>

ከጠ/ሚንስትሩ ጋር ለመወያየት "ኦሮምኛ ቋንቋ በደምብ መቻል" መመዘኛ ሆነና አረፈው!!! (ስዩም ተሾመ)

ከጠ/ሚንስትሩ ጋር ለመወያየት “ኦሮምኛ ቋንቋ በደምብ መቻል” መመዘኛ ሆነና አረፈው!!!
ስዩም ተሾመ
* “እኔ ዘወትር በአማርኛ የምፅፈው ስለ አልባኒያ ነው እንዴ?” 
 
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሚያስተምር ወዳጄ ጋራ በቀጣይ ቀናት ተገናኝተን ለመወያየት እየተነጋገርን ሳለ “ከጠ/ሚኒስተሩ ጋር ለሚደረገው ስብሰባ አዲስ አበባ ስለምመጣ እዚያው መገናኘታችን አይቀርም” አለኝ፡፡ “ከጠ/ሚኒስተሩ ጋር ስብሰባ ያለው መቼና ከማን ጋር ነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ “በቀጣይ ሳምንት ሰኞ እለት ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከዩኒቨርሲቲ ሙህራን ጋር ይወያያል፡፡ ከእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ በአማካይ 100 መምህራን በስብሰባው እንዲታደሙ ተጋብዘዋል? ‘አልተጋበዝኩም’ እንዳትለኝ ብቻ?” አለኝ፡፡ እኔም ነገሩ ገርሞኝ ወደ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ ም/ዲን ጋር ስልክ ደውዬ “በቀጣይ ሳምንት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለሚካሄደው ስብሰባ የመምህራን ስም አስተላልፋችኋል እንዴ?” ስል ጠየቅኩት፡፡ እሱም “አዎ” አለኝ፡፡ “እና የእኔ ስም አልተላለፈም?” እለዋለሁ በድጋሜ “አዎ!” አይለኝም መሰላችሁ?! አምና ከኦቦ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ ጋር አዳማ ላይ በተካሄደው ስብሰባ ላይ አልተጋበዝኩም! ምክንያቱን ስጠይቅ “ኦሮምኛ ቋንቋ በደንብ መናገር የሚችሉ ተብሏል” ብለውኝ ነበር፡፡ በወቅቱ “እኔ ዘወትር በአማርኛ የምፅፈው ስለ አልባኒያ ነው እንዴ?” ብዬ አለፍኩት፡፡ በተመሣሣይ በቀጣይ ሰኞ “ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለሚደረገው ስብሰባ ለምን አልተጋበዝኩም?” ብዬ ስጠይቅ በድጋሜ “#ኦሮምኛ_ቋንቋ በደንብ መናገር የሚችል ተብሏል” አይሉኝም መሰላችሁ? አንደኛ፦ ጠ/ሚኒስትሩ በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ከተወጣጡ ምሁራን ጋር የሚያደርጉት ውይይት በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ይሆናል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ገደቡ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁለተኛ፦ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ 10 መምህራን ቢመረጡ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ብቁ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን፣ የ100 መምህራን ስም ሲተላለፍ የእኔ ስም አለመካተቱ እጅግ በጣም አስገርሞኛል፡፡ በ2009 ዓ.ም “በመንግስት ላይ አመፅና ተቃውሞ የሚያነሳሱ ፅሁፎች ትፅፋለህ!” ተብዬ ወደ ጦላይ ተልኬ በተዓምር ከሞት ተርፌ ስመጣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የ3ወር ደሞዜን ቆርጦ ነበር የጠበቀኝ፡፡ የእሱ ሳያንስ በ2009 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የኢህአዴግ ተሃድሶ ስልጠናን ካልወሰድኩ ከሥራዬ እንደምባረር ማስጠንቀቂያ ፅፎብኛል፡፡ አሁን የመጣው ለውጥ እንዲመጣ የበኩሌን አስተዋፅዖ አበርክቼያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ግን ከጨቋኞች ጎን ቆሞ እኔን ሲጨቁነኝና ሲቀጣኝ ነበር፡፡ ይመስገነው! ያ… ክፉ ዘመን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሰናል! ነገር ግን፣ ከጨቋኞች ጎን ቆመው እኔን ሲጨቁኑኝና ሲቀጡኝ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተመራርጠው ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለመሰብሰብ  ተዘጋጅተዋል! ምነው “ሼም” የሚባል ነገር የለም እንዴ?
ግልባጭ፦ 
ለጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤት
Filed in: Amharic