>

ወደ አገር ቤት የገቡት ተቃዋሚዎች ከህወሀቱ ሎቢስ ቆስጠንጢኖስ ጋር ምን ይሰራሉ?!? (ኤርሚያስ ለገሰ)

ወደ አገር ቤት የገቡት ተቃዋሚዎች ከህወሀቱ ሎቢስ ቆስጠንጢኖስ ጋር ምን ይሰራሉ?!?
ኤርሚያስ ለገሰ
“አገርቤት ጠቅልለው ስለገቡ አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችና አመራሮች እየሰማሁት ያለሁት መረጃ ደስ አይልም። በጣም ደስ አይልም።
#ከገቡ ቀን ጀምሮ ሸራተን አዲስ ውሎና አዳራቸውን ያደረጉ እንዳሉ ይሰማል። የውሎና አዳሩን የአንዲት ቀን ሂሳብ ይሰራ ቢባል በትንሹ 5ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይሆናል። በአንድ ወር ውስጥ ለአንድ አመራር ብቻ ወደ 150ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው። እናም ይሄን ከፍተኛ ገንዘብ እየሸፈነ ያለው ማነው?
#አንዳንዶቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አዘውትረው የሚገናኙት እና የሚያመሹት ከህውሓት ከፍተኛ አማላይ (ሎቢስት) ከሆነው አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ ጋር ነው። እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ? ህውሓት ለቆስጠንጢኖስ የሰጠው ተልእኮ ምንድነው? የሸራተን አስተናጋጆች እስኪታዘቧችሁ ድረስ ከቆስጢ ጋር የኮኛክ ብርጭቆ ማጋጨት ምን የሚሉት ነው?
#አንዳንዶቻችሁ እንደ ድርጅትም እንደ አመራርም አገር ቤት ከገባችሁ ወራት ተቆጥረዋል። የምንመለከታችሁ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የራሱን በአላት እና ስብሰባ ሲጠራ በፊት መስመር ተሰልፋችሁ ከማየት ውጪ የተለየ ነገር መመልከት አልቻልንም። የኢህአዴግ ሊቀመንበሩ ዶክተር አቢይ የሶስት ወራት ፍጥነቱ “ማይክል ቦልት!” እያስባለው ነው። እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው?
በአንድ ወቅት የፌዴራል የስራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ የለውጥ አመራር አሰልጣኝ የነበረ አቶ አይችሎም የሚባል ሰው ነበር። ታዲያ አቶ አይችሎም በአንድ ቀን ውስጥ ሰላሳ ጊዜ የሚገልጣት አባባል ነበረችው። “የፈረንጅ ዘፋኝ <አይ ካን ፍላይ> ይላል፣ እኛ ደግሞ አልበር እንደ አሞራ ሰው አርጐ ፈጥሮኛል እንላለን” ይላል። አቶ አይችሎም (ይችላል?)። እናም አሁን ለምን እንደሆነ አላውቅም እናንተን ሳስብ ይህ የአቶ አይችሎም የዘወትር መዝሙር ውልብ ይልብኛል።
#እናም እናንተ አገር ቤት የገባችሁ የፓለቲካ ድርጅቶችና አመራሮች የኢትዮጵያን ብርቅዬ አፈር ከረገጣችሁ በኃላ የሰራችሁትን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ ስራ ንገሩን። በአደባባይ፣ ስቴዲዮም፣ አዳራሽ ምን ያህል ጊዜና ህዝብ ሰበሰባችሁ? መቼም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚባል ሰበብ አሁን እንደሌለ ለማንም ግልጥ ነው። …”ሕዝባችን!” በማለት የተናገራችሁት ወርዳችሁ አናግራችኃል? የት የት አካባቢ?… በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሽግግር ሂደት ላይ ድርጅታዊ ተሳትፎአችሁ ምን ይመስላል?…
 ለማንኛውም እንደ ” ማይክል ቦልት” መፍጠን፣ አሊያም እንደ “አሞራዋ” መብረር ቢያቅታችሁ እንኳን እንደ “ሰው!” ሁኑ።
Filed in: Amharic