>

ያልሠለጠኑ፣ ጎታች እና ኋላቀር አመለካከቶች ‹‹በቃ!›› ሊባሉ ይገባል!  (ይስሀቅ እሸቱ)

ያልሠለጠኑ፣ ጎታች እና ኋላቀር አመለካከቶች ‹‹በቃ!›› ሊባሉ ይገባል!
 ይስሀቅ እሸቱ
ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂ ዲፓርትመንት የሚያስተምረው ዶ/ር Cherkos WGeorgis በፌስቡክ ገጹ ላይ ከአንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መምህር የማይጠበቅ አሳፋሪ መልእክት አስተላልፎ ነበር – የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ክብርት ኬሪያ ኢብራሂም ከኃላፊነቷ ተነሥታ በክርስትያን ሴት እንድትትካ የሚጠይቅ መልእክት! ዶክተሩ በባለሥልጣኗ ላይ ያለውን ትችት ካሰፈረ በኋላ ኢትዮጵያን ልትወክል እንደማይገባ እና በክርስትያን ሴት ልትተካ እንደሚገባ መግለጹ ያስጸየፋቸው ወንድም እና እኅቶችም ‹‹እንዴት እንዲህ ዓይነት የድፍረት ንግግር ትናገራለህ?›› ሲሉ ትችት ይሠነዝሩበት ጀመር፡፡ (በወቅቱ ከማንም በፊት ንግግሩን ተችተው ኮሜንት የጻፉት የክርስትና እምነት ተከታይ ስም ያላቸው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መሆናቸው አገራችን ለተዋበችበት የሕዝብ ለሕዝብ መከባበር ምሥክር መሆኑ እንዳስደሰተኝ ሳልገልጽ አላልፍም።)
.
ዶክተሩ ትችቶቹን በማየት የጻፈውን ኤዲት ቢያደርገውም በኮሜንት እየመጣ ለመከላከል የሚያደርገው መፍጨርጨር ነገሩን ያባብሰው ጀመር፡፡ ‹‹የአብዬን ለእምዬ›› እንዲሉ የኋላቀር አመለካከት ተጠቂው እሱ ሆኖ ሳለ ተችዎቹን ‹‹ያልሠለጠኑ፤ የአደባባይ ግብረገብ ያነሳቸው›› ሲል በእንግሊዝኛ ይሸነቁጥ ጀመር፡፡ ይባስ ብሎም ባለሥልጣኗ አገር ልትወክል ከማይገባባቸው ምክንያቶች አንዱ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶ/ር Abiy Ahmed የአሥመራ ጉብኝት ወቅት ‹‹ሂጃብ ለብሳ መቅረቧ›› እንደሆነ ይገልጽ ጀመር፡፡ በጥቅሉ ሰዎች ኮሜንት በሰጡት ቁጥር #ኋላቀር የጥላቻ አመለካከቱ እየባሰበት ይሄድ ጀመር፡፡ እንደውም ቆየት ብሎ ከገዛ ብሄሩ ውጭ ያሉ ሰዎች አስተያየት እንደማያስጨንቀው እስከመግለጽ ደረሰ፡፡
.
ልብ አድርጉልኝ… ሰውየው ተራ ሰው አይደለም፤ በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ የሚያስተምር፣ የዶክትሬት ዲግሪ ‹‹የጫነ›› እና ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነት የተሰጠው መምህር ነው፡፡ ዓለማዊ ሥርዓት ባለበት አገር ውስጥ ፖለቲከኞች በሃይማኖታዊ ምርጫቸው ምክንያት ከኃላፊነት እንዲወገዱ መስበክ በእሱ ቦታ ላለ ሰው ከፍተኛ ጥፋት ነው፡፡
.
