>

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ፣ (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ፣
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
ለአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ “ከንቲባ” ለመሾም እንደተዘጋጁ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተነገረ ነው። የሚሾሙት “ከንቲባም” የከተማው ምክር ቤት አባል አለመሆናቸው እየተገለጠ ነው። በእኔ እምነት ይህ አካሄድ ህገ ወጥ ከመሆኑም በላይ ተመራጭ አካሄድ አይደለም። እንደ አንድ ሞጋች ደጋፊዎ ምክንያቶቼንና መፍትሔውን ለመጠቆም እፈልጋለሁ።
ምክንያቶች፣
#ምክንያት አንድ -:
የአዲስ አበባ ምክርቤት በህዝብ የተመረጠ ነው/ የተመረጠ አይደለም የሚል ክርክር ውስጥ ሳልገባ ምክርቤቱ የተሰጠውን አምስት አመት ጨርሷል። ከዚህ በኃላ ይሄ ምክር ቤት ቀጠለ ማለት ከተሰጠው የስራ ዘመን በላይ በህገ ወጥነት ቀጠለ ማለት ነው። በራሳችሁ  ህገ መንግስትም ሆነ በአስተዳደሩ ቻርተር ያለ ህዝብ ምርጫ የመንግስት ስልጣን መያዝ እንደማይቻል በግልፁ ተቀምጧል።
#ምክንያት ሁለት :- 
እንደዚህ አይነት አካሄድ ለነገ የሚሰጠው ትምህርት አደገኛ ነው። ነገ ሌላውም ተነስቶ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል። በትግራይ ደብረጺዮንን ለማንገስ ከተካሄደው መንግስት ግልበጣ የባሰም ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል። የባሰ የሚያደርገው የትግራይ ምክር ቤት ዘመኑ ያላለቀ በመሆኑ ነው።
#ምክንያት ሶስት:- 
የአዲስ አበባ ከንቲባ መመረጥ/ መመደብ ያለበት በነዋሪዎቹ ይሁንታ እና ተቀባይነት ያተረፈ ሊሆን ይገባል። ከዚህ በፊት አንድ እግራቸውን ባህርዳር፣ ጊሚር፣ ወለጋ(?)፣ አርሲ(?) …ወዘተ ሌላው እግራቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ከንቲባዎች የፈጠሩት ችግር የሚታወቅ ነው። የከተማው ሕዝብና ታዋቂ ፓለቲከኞች ለከንቲባዎቹ የሰጡት ስያሜም የሚረሳ አይደለም። ለምሳሌ አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ዶክተር ኃይሉ አርአያ አስተዳደሮቹን “ምስለኔ!” በማለት በተደጋጋሚ ይጠሯቸው ነበር።
#ምክንያት አራት: –
 አሁን ዘመኑን የጨረሰውና 138 መቀመጫ የያዘው የአዲስ አበባ ምክርቤት አባላት በይዘቱ ፀረ ለውጥ ነው። የምክርቤቱ አባላት የተመለመሉት በቀን ጅቦቹ ፊት አውራሪነት በመሆኑ የዲሞክራሲም ሆነ የለውጥ ሽታ የላቸውም። አንዳንዶቹም ወደ ምክር ቤቱ የገቡት በኔትወርክና የብሔር ታፔላ ነው። የምክርቤቱ አባላትን ጨምሮ በካቢኔ የተሾሙት አቅም የሌላቸው ናቸው። አቅም ቢኖራቸው ኖሮ ለአዲስ “ከንቲባነት” ከውጭ አይፈለግም ነበር።ድሪባ ኩማን ከንቲባ ፣ ኃይሌ ፍስሃን የማዘጋጃ ቤት ሃላፊ፣ ተወልደን የምክር ቤቱ ጠርናፊ፣ ሺሰማን የገንዘብ ሀላፊ ያደረገ ምክርቤት ለዶክተር አቢይ ቀጣይ ጉዞ እንቅፋት መፍጠሩ የማይቀር ነው። ዶክተር አቢይ የቀን ጅብ የሆነውን የህውሓት/ኢህአዴግ መዋቅር ማፈራረስ ካለበት ከላይ የተጠቀሱትን ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል።
  መፍትሔ
#መፍትሔ አንድ: –
  የከተማው ምክርቤት አምስት አመት የእድሜ ዘመኑን መጨረሱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ እንዲሰናበት ማድረግ። ይሄ ህጋዊም ነው። ተገቢም ነው። በተግባርም የታየ ነው። በ1995 ዓም አቶ መለስ ዜናዊ ለራሱ የስልጣን ማቆያና ዘረኝነቱን ለማስፋፋት ሲል እድሜ ያልደረሰውን የከተማው ምክር ቤት ህገ ወጥ በሆነ መልኩ መበተኑ ከሁላችንም ህሊና የሚጠፋ አይደለም። እርግጥ በወቅቱ የነበረው ቻርተር በአዲሳባ ህዝብ የተመረጠውን ምክርቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያፈርሱት ይችላሉ ስለሚል የህግ ጉዳይ መነሳት የለበትም የሚሉ ሰዎች አሉ። እዚህ ላይ ዘወትር ከጭንቅላቴ የማትጠፋ መራር እውነት በስላሽ አስገብቼ ላጫውታችሁ።
