>
5:13 pm - Saturday April 18, 9587

ፕ/ሮ መስፍን ከኢሳያስ አቀባበል ባለፈ!?! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ፕ/ሮ መስፍን ከኢሳያስ አቀባበል ባለፈ!?!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
ፕ/ር መስፍን የኤርትራውን መሪ ኢሳያስ አፈወርቄን ለመቀበል በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት እንዲታደሙ መጋበዛቸውን ሰማሁና ደስ አለኝ። ይኸ የሀገር ዋርካ; እውነተኛ ኢትዮጵያዊ; ያልተጋበዘ ሌላማ ማን ሊጋበዝ ይችላል? እንኳንም በህይወት ኖረው ይህን ታኣምር አዩ። እኔ ግን ይኸ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ምሁር ዕድሉ ተሰጥቷቸው የሆነ ነገር ቢሉ ብዬም ተመኘሁ!
ፕ/ር መስፍን በባህሪያቸው ሞገደኛ ናቸው። ካልመሰላቸው እስከጥግ ይሞግቱሃል። ካስፈለገም ልክ ልክህን ሊነግሩህ ይችላሉ። እሳቸው ጋር ማስመሰልና ተመሳስሎ መኖር አይታወቅም። ሰውዬው “የግንባር ሥጋ” የሚሉት ዓይነት ናቸው። የሚሰማቸውን እንደወረደ የሚናገሩ ግልፅ ሰው ናቸው። ይኸ ባህሪያቸው ነው። ልንወድደውም ልንጠላውም እንችላለን።
አንድ የማንለያይበት ሀቅ ቢኖር ግን አዋቂነታቸው ነው። ይሁንና ዕውቀትን እንደወረደ ተቀብለው; ምሁር ተብለውና በዚህ ተኮፍሰው መኖር የሚፈልጉ አይደሉም። ሰውዬው አሰላሳይና ተንታኝ ናቸው። አብዛኞቻችን በጥቅሉ “ትክክል” ብለን የተቀበልነውን ነገር እሳቸው “ብትንትን” አድርገውና ፈረቃቅጠው ሌሎቻችን ያላየነውን የማዬትና የማሳየት ብቃት አላቸው። በዚህም ሳቢያ “አወዛጋቢ” እስከመባል ደርሰዋል። ግሪካውያኑ ፈላስፎች እነ ሶቅራጥስኮ በዘመናቸው ተወግዘውና በብዙሃን ድምፅ መርዝ ጠጥተው እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል። ከሞቱ በኋላ ግን አስተምህሮአቸው ብቻ ሳይሆን በእሳቸው ላይ የተሰጠው ፍርድና የፍርድ አሰጣጡም ዘመን ተሻግሮ “Socratic trial” እየተባለ በዩኒቨርሲቲዎች ስለፍትህ መማሪያ ሆኗል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ፕ/ር መስፍን ካለፉ በኋላ የእሳቸውን አስተሳሰብና አስተምህሮ እየጠቀስን (ምናልባትም በልጆቻችንና በልጅልጆቻችን ዘመን) መማራችን አይቀርም። ፕ/ሩ ግን አሁን በህይወት አሉ። ግና በህይወት እያሉ ይህን ሰውዬ ምን ያህል ተጠቅመንባቸዋል? በተለይ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ፕ/ር መስፍንን ቤተ-መንግሥት ድረስ እየጠሩ ከኢትዮጰያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ብዙ ተጨባጭ እውቀት መቅሰም ይችላሉ። በተለይ ዶ/ር አብይንማ እንደፖለቲከኛና የመንግሥት መሪ ብቻ ሳይሆን የሀገር ባለውለታም ጭምር አድርገው የሚያዩት ይመስለኛል። እናም ፕ/ር መስፍን ያላቸውን ሁሉ አሟጥጦ ቢወስድ ደስ እንደሚላቸው ይ
መገመት ይቻላል።
ለሌሎቻችንም ቢሆን የፕ/ሩ ቤት ክፍት ነው። በሳቸው ቤት ዕድሜህ; የት/ደረጃህ; ዘርህ; የፖለቲካ አቋምህና የጀርባ ታሪክህ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። እሳቸው ጉዳያቸው ከሀሳብህ/አስተሳሰብህ ጋር ነው። ከእሳቸው ጋር በሀሳብ ብትለያይ ደንታ አይሰጣቸውም። ግና ማጣፊያው እስከሚያጥርህ ሊሞግቱህ ይችላሉ። በውጤቱም ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ስለሙግት አመራር ሥርዓትም ተምረህ ልትወጣ ትችላለህ። በዕድሜ ጠገብ መጽሐፍትና የተለያዩ ድርሳናት ሸክም የጎደጎደ ቤታቸውን አይተህ ልትደመምና  አዋቂ” ነኝ ብለህ የምትኮፈስ ከሆነም የዕውቀት ጥግ ከእይታህ ውጭ መሆኑን ልትገነዘብ ትችላለህ። ይህን የምነግርህ ከራሴ ገጠመኝ ተነስቼ ነው።
እናማ ይህን ሀገር ወዳድ; ተመራማሪ; አሰላሳይ ምሁር; እውነተኛ ፕ/ር (the real professor) እና የሀገር ሀብት በህይወት እያሉ እንጠቀምባቸው!
ረጅም ዕድሜና ጤና ለአንጋፋው ምሁርና የኢትዮጵያ ልጅ ለፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም!!!
Filed in: Amharic