ጉዳዩ ያበሳጨን ሰዎች በኮሜንት ሳጥን ስንሟገት ቆይተን በሰውየው የአዕምሮ ድህነት ስንገረም እሱ ደግሞ በተራው የመቐለ ዩኒቨርስቲ ስም አብሮ መወሳቱ እንዳስጨነቀው ያስታውቅ ጀመር፡፡ ብዙ ወንድም እና እኅቶችም የግለሰቡን አሳፋሪ አቋም በመሐየስ በርካታ ጽሑፎችን በገጻቸው ይጽፉ ጀመር፡፡ ብዙም ሳይቆይ #መቐለ ዩኒቨርሲቲ በፌስቡክ ገጹ ብቅ ብሎ የዶክተሩን አመለካከት አጥብቆ በማውገዝ ግለሰቡ የተቋሙ ስታፍ መሆን አለመሆኑ እንደሚጣራ በመግለጽ ለማረጋጋት ሞከረ፡፡ አያይዞም ‹‹ለተማሪዎቻችን ሞዴል ናት›› ሲል የገለጻት አፈጉባዔ #ኬሪያ በፖለቲካው ዘርፍ እያበረከተችው ያለውን አስተዋጽኦ እንደተቋም እንደሚያደንቅ እና ከእሷ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ጠቀሰ፡፡ ( https://goo.gl/Dx2mSN ) ዩኒቨርሲቲው እርምጃ ስለመውሰድም ሆነ ስላለመውሰድ በወቅቱ የጠቀሰው አንዳች ነገር ባይኖርም ፈጣን ምላሽ መስጠቱ በእውነቱ የሚያስመሠግነው ነው፡፡
.
በትናንትናው እለት ታዲያ ጉዳዩ ‹‹የእንጀራ ገመድ መበጠስ ጉዳይ›› እየሆነ መምጣቱ ያሳሰበው ዶ/ር ጨርቆስ የ‹‹ይቅርታ›› መልእክት ለመጻፍ ሞክሮ ነበር፡፡ በዚሁ ጽሑፍ ግለሰቡ አጉልቶ ያወጣው ‹‹ሰዎች ንግግሬን ከምሠራበት ተቋም ጋር ያያይዙታል ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር›› የሚለውን መልእክት ነበር፡፡ ይህ መልእክት የሰውየው ዋና ጭንቀት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በጉዳዩ መረበሽ እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡ ‹‹አዎን፤ የምሠራው መቐለ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በአገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከዋነኞቹ ይመደባል፡፡ ተቋሙ (ለእኔ) ከሥራ ተቋምም በላይ ነው፡፡ የፋኩልቲው አባል በመሆኔም እኮራለሁ፡፡ መቼም ከሚቀር ዘግይቼም ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ ስለሚሻል ዩኒቨርሲቲውን ለእኔ ስህተት መልስ እንዲሰጥ በማስጎተቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ…›› ሲልም ለተቋሙ ሞቅ ያለ መወድስ አውርዶ ይቅርታ ጠየቀ – ተቋሙን፡፡ መጨረሻ ላይ ‹‹እንዲሁም በስህተቴ ላስቀየምኳችሁ ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ›› ሲል እንደምንም ይቅርታ መሣይ ነገር ለመተንፈስ ሞከረ፡፡
.
ይቅርታው ከላይ እንዳያችሁት ሙሉ ለሙሉ ተቋሙን ‹‹እርምጃ አትውሰዱብኝ›› ሲል የሚለማመጥ እንጂ ከሚጠበቅበት ሙያዊ ሥነ-ምግባር ባፈነገጠው ኋላቀር ሐሳቡ የተጸጸተ መሆኑን የሚጠቁም አይደለም፡፡ ‹‹አፌን አዳልጦኝ አቅብጦኝ የውስጤን ተንፍሼ የተቋሜን ስም በክፉ አስነሣሁ›› የሚል ኑዛዜ እንጂ መላውን #ሙስሊም ማኅበረሰብ በጽሑፉ በማንቋሸሹ እና ሙስሊሞች በሃይማኖታቸው ምክንያት ከፖለቲካ እንዲገለሉ በአደባባይ በመስበኩ የተጸጸተ ሰው የጻፈው ዓይነት ይቅርታ አይደለም፡፡ ሰው እንዴት በመደመር ዘመን ይህን ዓይነት ኋላቀር እና ጎታች አስተሳሰብ እንደሚይዝ በእውነቱ ግራ ይገባል! ያውም ‹‹አባል በመሆኔ እኮራበታለሁ›› ባለው ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምር መምህር ሆኖ ሳለ!
.
የአቶ ጨርቆስ ዓይነት አመለካከት ኢትዮጵያችን ላይ ምን ጉዳት ያደርሳል?
**********************
.
የአቶ ጨርቆስን አመለካከት የሚጋሩ የኋላቀር እና ጎታች የመጠፋፋት ባሕል አቀንቃኞች እዚህም እዚያም አይጠፉም፡፡ አመለካከቶቻቸው እጅግ ኋላቀር ከመሆናቸውም ጋር አደገኛ ናቸው፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፡-
.
1/ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርን ያደናቅፋሉ፤
.