  (ወቅቱ አቶ መለስ የአዲስ አበባን ምክርቤት ሊያፈርስ እንደሆነ በመዲናይቱ በሰፊው የሚነገርበት ነበር። የዛን አካባቢ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ቤተሰብ ሞቶባቸው ለቅሶ ተቀምጠዋል። እናም ለቅሶ ለመድረስና ለማጽናናት ዛሬ በጋዜጠኝነት እና የዲሞክራሲ ታጋይነታቸው ድፍን ኢትዮጵያዊ የሚያውቃቸው ሰዎች ፕሬዝዳንቱ ቤት ይገኛሉ። በጨዋታ መሐል አቶ መለስ የአዲስ አበባን ምክርቤት ለማፍረስ ማሰባቸው ወደ ሞቀ አጀንዳነት ይመጣል። ዶክተር ነጋሶ ይሄን ሲሰሙ ተቆጡ። የሰውየው እርምጃ ህገ ወጥና ሕገ መንግስቱን የሚንድ ስለሆነ ሊቆም ይገባል ብለው ተከራከሩ። ከሀዘናቸው መልስ የአቶ መለስን ኢ-ህገመንግስታዊነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያጋልጡ ዛቱ። ለቅሶ ሊደርሱ የሄዱት ጋዜጠኞች በዶክተር ነጋሶ ንግግር ከመገረማቸውም በላይ ደነገጡ። አንዱ ጋዜጠኛ ለዛ ባለው አማርኛ ” ዶክተር የከተማው ቻርተር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክርቤቱን እንደሚያፈርስ በፊርማ ያፀደቁት እርሶ እኮ ኖት፣ ሳያነቡ ነው እንዴ የፈረሙት?” አላቸው። ይቺን ታሪክ ” የነጋሶ መንገድ” የሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደማገኘው ገምቼ ነበር። ግምቴ ትክክል አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሕገ መንግስቱ ሕዝቡ ያልተወያየበት ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ያልተሳተፋበት “የኢህአዴግ ፕሮግራም ነው” የሚለው ደመቅ ብሎ ተጽፏል።)
  የሆነው ሆኖ ዶክተር አቢይ ይሄንን ምክርቤት የሚያሰናብተው እድሜውን የጨረሰ በመሆኑ ነው። እንደውም ሁኔታውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ይኖርበታል። ተቀናቃኝ ከሆኑ ፀረ ለውጥ ሐይሎችም ከህገወጥነት አንፃር የሚነሳበት ጥያቄ አይኖርም።
#መፍትሔ ሁለት: – 
ዶክተር አቢይ ዘመኑን የጨረሰውን ምክርቤት ካባረረ በኃላ እስከሚቀጥለው የፌዴራል ምርጫ ድረስ ” የአዲስ አበባ የሽግግር መንግስት” አሊያም ” ባለ አደራ አስተዳደር” መመሰረት ይኖርበታል። ዶክተር አቢይ ከውስጥ ስሜት በመነጨ ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርአት አስተዋጽኦ አላቸው ብሎ የሚያምን ከሆነ ” የአዲስ አበባ የሽግግር መንግስት” ቢመሰርት የተሻለ ይሆናል። ይሄን ማድረግ ለዶክተር አቢይ ክብርና ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተርፍለታል። በአዲስ አበባ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ታሪኩን በድጋሚ ያሰፍራል። እዚህ ላይ የሚቋቋመው ካቤኔ ተሳታፊ የሚሆኑት (የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ) በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያላቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸው ከሶስተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የሆኑ ቢሆን ይመረጣል። በዚህ አጋጣሚ አሁን በከንቲባነት ይሾማሉ ተብለው ስማቸው የተነገረው ሰው መስፈርቱን የማሟላት እድል ስላላቸው ብዙ የሚያሳስብ አይደለም።ዶክተር አቢይ የአዲስ አበባ የሽግግር መንግስት ለመመስረት አስቸጋሪ ከሆነበት በቴክኖክራቶች የሚመራ “ባለአደራ አስተዳደር” መመስረት ይችላል። ቴክኖክራቶቹን የሚያማክር የአገር ሽማግሌዎችን የያዘ አማካሪ ምክር ቤት ቢያቋቁም ደግሞ የበለጠ ተመራጭ ይሆናል።
    እዚህ ላይ አንድ ነገር አስምሬ መሄድ እፈልጋለሁ። ከምርጫ 97 በኃላ የአዲስ አበባ ምክርቤት ምርጫ ከፌዴራሉ ተለይቶ ከሁለት አመት በኃላ እንዲካሄድ የተወሰነው መቀልበስ አለበት። ከምርጫ 97 በኃላ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ይኖርበታል። በመሆኑም የፌዴራል የፓርላማ ምርጫና የአዲስ አበባ ምክርቤት ምርጫ በተመሳሳይ ወቅት መሆን ይኖርበታል። ዶክተር አቢይ ምርጫዎቹ ሆን ተብሎ በተለያየ ወቅት እንዲካሄድ የተደረገበትን ሴራ ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስለኛል። የማታውቀው ከሆነም አጠገቦት ያለውን ፍፁም አረጋ ጠይቁት። ስለተሳተፈበት በዝርዝር ያውቀዋል። ጊዜ ካገኙ ደግሞ ” የመለስ ትሩፋት: ባለቤት አልባ ከተማ” የሚለውን መጽሐፍ እንዲገርቡት ፍቃዶት ይሁን።
Filed in: Amharic