>
5:13 pm - Sunday April 20, 1919

ከድሃ ላይ መስረቅን የመሰል የሚያፀይፍ ነገር የለም!!!  (ይልማ ኪዳኔ)

ከድሃ ላይ መስረቅን የመሰል የሚያፀይፍ ነገር የለም!!! 
ይልማ ኪዳኔ
አፍሪካ ውስጥ የኤርትራ ህዝብን ህዝብ ያህል በመሪው መኩራት የሚገባው ህዝብ ያለ አይመስለኝም። ይህ ጽሑፍ የኤርትራን ፖለቲካ አይመለከትም። ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድን ይዘው ወደ ቤታቸው ወሰደው ያደረጉላቸውን መስተንግዶ የሚያሳየውን የቪዲዮ ክሊፕ ስመለከት የተሰማኝን ስሜት ለመግለጽ ይቸግራኛል። ሲጀምር ፕሬዚዳንቱ በጉርብትና ከህዝቡ ጋር እንደ አንድ ተራ ሰው መኖራቸው እጅግ በጣም ደንቆኛል። ሲቀጥል ቤታቸውና ኑሮሃቸው ከተራው ህዝብ የተለየ ያለመሆኑ የእህልም ያህል ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ገርሞኛል። ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቡና አፍልተው እና ዳቦ ቆርሰው ያደረጉት መስተንግዶ ግን በእጅጉ ልቤን ነክቶታል። ያየሁት ሁሉ ፕ/ት አኢሳያስ አፈወርቂን እጅግ በጣም አድርጌ እንዳከብራቸውና እንድወዳቸው አድርጎኛል።
………………………………………………
ወደ እኛው አገር ስንመጣ አንድ ተራ የቀበሌ ካድሬ ከህዝብ በዘረፈው ገንዘብና ሓብት ከፕሬዚዳንት አሳያስ አፈወርቂ በተሻለ ቤት ውስጥ ይኖራል። ከስር ፎቶግራፉ ላይ የሚታየውን የወያኔውን ጄኔራል አብረሃ ወልደማሪያም ቤት ተመልከቱና የፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂን ቤት አስቡት። ከሁለቱ ማነው በእንዲህ ዓይነት ቤት መኖር የሚገባው? ጄኔራሉ መቶ ዓመት ቢሰሩ በሚያገኙት ደሞዝ ቤተሰብ አስተዳድረው፣ ይህን የመሰለብ ቤት ሰርተው መኖር ይችላሉ? ወይስ የህዝብን ሀብትና ንብረት መዝረፍ ሞያቸው ሆኖ ነው? ሌብነት የመንግስት ፖሊሲ እስኪመስለን ድረስ የህዝብ ሃብትና ንብረት መዝረፍ ተራ ነገር የሆነበት ስርዓት ወያኔ መፍጠር ችላለች። ይህ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም ይኖርበታል። ከህዝብ የተዘረፉ ሃብትና ንብረቶች መመለስ ይኖርባቸዋል። ሌቦቹንም እንደ ጥፋታቸው የሚገባቸውን ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከራሱ ተርፎ የሚዘረፍ ሃብትና ንብረት የለውም። ሰላም ስጡት። ጥሮ ግሮ ያገኛትን ትንሽ ሳንቲም ቢሆን መዝረፍ አቁሙ!!! ምድረ እፍረተ ቢስ ሌባ ሁላ አደብ ግዙ!!!
Filed in: Amharic