>

በማይጠፋ ቀለም የተጻፈ… ወርቃማው  የካርል መልዕክት! (አሰፋ ሀይሉ)

በማይጠፋ ቀለም የተጻፈ… ወርቃማው
 የካርል መልዕክት!
አሰፋ ሀይሉ
ብዙ ጊዜ የምመላለስበት መንገድ አይደለም፡፡ ግን እግር ጥሎኝ በሣርቤት አሳብሬ ካለፍኩ ወደ ብሥራተ ገብርዔል በሚወስደኝ አደባባይ መሐል አናት ላይ የተተከለውን ይሄን የካርል (የካርል ሄንዝ በም) ምሥል አንጋጥጬ ሣልሳለም አላልፈውም፡፡ ካርል አሁን የለም፡፡ ትቶልን የሄደው ‹‹ሜንሽን ፎር ሜንሽን›› (‹‹ሰዎች ለሰዎች››) የተባለ የኢትዮጵያውያን ወገን ለወገን መረዳጃ ግብረ ሰናይ ድርጅት ግን አለ፡፡
ትናንት ካርል ባነፀው የሜንሽን ኮሌጅ የሠለጠኑ የጤና ሳይንስ ባለሙያዎች ብዙዎችን ኢትዮጵያውያን እናቶች ከምጥ ገላግለዋል፣ ብዙ የወደፊቱን ሀገር ተረካቢ ህፃናትን አዋልደዋል፡፡ የብዙዎችን ስቃይ አስታግሰው ወደ ፈውስ መልሰዋል፡፡ ካርል አስተምሯቸው ያለፈው የኤሌክትሪካል ሣይንስ ባለሙያዎች ኤልፓም ይግቡ አየር መንገድ ወይም የትኛውም ፋብሪካ.. በየገቡበት ሥፍራ የሀገራችንን አገልግለዋል፡፡ ካርል ያስመረቃቸው የሜካኒካል ሣይንስ ባለሙያዎች.. ዛሬ በየተሽከርካሪው ኢንዱስትሪ፣ በየገራዡ፣ በየፋክተሪው በብርቅ የሚፈለጉ ብቁ ሙያተኞች ሆነዋል፡፡ ካርል የረዳቸው፣ ያስተማራቸው ህፃናት — ዛሬ አድገው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ፣ ሌሎችን የሚረዱ፣ የታነፀ ንፁህ ዜጋ የሚያፈሩ ድንቅ ዜጎች ሆነዋል፡፡
ካርል መኪናም ሆነ መንግሥት በማይዘልቃቸው ሩቅ ሩቅ የተረሱ የሀገሪቱ ክፍሎች ድረስ ሄዶ የሠራው ሆስፒታልና በየጫካው መሐል… ምንም ነገር ሳያግዳቸው.. እንደ ትንግርት ደርሰው ለህዝባችን ጤናን እያላበሱ ያሉ፣ ቢያንስ ቢያንስ የአንዲት ቀን ስቃዩን እያስታገሱ የቆዩ የእፎይታ ተቋማት ሆነዋል፡፡ ካርል ከሁሉ ቀድሞ… ሌላ ቀርቶ በከርቸሌ የሚገኙ እስረኞች በሜንሽን ፎር ሜንሽን ሠልጥነው የመስኖ እርሻ እንዲያለሙ፣ ለአካባቢያቸው ህዝብ በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ እንዲመግቡ፣ እና ከገቢውም ተጠቃሚ ሆነው በመታሰራቸው ኑሮ የጎደለባቸውን ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ፣ ለራሳቸው የማይደበዝዝ-ዋጋ-ያለው-ሰውነት፣ ለቤተሰቦቻቸው የትም ይሁኑ የት በአለኝታነት የሚቆሙ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጋ መሆናቸውን እንዲያውቁት፣ እንዲሰማቸው ታላላቅ የሰው ልጅ ቅፅሮችን አልፎ ማሰብና ያሰበውን ማድረግ የቻለ ድንቅ የሰብዓዊ ፀጋ ባለቤት ነው፡፡
ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ (ቢያንስ ከሁለትና ሶስት አሰርት ዓመታት ጀምሮ ገና ሥራው ባገራችን ሰው ልብ ገዝፎ በውል ሳይታወቅለት ገና ያኔ)… ካርል በሜንሽን ፎር ሜንሽን ራስን ችሎ ለሌላው የመትረፍ የእርሻ ሥራ ፕሮግራም… እንዲገቡ አድርጎ… የተለያዩ የምግብ አትክልቶችን እያመረቱ… በአቅራቢያቸው ላሉ ከተሞች ነዋሪዎች በማቅረብ… ታላቅን ሥራ ለአካባቢያቸው ህዝብ እንዲያከናወኑ፣ ለራሳቸውም በየከተማው የሚታዩ የገበሬዎች ማከፋፈያ ሱቆችና የብዙ ገቢ ባለቤቶች እንዲሆኑ ያስቻላቸው…  ገበሬዎችና የገበሬ ልጆች እጅግ በርካታ ነበሩ፡፡