እኒህን መሠል ኋላቀር አመለካከቶች የመልካም ሕዝባዊ ግንኙነት እንቅፋቶች ናቸው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብን የመዋደድ ገመድ የሚበጥሱ #የፍቅርመቀሶች ናቸው፡፡ በሃይማኖት፣ በ ዘርም ሆነ በማንነት የሚለያዩ የአንድ አገር ዜጎች አንዳቸው አንዳቸውን እንዲጠራጠር እና እንዳያምን፣ አንዳቸው አንዳቸውን እንዲንቅ እና እንዲያስገልል የሚወሰውሱ እኩይ ሐሳቦች ናቸው፡፡
.
2/ ዜጎች ለአገራቸው ፍቅር እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ
.
ዜጎች ለአገራቸው ፍቅር የሚኖራቸው በተግባር የአገሪቱ አካል እንደሆኑ ሲቆጠሩ እና የባለቤትነት ስሜት ሲያዳብሩ ነው፡፡ ይህ የሚመጣው ደግሞ በ #አካታች #ማኅበረፖለቲካ (#inclusive #SocioPolitics) እንጂ በአስማት አይደለም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ልታደርገው የሚገባው ጉዞ የማካተት (የመደመር) ጉዞ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ደጋግመው እየተናገሩ፣ መንግሥታዊ ተቋማትንም በዚሁ ቅኝት ለመቅረጽ እየሞከሩ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የዶ/ር ጨርቆስና መሠሎቹ የአካታችነት #ጥላቻ አገሪቱን ወደኋላ ለመመለስ የሚታገል የከሰረ ጩኸት ነው፡፡
.
3/ አገራዊ አንድነትን ያዳክማሉ፤
.
አገራዊ #አንድነት በማይታይ እና በማይዳሰስ መግነጢሳዊ ኃይል አየር ላይ የሚንጠለጠል ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም በማኅበረ-ፖለቲካዊ መስተጋብር መስተካከል እና በ #ፍትሕ ላይ የሚመሠረት ተጨባጭ ትስስር ነው፡፡ የዶ/ር ጨርቆስ እና መሠሎቹ አመለካከት ይህን ትስስር የሚያዳክም እና ሕዝቦችን ልብ ለልብ የሚያራርቅ አደገኛ ጠንቅ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ መዳከም ደግሞ የጊዜ ጥያቄ እንጂ መጨረሻው መበታተን እና መገነጣጠል ነው፡፡
.
ውዲቷ #ኢትዮጵያ አንድ ሆና ትቀጥል ዘንድ ያላት አማራጭ አካታች ፖለቲካን በመከተል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማጥበቅ እንጂ ማኅበረ ፖለቲካውን ማንነትን መሠረት ባደረገ መድልዎ ማቀጨጭ አይደለም፡፡ የሚጠቅመን ሕዝባዊነት እና የጋራ ተደጋጋፊ እድገት እንጂ የአንድ #ዘር፣ #ሃይማኖት፣ #ማንነት … ዶሚኔሽን አይደለም፡፡
.
4/ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ያደርጋሉ፤
.
አገር እንደሯጭ ልትመሠል ትችላለች፡፡ አንድ #ሯጭ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሙሉ አካሉ ጤናማ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ ግማሽ አካሉ የተጎዳ፣ አንድ እግሩ የተሰበረ አልያም አንድ እጁ የሰለለ ሯጭ ውድድሩን በስኬት ሊጨርስ አይችልም፡፡ በተለያዩ አካሎቹ መጎዳት ምክንያት ጠቅላላ ጥረቱ ከስኬት ደጃፍ ለመድረስ ይቸገራል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ የተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍሏ ከማኅበረ ፖለቲካው የተገለሉባት ኢትዮጵያ ስኬታማ ልትሆን አትችልም፡፡ ሕዝቦቿ በማንነታቸው፣ በእምነታቸው፣ በብሄራቸው እና በባሕላቸው ምክንያት የተገፉባት ኢትዮጵያ ሩቅ ልትጓዝ አትችልም፡፡
.
ሌሎችም ጉዳቶችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም ለጊዜው አራቱ ምክንያቶች ዶ/ር #ጨርቆስ እንዳንጸባረቀው ዓይነት አመለካከቶችን በጽኑ ለማውገዝ ከበቂ በላይ ይመስሉኛል፡፡
.
 ነገሩ ለምን ተካበደ?
.
