጽር ይተነተናሉ፣ በዛም ላይ ተንተርሶ ህዝብን ለትግል ማደራጃ ሆነው ያገለግላሉ። በአሁኑ ጊዜ ሁለት ትርክቶች የከተማውንም ሆነ የአገሪቱን ትኩረት ስበው ይገኛሉ ። ሁለቱም ታሪክን በተለያየ መንገድ ይመለከታሉ የራሳቸውንም በደሎች ያጣቅሳሉ። አንደኛው ህብርብሄራዊ ሆኖ ረጅም የታሪክ ምልከታ ይዞ አዲስ አበባን፣ ከፍ ሲልም ኢትዮጵያን በህብረብሄራዊ መነጽር እያየ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ ያሉ የተንከባለሉ ብሶቶችን በመደብ መነጽር ይተነትናል። ሁለተኛው ብሄርን ማዕከል አድርጎ በቅርቡ የታሪክ እይታ ተመስርቶ ከተማውን፣ በከተማዉና በአገሪቱ ያሉ የተከማቹ በደሎችን በብሄር መነጽር ይሞግታል፣ አማራጮችንም ይጠቁማል።
ሁለቱም እይታዎች እነሱም ላይ የቆሙ ትንተናዎች የየራሳቸው እዉነቶች አሏቸዉ። የከተማዉን ብሎም የአገሪቷን ታሪክ እና ነባራዊ ሁኔታ በራሳቸው መንገድ ይተርካሉ ፣ ይሞግታሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን በሁለቱ መነጽሮች ብቻ መመልከት የከተማዋን በዛውም የአገሪቷን ንብርብር እና ቁልፍልፍ ታሪክና እውነት አበጥሮ ፣ አብጠርጥሮ ለመረዳት የሚያስችል መንገድ አይሆንም። የጎደለ እይታን ይፈጥራልና። በተለይ ደግሞ መጤ እና ነባር የሚለው ትርክት በአንድ አገር ዜጎች መሐከል ደረጃ በማውጣት አንደኛና ሁለተኛ ዜግነትን በመፍጠር የማግለል አንዳንዴም የመንቀል ፖለቲካን ያመጣል። በሰዎች ህይወትም ላይ የሚወስን ነውና አደገኛም ነው። በቅርቡም በመንግስት የቀረበው “የልዩ ጥቅም መብት“ ከፍ ሲልም በአንዳንድ የዘውጌ ልሂቃን የተነሳው “የባለቤትነት“ ጥያቄ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ ያለውን ውጥረት ያሳያል። የአዲስ አበባ የልዩ መብትና የባለቤትነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ እየጦዘ ፣ እንዲጦዝ እየተደረገ ያለው የዜግነት፣ የአገርነትና ፣ የአገር ባለቤትነት ትልቅ ጥያቄ መገለጫ ነው። ታዲያ ምን ይሻላል።
የአዲስ አበባ ምሳሌነት አዲስ አበባ በብዙ መንገድ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗ በየቀኑ የሚታይ እውነታ ነው ከተማዋን ማወቅ ማለት አገሪቷን መረዳት ማለት ነው። የአዲስ አበባን ችግሮች ተረድተን መፍታት ከጀመርን የኢትዮጵያን ጥያቄዎች የመሞገት ፣ ፈተናዎቿንም የመጋፈጥ ታላቅ ስራ ጀመርን ማለት ይሆናል። ከተማዋን የምንመለከትበት መነጽር ፣ ከፍታዎቿን፣ ዝቅታዎቿንና ተስፋዎቿን የምንተነትንበት መንገድ ለአገሪቷም ይሰራልና ለጊዜው እንደዚህ ብንጀምርስ፣ አንደኛ፣ እይታዎቻችን በብሄር ወይንም በመደብ ምልከታ ከማጥበብ፣ እኛም ከመጥበብ ሰፋ አድርገን ፣ ሁለቱንም ተቀብለን ሌሎችም አማራጮች እንዳሉ ግን አጥብቀን ተረድተን ፣ እንሱንም ፈልገን ፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ እይታ ብንፈጥርስ (avoiding the danger of a single story)
ሁለተኛ፣ ከተማችን እንዲሁም አገራችን የብዙዎች እኛነቶች ጥምር ውጤት መሆኗን አምነን ያንዳችን ችግር ወይም ብሶት እንደራሳችን ወስደን እይታቸውንም ዋጋ ሰጥተን ያጋመዱንን ገመዶች ብናጠብቅስ (having radical empathy for fellow countrymen) ሶስተኛ፣ በእኔነት እና በልዩነት ብቻ የገነገነውን ፖለቲካና ትርክታችንን በእኛነት ላይ፣ ድልድይ በመስራት ፣ ከእኛ ባሻገር ካሉ የኛዎች ጋር ባለን አንድነት ላይ አትኩረን። ብንሰራስ (Bridge building, crossing borders)
ሺመልስ ቦንሣ
ህዳር 16, 2010 ዓ.ም.
Filed in: Amharic