መጠለያ የሚሆን ቤት በማጣታቸው ብቻ፣ የገንዘብ ዋስትና የሌላቸው ደሃ-አደግ በመሆናቸው ብቻ፣ መጠጊያ የሚሆናቸው ቤተሰብ ስለሌላቸው ብቻ.. ሀገራቸው ምን ደሃ ብትሆን.. በሜዳ ተበትነው እንዳይቀሩ፣ የባዕድነት ሥሜት በውስጣቸው ዘልቆ እንዳይጎዳቸው፣ ብቸኝነትና የመጣል፣ የመገለል ስሜት እንዳያድርባቸው፣ በኑሮ አቋማቸው የበታችነት እንዳይሰማቸው፣ መጠቃት እንዳያድርባቸው፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር… ካርል ብዙ ብዙ ህፃናትን እና ወጣቶችን ከያሉበት ጥግ እየሰበሰበ በአዳሪ ት/ቤት እያስገባ እስከ ኮሌጅ አስተምሯል፡፡ አንዳንዴ ራሳችንን ብቻ የደግ መጨረሻ፣ ራሳችንን ብቻ የእንግዳ ተቀባዮች መጨረሻ፣ ከኛ በላይ አዛኝ የሌለ የአዛኞች መጨረሻ፣ የፈሪሃ እግዜር ብቸኛ መገኛና መድረሻ አድርገን ለምንቆጥር.. ለብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን.. ምናልባት ልብ ካልነው… ይህ የካርል ሥራ… ያለንግግር ብዙ አስተምሮን አልፏል — ብዬ በበኩሌ በግሌ — አፌን ሞልቼ መናገር እችላሁ፡፡
ካርል ጥቁር ነጭ አላለም፡፡ ካርል ዘር አልቆጠረም፡፡ ካርል ኦሮሞ አማራ አላለም፡፡ ካርል ትግሬ ወላይታ አላለም፡፡ ካርል በስህተት እንኳ የቆጠረው ዘር ቢኖር አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ክቡሩ የሰው ዘር ነው፡፡ የሰው ልጅ ዘር ብቻ፡፡ በአንድ ወቅት በምድረ አውሮፓ ስመጥር የፊልም ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ከሀብታም ቤተሰቦችም የወጣው — ይሄ ካርል ሄንዝ በም የተሰኘ የሰው ዘር— ሌላ ቀርቶ — ያገባት ኢትዮጵያዊት ሚስት (አልማዝ — ስምን መልዓክ!!) ማንነት እንኳን — ሌላው ሌላው ቢቀር — ካርል የተላበሰውን በሰብዓዊ እሴት የጎለበተ፣ በሰውነት ሚዛን የላቀ — እና ፍፁም ከወረደ ዘረኝነት — ፍፁም የጸዳ — ፍፁም ጤናማ የሆነ የሰው ልጅ መልካም አስተሳሰብ ባለቤት መሆኑን — ያለምንም ተጨማሪ ቃል — ቁልጭ አድርጎ ይመሰክርለታል፡፡
እና እንግዲህ — በእነዚህ እና በሌሎች ተነግረው በማያልቁ ምክንያቶች የተነሣ ነው… — ዛሬም ሆነ ወደፊት… — ችዬ ቆሜ በህይወት እስከተመላለስኩ ድረስ — መልዓኩን ብሥራተ ገብርኤልን ከመሣለሜ በፊት… — ቀና ብዬ… — እጅግ ቅን ከሆነ አስተሳሰቡ በስተቀር — እንደ እኔው ሰው የሆነውን — ሰብዓዊ ፍጡርነቱ ከእርሱ ያልራቀውን — ሰብዓዊ እሴቱ ሳይለየው የኖረውን… — የማከብረውን ካርልን.. — ባረፈበት አደባባይ አናት እንዳለ — ከመንገዴ ቀና ብዬ ሣልሳለመው የማላልፈው!!