የዶ/ር ጨርቆስን ጸያፍ ንግግር አንድ ተራ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቢናገረው በምክር ወይም በምልልስ መታለፍ የሚችል ነገር ነበር፡፡ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ የደረሰው ግለሰቡ ከአገሪቱ ዋነኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ በሆነው መቐለ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር እና የዶክትሬት ማዕረግ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህን መሰል ተቋም ውስጥ ያለ ግለሰብ የሚጠበቅበትን ሞራላዊ ግዴታ ፍጹም የጣሰ ይህን መሠል ጸያፍ ንግግር በዝምታ ቢታለፍ ለተቋሙም ሆነ በውስጡ ለሚማሩት ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ትልቅ በደል ይሆናል፡፡ ትውልድን የመገንባት ከባድ ኃላፊነት የወሰዱ መምህራን እንዲህ ዓይነት ኋላቀር አመለካከት ይዘው ወደአዲሱ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ይህ ግለሰብ ሌላው ቢቀር ለፖለቲካዊ ተሳትፎ በተጸየፋቸው ሙስሊም ተማሪዎቹ ላይ ሊፈጽም የሚችለው በደል ሊኖር እንደሚችልም መሠጋት አለበት፡፡
.
ከዚህ አንጻር በየትኛውም የትምህርት ተቋም ውስጥ መምህራን እንዲህ ዓይነት አግላይ እና በጥላቻ የተለወሰ አመለካከት ይዘው ትውልድ እንዲቀርጹ ሊፈቀድላቸው የማይገባ በመሆኑ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ( https://www.facebook.com/MekelleUniversity/)  ይህንን ጉዳይ ግለሰቡን ይቅርታ በማስጠየቅ ብቻ ሊያልፈው የማይገባ እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባስተላለፈው መልእክት ግለሰቡ የስታፍ አባል መሆን አለመሆኑን እእንደሚያጣራ መግለጹ በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የስታፍ አባል መሆኑ በግልጽ ታውቋል፡፡ ዶክተሩም በዋነኝነት ‹‹የተቋሙን ስም በክፉ በማስነሣቱ›› መጸጸቱን በ‹‹ይቅርታ››ው መልእክት ከመግለጹ ውጭ መርዘኛ እና ጠርዘኛ አመለካከቱን ስለመቀየሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንደውም ኮሜንት ሳጥን ውስጥ ያደረገው ክርክር ተቃራኒውን ነው የሚጠቁመው፡፡
.
የትኛውም ስም የገነባ ተቋም መልካም ገጽታውን ጠብቆ ለማቆየት ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ትላልቅ የትምህርት ተቋማት ምንጊዜም ስታፎቻቸው የተቋሙን ሙያዊ (ፕሮፌሽናል) ስታንዳርድ አሟልተው የሚቀጥሉ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሸክም አለባቸው፡፡ በሠለጠነው ዓለምም ቢሆን የጥላቻ ሰበካ (Hate Speech) ወንጀል የሚፈጽሙ መምህራንን የሚታገስ የትምህርት ተቋም የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ከዩኒቨርሲቲው የሚጠበቀው አሥተዳደራዊ እርምጃ እንጂ የይቅርታ መልእክት እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቅጥር ግቢው ያሉት ልጆቻችን በመርዘኛ እና አግላይ መምህራን እጅ ላይ ላለመውደቃቸው ማረጋገጫ የሚሰጠን አሥተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ እና የወሰደውን እርምጃም በይፋ በማሳወቅ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን ነገሩን ከማለባበስ እና የተቋሙ ስታፍ አባላት የፈለጉትን ጥላቻ እየሰበኩ በቀላል ይቅርታ ያለተጠያቂነት የሠላም አየር እንዲተነፍሱ ከማድረግ የተለየ አይሆንም፡፡
.
በበኩሌ ከአገሪቱ ዋና ዋና የትምህርት ተቋማት መካከል ከፊት የሚሰለፈው መቐለ ዩኒቨርሲቲ በዶክተሩ ላይ የሚወስደውን አሥተዳደራዊ እርምጃ በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ ጉዳዩ በቀላሉ የምንፋታው አይደለምና ተቋሙ አለባብሶ ለማለፍ በመሞከር እንደማያጓትተው እና በጉዳዩ ላይ እንድንከርምበት እንደማያስገድደን ተስፋ አለኝ፡፡
.
