>
5:13 pm - Sunday April 19, 7722

እውነት ኦሮሞ ብዙ ስልጣን ይዟል? (ብርሃነ መስቀል አበበ)

እውነት ኦሮሞ ብዙ ስልጣን ይዟል?

ብርሃነ መስቀል አበበ

ይቺ ተሿሚው ሁሉ ኦሮሞ ነው የምትለው ወሬ እግር አውጥታ እውነት መስላ ወደ እኛው ሳትመለስ አንድ ሁለት ነገር ማለት ያለብን ይመስላኛል።

እውነታውን እንነጋገር። ኦሮሞ በኢትዮጵያ ፓላቲካ፣ኢኮኖሚ፣ መህበራዊ ተቋማት፣ የኃይማኖት ተቋማት (በክርስትናውም ሆነ በእስልምናውም)፣ በከተማ አሰፋፈሩ እና በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት ውስጥ (አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርን ጨምሮ) የለም። አገር አልባ ህዝብ ተደርጓል።

ኦሮሞ በኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት አለ ተብሎ የሚደለለው እንደባንዲራ ከሩቅ የሚታዩ ውስን ቦታዎችን ለኦሮሞ ግለሰቦች በመስጠት ነው።

ለምሳሌ፣

1ኛ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ ህወሃት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ያቺ የይስሙላ ቦታ የኦሮሞ ነች። ነገር ግን ከምክትሎቹ አንስቶ ቁልፍ የመምሪያ ኃላፊዎችና የክፍለ ከተሞች ከንቲባዎች በሙሉ ኦሮሞ አይደሉም። የማዘጋጃ ሠራተኞቹ ውስጥ በደም ኦሮሞ ነገር ግን ኦሮሚኛ የማይናገሩ ወደ 10% አሉ። 90% ቱ ሌላ ናቸው። የኦሮሞ ህዝብን የሚደልሉት ግን ከንቲባው ኦሮሞ ነው ተብሎ ነው። አዲስ አበባ ባለፉት 15 ዓመታት ብቻ ወደ 700,000 ኦሮሞ ገበሬ መሬቱን ቀምታ አፈናቅላለች። ባለፉት 27 ዓመታት አዲስ አበባ ከአንድ ሚልዮን በላይ ኦሮሞ አፈናቅላለች።

2ኛ፣ ውጭ ጉዳይ፣ ከሁለት ዓመት ጀምሮ ሚንስትሩ ኦሮሞ ነው። የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊዎች ውስጥ ከልተሳሳትኩ አንድ ኦሮሞ የለም። ምክትል ሚንስትሮቹም ውስጥ እንደዛው። ከአስር አመት በፊት እኔ መ/ቤቱን በፓላቲካ ምክንያት ስለቅ ከ600 በላይ ዲፕሎማቶች ውስጥ ኦሮሞ ቁጥር 13 ብቻ ነው።አሁንም እውነታው ይኸው ነው። የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ ኦሮሞ አለ ለማለት አይቻልም። ኦሮሞ ውጭ ጉዳይን ተቆጣጥሮታል ተብሎ ግን ይወራል።

3ኛ፣ መከላከያ ሚንስትር፣ ይህ መ/ቤት የህወሃቶች መሆኑ ይታወቃል። በቅርቡ ግን አንድ ኦሮሞ ሚንስትር ሆኖ ስለተሾመ ኦሮሞ መከላከያን ተቆጣጥሮታል እየተባለ ነው። አንድ ስልጤ ለአመታት የህወሃት ዕቃ ሆኖ አገር ስያሸብር ስልጤ መከላከያን ተቆጣጥሮታል አልተባለም።

4ኛ፣ፕሬዚደንት፣ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ፕሬዚዳንት ምንም ስልጣን የለውም። ምንም ስልጣን ያሌለው ቦታ ስለሆነ ሁሌ የሚሰጠው ለኦሮሞ ነው። ስሙ ትልቅ ስለሚመስል የኦሮሞን ህዝብ መደለያ ሆኗል። ብቸግራኝ ቤቱን ለአፄ ኃይለስላሴ ልጆች ለምን አይሰጡም ብዬ በቅርቡ ፅፌ ነበር። ቢያንስ የኦሮሞ ህዝብ መደለያ አንድ ነገር ይቀንስ ነበር። አሁን ግን ያው ኦሮሞ ስልጣኑን ተቆጣጥሮታል ተብሎ ወሬ ለማሰመር እየተጠቀሙበት ነው።

5ኛ፣ ፍትህ ሚንስትር።ላለፉት 27 ዓመታት ኦሮሞ መታሰር እንጂ በዚህ ቤት የለም። አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ግን አንድ ኦሮሞ ተሾሞ ከእርሱ ቀደም የነበሩት ያሰሩትን ብዙ ሺህ ህዝብ እየፈታ ነው። የፍትህ ሚንስትር የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች በሙሉ ግን የተያዙት በሌሎች ነው። መ/ቤቱ ውስጥ ካሉት ጠበቆች የኦሮሞ ቁጥር ከ5% በታች ነው። ኦሮሞ ፍትህ ሚንስቴርን ተቆጣጥሯል እየተባለ ግን ይወራል።

6ኛ፣ ንግድ ባንክ፣ በቅርቡ አንድ ታታሪና ዕድሜውን በሙሉ ባንክ ውስጥ የሰራ ኦሮሞ በብቃቱ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆኗል። ሌቦቹን ቦታ አስለቅቆ። ሁሉም ምክትል ፕሬዚደንቶች ግን ከሌላ ብሄር ናቸው። ከ240 በላይ የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አንድ ኦሮሞ ብቻ ነው ያለው። የባንኩ ሰራተኞች ውስጥ ኦሮሞ ወደ 8% ነው። ወሬው ግን ኦሮሞ ንግድ ባንክን ተቆጣጥሮታል ነው።

7ኛ፣ የጉምሩክ ባለስልጣን። ይህ መ/ቤት የህወሃት ሌቦች መነሃሪ ነው። ኦሮሞ መ/ቤቱ ውስጥ የለም ማለቱ ይቀላል። አንድ ኦሮሞ በቦታው ሲመደብ ግን ኦሮሞ ጉምሩክን ተቆጣጥሮታል እያሉን ነው።

ዝርዝሩ ብዙ ነው። ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መች ነው እውነት የምንነጋገረው? መች ነው በእውነትና በእውቀት ችግሮችን ወደ መፍታት የምንሻገረው? አረ ይህ ውሸት አገር ያፈርሳል!

Filed in: Amharic