ካርል ታላቅ የኢትዮጵያውያን ወዳጅና ቤተሰብ ነው፡፡ ካርል በአካል ቢሞትም… በሰብዓዊ መንፈሱና በማይሞቱ ሰብዓዊ ሥራዎቹ — ገና ወደፊት ለትውልድም ካርልነቱን በተግባር እየተረጎመ፣ ብዙዎችን እያስተማረ፣ ብዙዎችን መልካምነት እያላበሰ፣ ዜጎቻችንን እያነፀ መኖሩን ይቀጥላል፡፡ በተለይ በተለይ — በተለይ — ላለፉት ዓመታት በትውልዳችን ላይ ሲዘራ የከረመው.. — እና በአሁን ሰዓት ፍሬውን አፍርቶ… — ልክ የአባያችንን መነሻ ጣናን እንደወረሰው… ልክ እንደ እንቦጭ አረም ሁሉ… — ስንት ነገርን ሊፈጥር የሚችለውን የሀገራችንን አምራች ትውልድ… — ከጫፍ ጫፍ ወርሶት የሚገኘው… — ይህ በአካል በአምሳል ዘወትር በምድራችን እየተመላለሰ አስቀያሚ ጥምቡን ሲጥል የምናየው — እጅጉን የጠበበ እና የወረደ… — ከዓለም እጅጉን ወደ ኋላ የቀረ እና የሚያስቀረን — እጅግ አሳዛኝ የዘረኝነት አረም — ሁላችንን እኛን ተስፋ ከነምንጥልባቸው ትውልዶቻችን ጭምር በተፀናወተን በዚህ ፈታኝ ሰዓት…— በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት — የካርል ፍፁም ከዘረኝነት ነፃ የሆነ፣ ፍፁም ጎሰኝነት ያልዳሰሰው — እና እንደ ሰው ልጅ አስቦ — እንደ ሰው ልጅ የተንቀሳቀሰ… — እጅግ አስደናቂ ሰውነት — እና እጅግ አስደማሚ ሰብዓዊነት — ለእኔም፣ ለአንተም፣ ለአንቺም፣ ለሁላችንም፣ ለመጪው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ሁሉ — አንዳች መልካምነትን የተላበሰ ፈዋሽ ሰብዓዊ ቅመምን የሚለግስ — ትልቅ የመልካምነት ማብሠሪያ አብነት ነው፡፡
በአንደም ሆነ በሌላ መልኩ — ማናችንም ብንሆን — ባለፍንበት፣ በዋልንበት፣ ባደግንበት፣ ወይም በስልት በተዘራብን ሀገር አቆርቋዥ የአረም ዘር — በውስጣችን እንዲበቅልብን በሆነው — ቀንድ ያወጣ ዘረኝነት ተታልለን — ወይም ተነድተን… — ወይም አምነን —ትልቁን ሰብዓዊ ማንነታችንን ከናካቴው ልንረሳው እንዳንቃረብ — እንዳንረሳው… — በዝንጋታ ልንረሳው የዳዳንም ካለን — ጨርሶ ሰብዓዊነታችንን ከልባችን አውጥተን እንዳንጥለው — ሰብዓዊ ልቦናችንን፣ ሰብዓዊ አዕምሯችንን፣ ሰብዓዊውን የህሊና ሚዛናችንን ከውስጣችን እንዳናከስመው — …. ዘወትር የለመለመ ሰብዓዊነትን፣ ለወገን-ደራሽ የሆነ ታላቁን የሰብዓዊነት ክብራችንን — ባለፍ ባገደምን ቁጥር የሚያስታውሰን — ይህን የዘር ጥግ እና የቋንቋ አጥር እና የቀለም ግድግዳ የሌለውን ሰብዓዊነት ለትውልድ የሚዘክር — ትልቅ ቁምነገርን ያዘለውን — ትንሹን የካርል መጻሸቢያ ኃውልት — ትልቁን ሰብዓዊነት ማስታወሻ ማንቂያ ደወላችን ሊሆን የሚገባው ነው በእውነቱ፡፡ ዘረኝነት ከወለደው ክፋት ራሳችንን መጠበቂያ ካስፈለገ… — ባጠገቡ እልፍ ይበልና — ታላቅ የትውልድ ልጓምን ከካርል ጭንቅላት ይቀበላል፡