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (Ethiopian Women Lawyers Association) ከሰሞኑ የሯጭ አትሌት ውዝግብ ጋር አያይዞ ይህንንም ጉዳይ የሚመለከት በሚመስል መልኩ በትናንትናው እለት በገጹ ባሰፈረው መልእክት ‹‹ሴቶችን ለዚያውም በከፍተኛ አመራር ሰጪነት ቦታ ላይ እና ስኬት ላይ ያሉን በአለባበሳቸው እና በውጫዊ አካላዊ አቋማቸው ብቻ ችሎታቸውን መጠራጠር እና በግልጽ መተቸት ሕገ ወጥ ተግባር ነው …. የሴቶች ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ አለባበስ እንዲሁም አካላዊ አቋም ከአስተሳስባቸው ጋር ምንም አያገናኘውም፡፡ ለችሎታቸውም መመዘኛ አይሆንም›› በማለት በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም አንጸባርቋል፡፡ ( https://goo.gl/NxXBqQ)
.
በዚህ አጋጣሚ ትላልቅ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ እንደዶ/ር ጨርቆስ ዓይነት ሰዎች በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚያካሂዱት የጥላቻ ቅስቀሳ በምንም መልኩ በዝምታ ሊታለፍ የማይገባው እና በርካቶችን ለመብት ጥሰት የሚዳርግ በመሆኑ ከሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማትም ቢሆን ተመሣሣይ የውግዘት መልእክቶች ይጠበቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (Ethiopian Human Rights Commission)፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (Human Rights Council { https://www.facebook.com/HumanRightsCouncilEthiopia/ }፣ የሰብዓዊ መብቶች ማኅበር በኢትዮጵያ (https://www.facebook.com/AHREthio.org/)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት (https://www.facebook.com/ehrproj/) እና ሌሎችም የአገር ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ አቋማቸውን ሊያሳውቁን ይገባል፡፡ (ስያሜያቸው እና ታጉ ስላስቸገረኝ አሳስቼ ከሆነ በማረም እና ሌሎች የሚመለከታቸውን ድርጅቶችን በኮሜንት እና ሼር ታግ በማድረጉ ላይ ትብብር እጠይቃለሁ!)
.
አጭር መልእክት ለዶ/ር ጨርቆስ እና የአመለካከት ተጋሪዎቹ 
**********
ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ ብዙ ነገር ቢቀየርም በዋነኝነት የተቀየረው ግን ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ ሙስሊም አባት እናቶቻችን በሃይማኖታቸው፣ በማንነታቸው እና በባሕላቸው ምክንያት ሲያርፍባቸው የኖረውን ሥርዓታዊ ጭቆና ተሸክመው በአቅማቸው እየታገሉ ኖረዋል፡፡ አሁን የዓለም ሥርዓት ተቀይሯል፡፡ እንደዱሮው የፈለጋችሁትን እያስገለላችሁ እና እያጠለላችሁ ልትኖሩ አትችሉም፡፡ አንፈቅድላችሁም፡፡ አገሪቷን የተሸከመው የሁላችንም ጫንቃ ነው፡፡ እጣ ፈንታችን ያለው በሁላችንም እጅ ነው፡፡
.
በዱሮው ዘመን የተወሰነን የሕዝብ ክፍል ከዘመናዊ ትምህርት በማገድ መብቱን የሚጠይቅ ትውልድ እንዳይፈጠር ስትጥሩ ቆይታችኋል፡፡ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላችሁ ይሆናል፡፡ ዛሬ ግን በግሎባላይዜሽን ዘመን ይህንን ልታደርጉ የሚቻላችሁ አይደለም፡፡ የትም ብትዞሩ አብረናችሁ አለን፡፡ “WE ARE HERE TO STAY SO GET USED TO IT!” ይላል ፈረንጅ – ‹‹አለን! የትም አንሄድምና ልመዱት!›› እንደማለት፡፡
.
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ምድር ማንም ማንንም እንደፈለገ ሊገፋ አይችልም! ዘመኑ የሕዝብ ማዕበል ዘመን ነው! ዘመኑ የ #ድምጻችንይሰማ ዘመን ነው! የ #ቄሮ ዘመን ነው! የ #ፋኖ ዘመን ነው! የሕዝባዊ ትግል ዘመን ነው! ከምንም በላይ ደግሞ ዘመኑ የ #መደመር፣ የመባዛት እና የመካፈል ዘመን ነው! በጊዜ ኋላቀር አመለካከታችሁን አስወግዱ! በፍየል ዘመን በግ አትሁኑ! በሠለጠነ ዘመን ‹‹እንጥል እንቁረጥ፣ ግግ እንቧጥ›› አትበሉ! ለራሳችሁ እወቁበት… አለበለዚያ ‹‹ኋላቀር›› የሚለው ቃል እጣ ፈንታችሁን የጸነሰ ቃል ሆኖ ኋላ ቀርታችሁ ትቀነሳላችሁ!
Filed in: Amharic