እና ባጠገቡ ካለፍክ — ባጠገቡ ካለፍሽ — አደራህን፣ አደራሽን — አንድ ነገር አንርሳ፡- ለካርል — ይገባዋል ሠላምታ፡፡ ይገባዋል ክብር፡፡ ይገባዋል በቀን ሶስት ጊዜ መታወስ፡፡ ይገባዋል ሰብዓዊ ሥራው ዘወትር መዘከር፡፡ ምክንያቱም — ካርል — የመልካምነት አርዓያ ሰብዕ ነው፡፡ ምክንያቱም — ይህ ሲንቀሳቀስ የሚታይ አካላችን ብቻ ሣይሆን — አዕምሯችንም — ጤናማ መሆን ያስፈልገዋልና ነው፡፡ ምክንያቱም — ልክ አካላችንን… ጥሩ ጥሩ አልሚ ንጥረ-ነገር ስንሰጠው፣ በመልካም ጤንነት እንደሚያመላልሰን ሁሉ — እና መጥፎ መጥፎውን ስንግተውም በአጣዳፊ ህመም እንደሚቀስፈን ሁሉ — አዕምሮአችንም — በጤንነት ጎዳና፣ በመልካምነት መንፈስ፣ በሙሉ የመልካምነት አቅሙ ይመላለስልን ዘንድ — እንደ መንፈስ ምግብ የሚሆነው — እንደ ካርል ያለ — መልካም ሰብዓዊ አስታዋሽ እስትንፋስ — መልካም ሰብዓዊነትን ማጎልመሻ አብነት — መልካም ሰብዕናን መመልከቻ መነፅር፣ ማየት፣ መመገብ፣ እና መጥገብ ያስፈልገዋልና ነው፡፡ እና … ከብዙው  ባጭሩ… — አዕምሮውን በመልካም ሃሳቦች መሙላት ለፈለገ — ከስንት አንዴም ቢሆን — በካርል አጠገብ ይለፍ፡፡ እና ቀና ብሎ ይመልከተው፡፡ ያን ጊዜ — ዘር ያልገደበው ሰብዓዊነት — በዘር የተሸነሸነውን ከንቱ እሳቤ — በመልካምነት ድል ሲነሳው — በአካል — በአምሳል — ያያል፣ ያስተውላል፣ ያስታውሳል፣ ያምሰለስላል፣ ይገባዋል፣ ይዘልቀዋል! (ወይ እንደ እኔ.. ኩም ይላልና!)፡፡
እመኑኝ — ማንም — ላፍታ — በካርል አጠገብ — ልብ ብሎ ያለፈ ሀበሻዊ ፍጡር — መቼም ቢያንስ ቢያንስ — ሰብዓዊነት — መልካምነት — ግብረገብነት — እንደ ሰው.. ሰውን መርዳት.. እና መረዳዳትን.. — ቢያንስ ለአንዲት ሰከንድ በአዕምሮው ሣያውጠነጥን አያልፍም፡፡ እንዲያውም በቃ — የካርል ፊት ላይ — የካርል ዓይኖች ላይ — የካርል ማንነትና ሰብዓዊነት ላይ — እንዲህ የሚል ‹‹‹እስቲ ድፈር?›› የሚል መልዕክት በማይታወቅ ሰብዓዊ ቋንቋ የሚተላለፍልህ ይመስለኛል፡-
‹‹ማንም ህሊና ያለው ሰው ቢኖር— እስቲ ልቡን አዘጋጅቶ በእኔ
በካርል ሰብዓዊነት ሥር እልፍ ይበል — እና — በምንም ዓይነት
የዘር ማንዘር ትብታብ ያልተጠላለፈውን — በጭፍን የዘረኝነት
ጉድጓድ ዝቅ ብሎ ወርዶ ያልተቸነከረውን… — ከበላዬ እንደምታዩት
የገዘፈ ሠማይ.. እጅግ  የገዘፈውን ታላቅ ሰብዓዊ ልባስ — ድንበር
የማያግደውን ታላቅ ሰብዓዊ ማንነት — እነሆ በምትዞሩበት ሥፍራ
ሁሉ ተሸክማችሁ እንድትሄዱ — በመዲናችን መሐል አደባባይ
ቆሜ — እነሆ ሰብዓዊ መልዕክቴን በፍቅር አስተላልፍላችኋለሁ!››
የሚል — የካርልን ፊት በማየት ብቻ በውስጥህ እንደ መግነጢሳዊ ኃይል ንዝር ብሎ የሚሰርፅብህ — የሆነ አንዳች አስገራሚ ሰብዓዊ መልዕክት ሁሉ የሚረጭብህ ይመስለኛል፡፡
ለማንኛውም — በማይሞተው ህያው እና ለትውልድም ቀጣይ በሆነ ተግባሩ — የሰው ልጅነት ፀጋ … የትልቅ ፍጡርነት ፀጋ መሆኑን እንዲህ — በዓይናችን — በትውልዳችን — ለትውልዳችን በተግባር አሣይቶን ላለፈው — ለታላቁ ወገን-ደራሽ ወንድማችን — ለካርል ሄንዝ በህም — ባረፈበት የገነት አፀድ — የማያልቅ ክብር፣ እና የማይጠወልግ ፍቅር፣ እና የማይነጥፍ እረፍት፣ እና እጅግ እጅግ እጅግ የበዛ… ዘለዓለማዊ እፎይታና ሠላም ይሆንለት ዘንድ ከልብ እንመኛለን!!!
የካርል ቀለም ነጭ አይደለም፡፡ የካርል ቀለም ጥቁር አይደለም፡፡ ‹‹ካርል›› የሚለው ቃል — የዘር፣ የቀለም፣ የጎሳን፣ የዘረኝነትን አጥሮች ሁሉ በፍቅርና በሰብዓዊነት ቀለም የተሻገረ — እና በመካከላችን በወገን ፍቅር ሲመላለስ ኖሮ፣ ደክሞ፣ በሰላም ያረፈ — የአንድ መልካም ሰው መጠሪያ ስም ነው፡፡ የካርል ማንነት የዘር ውክልና የለውም፡፡ ድንበር የለውም፡፡ አጥር የለውም፡፡ ቀለም የለውም፡፡ የካርል ቀለም ወርቃማ ነው፡፡ ወርቃማ ሰብዓዊ ቀለም፡፡ እና በዚያ ሰብዓዊ ወርቃማ ቀለሙ… ወርቃማ ሰብዓዊ ሥራውን… ለእኛ ለሚወደን ኢትዮጵያውያን ትውልዶች ጽፎልን… ትቶልን… በመካከላችን አረፈ፡፡ ‹‹ሜንሽን ፎር ሜንሽን››…. ‹‹ሂዩመንስ ፎር ሂዩመንስ››… ‹‹ሰዎች ለሰዎች›› ! አዎን! ለሰው መድኃኒቱ — ሰው ነው!!! ለወገንም መድኃኒቱ ወገን፡፡ ማለፍ ካልቀረ — እንዲህ — እንደ ካርል — መድኃኒት ሆኖ ነው እንጂ! አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ አምላክ — መላ ኢትዮጵያውያንን — እና ኢትዮጵያውያንን ያሉ ወንድሞቻችንን — እህቶቻችን — አባቶቻችንን — እናቶቻችንን — እና ወደፊትም ኢትዮጵያውያንን የሚሉ ትውልዶቻችንን ጭምር — አብዝቶ — አብዝቶ — አብዝቶ — አብዝቶ ይባርክ፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ — ምስኪኗ እናት ሀገራችን — ለዘለዓለም በልጆቿ የበዛ ፍቅር ተሞልታ — በልጆቿ እልፍ ፍቅር ተፈውሳ — በእልፍ አዕላፍ ልጆቿ ኅብረት ፀንታ — ለዘለዓለም ትኑር፡፡
የፎቶ ምንጭ/ምስጋና፡-
ካርል ወርቃማ ቀለም የተቀባ የገዛ ራሱን የፊት ኃውልት (‹ቡስት›) በስሙ የተሰየመውን አደባባይ መርቆ በሚከፍትበት ዕለት ከባለቤቱ ከአልማዝ ጋር ተገኝቶ የተነሣው ፎቶግራፍ (በበጎነት ፎቶውን በድረገጽ ላካፈለን ለአላሚ ፎቶ አርካይቭስ፣ እና በፎቶው ለምናያቸው በጎ አድራጊ ወገኖች ለካርልና ባለቤቱ አልማዝ እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
‹‹Founder of the ‘People for People’ Foundation, Karl Heinz Boehm (L), and his wife Almaz Boehm stand in front of a sculpture with Boehm’s likeness unveiled – Alamy photo archives››
Filed in: Amharic